ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
በአውሮፓዊቷ የባሕር ሰርጥ በጣሊያን መዲና ሮም ከተማ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ራሷን የቻለች በዓለም ትንሿ ሀገር ትገኛለች፡፡ ይህቺ ሀገር ቫቲካን ትባላለች። በደቃቋ የዓለማችን ሀገር እየተንሸራሸርን የውስጥ መስህቦቿን እንዲሁም ታሪኳን እየቃኘን አብረን እንቆይ።
በሮም ከተማ ውስጥ ያለች ሀገር፣ ያውም በ0.44 ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት ላይ የተቀመጠች እና የሕዝብ ቁጥሯ 825 ብቻ የሆነ ሀገር አለች ቢሉ ለማመን ይከብድ ይሆናል፣ ግን ይህ የማይታበል እውነት ነው። ስፋቷ እና የሕዝብ ቁጥሯ ማነስ በዓለም ትንሿ ሉዓላዊት ሀገር ወይም መንግሥት አስብሏታል። ዙሪያዋን 12 ሜትር በሚረዝም ግምብ ታጥራለች። ቫቲካን የተቆረቆረችው በሞንስ ቫቲካነስ ኮረብታ ላይ ነው። ስሟም የመጣው “ቫቲካናሪ” ከሚል የላቲን ቃል ሲሆን “መተንበይ” እንደማለት ሆኖ በሮማውያን ዘመን በአካባቢው የሚያዘወትሩትን ትንቢተኞችን ይወክላል።
የቫቲካን ከተማ በታይበር ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ ላይ ትገኛለች። ዙሪያዋን በመካከለኛው እና በተሀድሶ ዘመን የተገነቡት የግንብ ቅጥሮቿ ወሰኖቿን ከልለዋል። በሁሉም አቅጣጫ ብቸኛ አዋሳኟ የሮም ከተማ ናት። ሀገረ ቫቲካን ስድስት በሮች አሏት፤ ከእነዚህ መካከልም ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ሦስቱ ብቻ ናቸው። እነርሱም ፒያሳ፣ አርኮ ዴሌ ካምፓኔ የተሰኘው ከቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ያለው መግቢያ እና ወደ ቫቲካን ቤተ መዘክሮች “ጋላሪዎች” የሚወስደው መግቢያ በሚል የሚታወቁት ናቸው።
አጠቃላይ ሕዝቧ 825 ናቸው። ሆኖም 104 የስዊዝ ጋርዶች አባላትን ጨምሮ 246 ሰዎች ብቻ በቅጥሩ ውስጥ ይኖራሉ። በግምት ግማሽ የሚሆነው ሕዝቧ በአገልግሎት ምክንያት ከሀገሪቱ ውጭ ይኖራሉ። የቫቲካን ዜግነት በትውልድ ወይም በደም የሚገኝ ሳይሆን እዚያው ለሚኖሩ እና ለቫቲካን ለሚሰሩ የሚሰጥ ነው። bቫቲካን ከተማ ወይም በሮም የሚኖሩ ካርዲናሎች እንዲሁም ዲፕሎማቶችን እንደ ዜጋ ይቆጠራሉ። የአገልግሎት ዘመኑ እንዳበቃ የሰውየው ዜግነት ይሰረዛል። ሕፃናት ከወላጆቻቸው ዜግነቱን መውረስ አይችሉም። በቫቲካን ጥምር ዜግነትን የተፈቀደ ነው።
በሮማውያን ዘመን ከሮም ከተማ ውጭ ያለውን አካባቢ እንደገና በማፍረስ ቪላዎች፣ የንጉሥ ካሊጉላ እናት በአግሪፓ የአትክልት ስፍራዎች እና በዋና መጋቢ መንገዶች አጠገብ የመቃብር ስፍራዎች ተከልለውበታል። ንጉሥ ካሊጉላ ደግሞ በእናቱ የአትክልት ስፍራዎች ውስጥ የፈረስ መወዳደሪያ መም አስገንብቷል።
