ትንሿን ብርሐን ለነገ መዳረሻ

0
219

ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ትምህርት ቤት ሄደው ትምህርታቸውን መከታተል በማይችሉበት ወቅት ለአሉታዊ አስተሳሰቦች እና ላልተፈለጉ ልማዶች ተገዥ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው:: በሰሜን ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የነበረው ጦርነት በርካታ ትምህርት ቤቶች መማር ማስተማር መስጠት እንዳይችሉ ተደርገው ለጉዳት ተዳርገዋል:: መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ብዙ ሴት ተማሪዎች ተደፍረዋል፤ ቤተሰቦቻቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ አጥተዋል፤ ሲገደሉ አይተዋል፤ ከጦርነት ሽሽት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል:: እነዚህ ሁሉ ችግሮች ብዙዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል:: የጀመሩትን ትምህርትም እንዳያስቀጥሉ አድርጓቸዋል::

ግጭቱ አሁንም በአማራ ክልል መቀጠሉ ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ አድርጓል:: ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተማሪዎች ደግሞ አሁንም ወደ ትምህርት ገበታቸው አልመጡም::

የጥይት ድምጽ በተደጋጋሚ መሰማት፣ የመንገዶች መዘጋት፣ በተለያዩ ቦታዎች እየተስተዋሉ ያሉ ዝርፊያዎች እና እገታዎች አሁንም ተማሪዎች ትምህርታቸውን የማስቀጠል ፍላጎት የገቱ ሆነው ይነሳሉ:: እነዚህም ችግሮች በአንዳንድ አካባቢዎች ተማሪዎች የጀመሩትን ትምህርት እንዲያቋርጡ አስገድደዋል:: ለመሆኑ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በተማሪዎች ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ከሥነ ልቦና አንጻር እንዴት ይታያል?

አቶ የሺዓምባው ወርቄ የሥነ ልቦና ባለሙያ ናቸው:: ሥነ ልቦና ስለ ሰው ልጅ አስተሳሰብ፣ ስሜት እና ባህሪ የሚያጠና የሳይንስ ዘርፍ መሆኑን በቅድሚያ አንስተዋል:: ከዚህ አኳያ በየትኛውም ዘርፍ የተሰማራ አንድ ሰው ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ጠንካራ ሥነ ልቦናን መገንባት ሲችል እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል:: ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ እያጋጠሙ ያሉ ማኅበራዊ ቀውሶች ሰዎች በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ እንዳይሆኑ እያደረጉ ይገኛል::

ባለሙያው አካላዊ ሕመሞችን በመድኃኒትና በተለያዩ ሕክምናዎች አክሞ ማዳን፣ ምጣኔ ሐብታዊ ቀውሱንም በሥራ መመለስ ቢቻልም በተለያዩ ምክንያቶች ለሚደርሱ ሥነ ልቦናዊ መታወኮች የተሰጠው ትኩረት ግን አናሳ መሆኑን አንስተዋል:: እንደ ጦርነት የመሰሉ ማኅበራዊ አለመረጋጋቶች ሰዎች ለጭንቀት፣ ለድባቴ፣ ብዙዎች ለሕይወታቸው ልዩ ትርጉም እንዳይሰጡ ይልቁንም ለተስፋ ቢስነት ተገዥ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል:: ለችግሮች መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ ከጭንቀት ለመውጣት ሱስን ብቸኛ አማራጭ ያደርጋሉ:: ይህ ሱስ ደግሞ ነገ በሽታና ህመም ሆኖ ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ አስሮ ያስቀምጣቸዋል::

የተፈጠረው የሰላም መናጋት ችግር ከግለሰብ ግለሰብ የተለያየ መልክ እንዳለው የሥነ ልቦና ባለሙያው ጠቁመዋል። በተለይ ችግሩ በታዳጊ ተማሪዎች ሥነ ልቦና ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ ከፍተኛ እንደሚሆን ተናግረዋል::

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች ከትምህር ውጪ በሚሆኑበት ወቅት የሚያጋጥማቸው አእምሯዊ መረበሽ እና የሐሳብ መበተን በሕይወታቸው ተስፋ ካደረጉበት ቦታ እንዳይደርሱ ያደርጋቸዋል:: የሰው ልጅ ስለ ነገ እንዲኖር የሚያደርገው ተስፋ በዚህ ምክንያት ሲገታ አዕምሯቸው አሉታዊ ነገሮችን ያስተጋባል:: ይህም ለድብርት፣ ለጭንቀት እና ለተለያዩ ሱሶች ተገዥ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል::