ንጉሥ ካሊጉላ ከግብፅ ሀገር በሄሊዮፖሊስ ከተማ ላይ ቆሞ የነበረውን ሀውልት ወደ ሮም እንዲያመጡት ወታደሮቹን ባዘዘው መሰረት በአምፊቲያትር ማእከል ላይ እንዲተክሉት አድርጓል። ሀውልቱ ከአንድ ወጥ አለት የተሰራ ከ350 ቶን በላይ የሚመዝን ሲሆን፣ ለአንድ የግብፅ ፈርኦን ክብር ተብሎ የተሰራ፣ ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው። ሀውልቱ በ1578 ዓ.ም ላይ አሁን ተተክሎ ወደ ሚገኝበት የቅዱስ ጳውሎስ አደባባይ መሀል ላይ እንዲዛወር የተደረገ ሲሆን በዚያም እግረ መንገዱን የፀሐይን ጥላ መሰረት በማድረግ ሰዓት ለመቁጠሪያ መሳሪያነት ያገለግል ነበር። በጥንቱ ዘመን የተሰራ አንድ የሮማውያን የመቃብር ስፍራም በቫቲካን ኮረብታ ላይ ይገኛል።
በሀምሳ ስድስት ዓ.ም በሮም ውስጥ የተነሳ አንድ ከባድ የእሳት ቃጠሎ አብዛኛውን የከተማዋን ክፍል ወደ አመድነት በቀየረበት ወቅት ንጉሥ ኔሮ ከወቀሳ ለመሸሽ ሲል ችግሩን በክርስቲያኖች ላይ አላከከ። በመሆኑም ክርስቲያኖችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉ የማድረግ እርምጃ እንደወሰደ ታሪክ ያስረዳል። በስቅላት ከተገደሉት መካከል አንዱ የክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ፣ የሐዋርያት መሪ እና የመጀመሪያው ሮማዊ ጳጳስ ቅዱስ ጳውሎስ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስም በቫቲካን ኮረብታ፣ ጥልቅ ባልሆነ አንድ መቃብር ውስጥ እንደተቀበረ ይታመን ነበር።
ከዓመታት በኋላ በሮማ ግዛት የነገሠው ንጉሠ ነገሥት ቆንስጠንጢኖስ ቀዳማዊ በ305 ዓ.ም ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ አንድ ነገር ሆነ። በቅዱስ ጳውሎስ መቃብር መሀል በጥንታዊው የመቃብር ስፍራ አናት ላይ የቤተክርስቲያን ግንባታ እንዳስጀመረ የታሪክ መዛግብት ዋቢ ናቸው። ቫቲካንን ከክርስትና ታሪክ ጋር በተጨባጭ ማቆራኘት የተጀመረውም ከዚህ ክስተት ወዲህ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል። ቤተ ክርስቲያኑ፣ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን መቃብር አቅፎ ይዟል። ቫቲካን ከጊዜ በኋላ የጳጳሶች ቋሚ መኖሪያ ሆናለች። በተጨማሪም ቤተክርስቲያኑ ለክርስቲያናዊ መንፈሳዊ ጉዞዎች አንድ መንፈሳዊ ማእከል ሆኗል።
በስምንት መቶ ሰላሳ ስምንት ዓ.ም የሳርካን ወንበዴዎች በቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ አቡኑ ሊዎ 4ኛ ቤተክርስቲያኑን እና ተያያዥነት ያላቸውን ህንፃዎች ለመከላከል ሲል የግንብ ቅጥርም እንዲሰራ አዘዘ። በመሆኑም ቁመቱ እስከ 39 ጫማ የሚረዝመው የግንብ ቅጥር በ844 ዓ.ም የተጠናቀቀ ሲሆን ግንባታው እስከ አቡነ ኡርባን 8ኛ ዘመን፣ እስከ 1640ዎቹ ድረስ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ እየተስፋፋ እና እየዘመነ ቀጥሎ የዛሬውን ቅርፅ ይዟል።
በአጭሩ ቫቲካን የተለያዩ የታሪክ ውጣ ውረዶችን አልፋ አሁን የዓለማችን 1.2 ቢልዮን የሮማ ካቶሊክ አማኞች ማእከል እና የዋናው ጳጳስ ቋሚ መቀመጫ ሆናለች። ቫቲካን በምርጫ የሚሰየም ዘውዳዊ ስርአት የተከተለ የራሷ የመንግሥት መዋቅር አላት፡፡ ጳጳሱም ከመንፈሳዊ መሪነት ባለፈ የመንግሥቱ ርእሰ ብሔር በመሆን ያገለግላሉ። የጳጳሱ መደበኛ ማእረግም “የሮም ጳጳስ እና የኢየሱስ ክርስቶስ ቄሰ ገበዝ፣ የቅዱስ ጳውሎስ ወራሽ፣ የሐዋርያት ልዑል፣ የዓለማቀፍ ቤተክርስቲያን ዋና ጳጳስ፣ የጣሊያን መሪ ካህን፣ የሮማውያን አውራጃ ሊቀ ጳጳስ እና የሰበካ ጉባኤ ጳጳስ፣ የቫቲካን ከተማ መንግሥት ባለስልጣን፣ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ባሪያ” የሚል ነው። ጳጳሱ የሚሾሙበት እለትም ብሔራዊ በዓል ተደርጎ ይከበራል።
ሀገሪቱ ካላት የቆዳ ስፋት እና የሕዝብ ቁጥር አንፃር በየዓመቱ የሚጎበኛት ጎብኝ ቁጥር ከሕዝቧ ቁጥር ጋር አይመጣጠንም። በየዓመቱ ከ18 ሚሊየን በላይ ጎብኝ እንደሚጎበኛት መረጃዎች ዋቢ ናቸው። ይህ አኃዝ ቱሪዝም የሀገሪቱ ትልቅ የኢኮኖሚዋ ዋልታ መሆኑን ያሳያል። ዋናው የገቢዋ ምንጭ ግን ለቤተ ክርስቲያን ከሚበረከት ገንዘብ መሆኑን እግረ መንገዳችንን እንጠቁማችሁ።
ቫቲካን የዓለም ወሳኝ የጥበብ እና የቅርፃ ቅርፅ ተምሳሌት የሆኑ ስራዎች መገኛ ናት። እንዲሁም በዓለም ትንሹ ግን ደግሞ በምድራችን ረጅም ዘመን ያገለገለ ሰራዊት (ስዊዝ ጋርድ) ባለቤት ናት።
በጣሊያን ግዛት ሥር የነበረችበትን ግንኙነት ተቋርጦ ነፃ ሉዓላዊነት ሀገር ለመሆን የበቃችው በ1921 ዓ.ም ላተራን ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነበር። በዚህ ስምምነት ነበር ቫቲካን በ44 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውን በግምብ የታጠረ ስፍራ ይዛ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የበቃችው።
የዓለማችንን ትንሿን ሀገር ቫቲካንን በየዓመቱ ከ18 ሚሊየን በላይ ሕዝብ እንዲጎበኛት ያደረጉ ምስጢራት ታዲያ ምን ይሆኑ? ተብለን ከጠየቅን ለአፍታ የከተማዋን ዋና ዋና መስህቦች በፁፋችን ቃኘት ስናደርግ ይመለስልናል። ቫቲካን ሄዶ የቅዱስ ጴጥሮስን አደባባይ እና የቅዱስ ጴጥሮስን ቤተክርስቲያን፣ የቫቲካን የአትክልት ስፍራዎችን፣ የቫቲካን ቤተ መዘክሮችን ሳያዩ መመለስ ከጉብኝት አይቆጠርም።
የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ዋናው የቫቲካን መገለጫ ነው። በዓለም ትልቁ ቤተክርስቲያን እንደሆነም ይነገርለታል። በቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር ላይ የተመሰረተው ይህ ቤተክርስቲያን እንደ ሚካኤል አንጀሎ እና በርኒ ባሉ የተሀድሶ ዘመን እውቅ እውቅ አርክቴክቶች አማካይነት ንድፉ የተሰራለት መሆኑን አመላካች መረጃዎች አሉ። በዓለም ረጅሙን የቤተክርስቲያን ጉልላትም እዚሁ ያገኙታል። ከጉልላቱ ጫፍ ላይ ሆኖ የሮምን ከተማ አስደማሚ ገጽታ ማየት ይችላሉ።