የስሜት ዝቅታም ሌላው በችግሩ ያለፉ ተማሪዎች መገለጫ እንደሆነ አቶ  የሺዓምባው ተናግረዋል:: በተለይ ችግሩ ከሁለት ሳምንት በላይ የሚዘልቅ ከሆነ የመኖር ጉጉት ማጣት እና ተስፋ ቢስነት ስሜት እየጎለበተ ይሄዳል:: ስለ መኖር አለማሰብ፣ ራስን መውቀስ፣ ከሰው የመነጠል ስሜትም ያጋጥማል::

አደጋ ከተከሰተ በኋላ የሚያጋጥመው የሥነ ልቦና መታወክ (ድህረ አደጋ ሰቀቀን) ሌላው ተማሪዎች በትምህርታቸው ብቁ እንዳይሆኑ ሊደርጋቸው ይችላል:: በግጭት ቦታ ሆነው ሰዎች ሲገደሉ  ያዩ፣ ወላጆቻቸው የተገደሉባቸው እና ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ወገኖች ለድረ አደጋ ሰቀቀን ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ባለሙያው ጠቁመዋል::

እነዚህ ልጆች ግን የደረሰባቸውን ችግር ተናግረው መፍትሄ ለማግኘት ሰው ላይጠይቁ እንደሚችሉ ተናግረዋል:: በዚህ ወቅት የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ተማሪዎች ስሜታቸውን አውጥተው እስከሚናገሩ ከመጠበቅ ይልቅ አካላዊ ስሜታቸውን በዕይታ መረዳት እንደሚያስፈልግ ባለሙያው አስገንዝበዋል:: የመረበሽ፣ በቀላሉ የመቆጣት፣ ብቸኛ መሆን፣ የትምህርት አፈጻጸማቸው መቀነስ… ሊስተዋል ይችላል::

ተማሪዎች ከጦርነት በኋላ ወደ ትምህርት በሚመለሱበት ወቅት ያሳለፉት የችግር ወቅት ከአእምሯቸው ስለማይጠፋ ወጣ ያሉ ባህሪያትን ሊያሳዩ እንደሚችልም ባለሙያው ጠቁመዋል:: እናት ወይም  አባቱ ሲገደል ያየ ታዳጊ አዕምሮው የሚያስበው የተጠቂነት እና የአቅመ ቢስነት ሥነ ልቦና በመሆኑ ከመጠቃት ይልቅ ማጥቃትን (በቀል) ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ሊነሳ ይችላል:: እናም ይህ ሁኔታ በሰዎች ላይ በሚስተዋልበት ወቅት ያለፉ ታሪኮችን በመጠየቅ ስሜታቸውን መጋራት፣ ችግራቸውን መካፈል፣ አለሁልህ/ሽ/ በማለት ወደ ነበሩበት ሕይወት እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል::

ከግጭት ወይም ጦርነት መልስ ተማሪዎች ለትምህርት ቤት ሕግና ደንብ ተገዥ ላይሆኑ እንደሚችሉም ቀድሞ መረዳት እንደሚገባ ባለሙያው ጠቅሰዋል:: ታዲያ በዚህ ወቅት መምህራን እና የትምህርት አመራሩ ተማሪዎችን በጥፋተኝነት ከመፈረጅ ይልቅ አቅርቦ ህመማቸውን መረዳት እንደሚገባ አሳስበዋል:: በዚህ ወቅት እያንዳንዱ መምህራን የሥነ ልቦና ባለሙያ ሆኖ ተማሪዎች ከገቡበት ያልተገባ ባህሪ እንዲወጡ ማድረግ እንደሚኖርበት ጠቁመዋል::

አንዳንድ ችግሮች እኛ የማንቆጣጠራቸው፣ ምናልባትም የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት አስተዋጽኦ የማናደርግባቸው ሊሆኑ እንደሚችልም የሥነ ልቦና ባለሙያው በመጥቀስ ያስረዳሉ:: ሰዎች ተጽእኖ በማያደርጉባቸው ችግሮች ላይ አብዝተው በተጨነቁ ቁጥር ተስፋ የማጣት፣ “ዋጋ የለኝም” ብሎ የማሰብ፣ “ምንም ነገር ማድረግ አልችልም” የሚል አቅመ ቢስ ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ ውጤታማ እንዳይሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል:: ይህ አይነቱ ችግር በተለይ በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑን የሥነ ልቦና ባለሙያው አብነት እያነሱ ያስረዳሉ::

ተማሪዎችም አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ሲደረግ ከእነሱ የሚጠበቀውን ለተነሱለት ዓላማ ስኬት የሚያበቃቸውን  ብቻ ከመከወን ውጪ ስለሌላ ነገር ሊያስቡ አይገባቸውም:: በተለይ “ዛሬ የተከፈተው ትምህርት ነገ ይዘጋ ይሆን፣ ለፈተናስ እንደርሳለን፣ ይዘቱስ በወቅቱ ይሸፈን ይሆን?” የሚሉ ጉዳዮች ተማሪዎችን ሊያስጨንቁ እና ሊያሳስቡ የሚችሉ ጉዳዮች አለመሆናቸውን አስታውቀዋል:: ምክንያቱም እነዚህን ክስተቶች ተማሪዎች የሚቆጣጠሯቸውና ተጽእኖ የሚያደርጉባቸው አይደሉምና ነው::

እንደ ባለሙያው እምነት ከተማሪዎች የሚጠበቀው የሚሰጠውን ትምህርት በንቃት መከታተል፣ ከትምህርት ውጪ የሆኑ ጊዜያትን በአግባቡ መጠቀም፣ ለነገ ግብ አወንታዊ ምልከታ ማድረግ ብቻ ነው:: አወንታዊ ምልከታ ሲባል ችግር እንደሌለ አድርጎ ማሰብ ሳይሆን ችግሮችን በበጎ መንገድ መመልከት ነው::

የችግሩ ግዝፈት ሰዎች ካላቸው ሥነ ልቦናዊ አቅም ጋር ሳይመጣጠን ሲቀር የሚፈጠሩ ችግሮች ደግሞ ሰዎች እንዳይረጋጉ የሚያደርጉ ናቸው:: ነገር ግን በዚያ ጉዳይ ላይ የራስ አስተዋጽኦ ምንድን ነው? ብሎ ማሰብ ካለመረጋጋቱ ለመውጣት ያስችላል:: በመሆኑም ተማሪዎች ትምህርት በሚጀምሩበት ወቅት በምንም አይነት ችግር ተጠልፈው ባለመውደቅ ከዓላማቸው ለመድረስ  ሥነ ልቦናቸውን ሊያጠነክሩ ይገባል:: ከሚገጥም ችግር ለመውጣትም በጎ ሐሳብን ማዳበር፣ ነገን አጨልሞ ከማየት ትንሿን ብርሐን አስፍቶ ማየት ያስፈልጋል::

ችግር እና መከራን አብዝቶ ማውራት ሰዎች ይበልጥ እንዲረበሹ፣ ተስፋ እንዲያጡ፣ የባዶነት ስሜት እንዲነግሥ፣ ለክፉ ሐሳብ ተገዢ የመሆን አስተሳሰብ እየሰፋ እንደሚሄድ የሥነ ልቦና ባለሙያው አስታውቀዋል:: በመሆኑም ልጆች ከተስፋ መቁረጥ ወጥተው በተስፋ አሻግረው ወደሚመለከቱት መዳረሻ እንዲጓዙ የሚያደርጉ በጎ ነገሮችን ማስተጋባት ከወላጆች እንደሚጠበቅ አቶ የሺዓምባው ተናግረዋል:: ሰዎች አንድ ቦታ ላይ የሚደርሱት ሲጀምሩት ነው ያሉት የሥነ ልቦና ባለሙያው፣ ለዚህም ያልጨረስነውን ከማየት ይልቅ በጀመርነው ላይ ትኩረት ማድረግ ለውጤት እንደሚያበቃ አስገንዝበዋል::

ትምህርት ያልጀመሩ ተማሪዎችም “ለራሴ ያለሁት እኔ ነኝ” የሚል አመለካከትን በማዳበር ካልተፈለገ አካሄድ ራሳቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ አሳስበዋል:: ነገን በአወንታ መመልከት፣ ቤተሰብን በሥራ ማገዝ፣ ዕውቀትን ሊያስጨብጡና አስተሳሰብን በመልካም ሊቀይሩ የሚችሉ መጽሐፍን ማንበብ፣ ነገ ትምህርት እንደሚጀመር አስቦ ለትምህርት ራስን ዝግጁ ማድረግ፣ ትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት ጊዜ አጥተው ወደ ጎን ትተዋቸው የነበሩ የተለያዩ ክህሎቶቻቸውን ማየት ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን ተከትሎ ወዳልተፈለገ ቦታ የማምራት ፍላጎታቸውን ለመግታት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሐሳቦች አድርገው አቅርበዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here