የውስጥ ክፍሉ ከጣሪያ እስከ ግድግዳ በቃላት የማይገለፅ ውበትን ያላበሰው የእነ ሚካኤል አንጀሎ፣ በርኒ፣ ራፋኤል እና ሌሎች ቱባ ሠዓሊያን የስዕል ጥበብ አሻራዎችን ማየት ምንኛ ያስደምማል! በባለ ረዥም ጣራው እና በወለለ ሰፊው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ ሀይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ቅርፃ ቅርፃች በማየት እየተገረሙ፣ ውስጡ ባለው ፀጥታ መንፈስዎ ተረጋግቶ ታድሰው የሚወጡበት አንዱ የቫቲካን የውበት ፈርጥ ነው።
የቫቲካን ቤተ መዘክሮች የተቋቋሙት በአቡነ ጁሊየስ ዳግማዊ በ16ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሲሆን ተከታትለው የነገሡት ጳጳሳትም እያሰፉት ቀጥለዋል። በውስጡ ከ70 ሺህ በላይ ሥዕሎች እና ቅርፃ ቅርፃች ስብስቦች የያዘ ሲሆን በ54 ጋላሪዎች ተከፍሎ ለእይታ ይቀርባል። የተሀድሶ ዘመኖቹ የራፋኤል፣ የካራቫጅኦ፣ የበርኒኒ እና የዳቬንቺ ድንቅ ድንቅ ስራዎችም በቤተ መዘክሮቹ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ ይዘው ይመለከታሉ።
የቫቲካን አትክልት ስፍራዎች የቫቲካን ከተማ ውበት በጣሙን የሚገለጽባቸው ናቸው። የሀገሪቱን አብዛኛውን ክፍል የሚሸፍኑት እነዚህ መንፈስ አዳሽ የአትክልት ስፍራዎች በታበሪ ወንዝ ምዕራብ ዳርቻ ላይ በሚያምር ንድፍ ተዘጋጅተው ይታያሉ።
የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከቤተ ክርስቲያኑ ፊት ለፊት ተዘርግቶ ያለ የሚያምር ክፍት ቦታ ነው። ታላላቅ መንፈሳዊ ዝግጅቶች እና በዓላት ይከወኑበታል፤ ጳጳሱንም በግላጭ ማየት የሚቻልበትም ስፍራ ነው። በአደባባዩ እምብርት ላይ 25 ሜትር የሚረዝም ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተቀረፀ ሀውልት ቆሞ ይታያል። በ1500 ዓ.ዓ በግብፅ ቆሞ የነበረ የታሪክ አሻራ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የቫቲካን ሀዋሪያዊ ቤተ መፃሕፍት ሌላው በቫቲካን የሚገኝ መስህብ ነው። ዋጋ ያልተተመነላቸውን ከ150 ሺህ በላይ ማኑስክሪፕቶችን እና 1.6 ሚሊዮን የታተሙ መፃሕፍትን ይዟል። አብዛኞቹ ከክርስትና በፊት እና ክርስትና እንደጀመረ አካባቢ የተፃፉ ናቸው።
በዓለም ደቃቋን ሀገር ቫቲካንን በወፍ በረር እንዲህ አሳየናችሁ እንጅ በርካታ የሚጎበኙ የመካከለኛውን እና የተሀድሶ ዘመኑን ትንግርት የሚተርኩ በርካታ ቅርሶች አሉ። ወደ 825 ዜጎች ያላት በ44 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈችውን ቫቲካንን ለመጎብኘት ምንም አይነት ፓስፖርት አይጠየቁም። በዓለም ትንሿ ሀገር በርካታ ትላልቅ ድንቃ ድንቆችን ያገኙባታል። ሽርሽራችንን አበቃን።
ምንጭ፡- www.thevaticantickets.com
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም