አነስተኛ መጠን ያላቸው ተሽከርካሪዎች ወይም “ናኖትራክስ” በመስራት ፋና ወጊ ወይም መስራች የሆነው ጆናታን አቦት የሚመሩት የመሀንዲሶች ቡድን በእጅ መዳፍ ሊያዝ የሚችል የሚሰራ ቆፍሮ መዛቂያ “ኤክስካቫተር” መስራታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል::
“N320” ሙሉ በሙሉ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚሰራው “ኤክስካቫተር” ከከፍተኛው መጠን 1/64ኛ የሚያንስ ሞዴል ወይም አምሳያ ነው ተሰርቶ ለእይታ የበቃው::
ጆናታን አቦት በሚመሩት የመሀንዲሶች ቡድን የተሰራውን ሞዴል በድረገጽ በማሳየት በሚፈለገው ወይም በተመረጠ ቁስ በብዛት አምርቶ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ፍላጐት ካላቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉንም ድረ ገጹ አስነብቧል::
ትንሿ “ኤክስካቫተር” ከትልቁ መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ ማንቀሳቀሻ ተሽከርካሪ የብረት ሰንሰለት፣ መቆፈሪያ እና መዛቂያ ወይም መጫኛ ቋት አለው:: የመቆፈሪያው መጠኑ የሚረዝም እና የሚያጥር፣ እንዲሁም በጥልቀት ለመቆፈር የሚያስችል ጥርሶች ተገጥመውለታል::
ጆናታን አቦት ከጥቂት አመታት በፊት ዩቲዩብ ድረገጽ ላይ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚሰራ አነስተኛ ተሽከርካሪ መመልከታቸውን እና አሰራሩን በሚገባ ለማወቅ አፈላልገው ማጣታቸውን አስታውሰዋል:: ከዚያ በኋላ “ለምን እኔ አልሰራውም” የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰው እንደተያያዙትም ነው ያረጋገጡት::
ጆናታን የመጀመሪያውን ናሙና ሰርተው ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጋቸውን ቁስ፣ ዓይነትና ብዛት ለይተው ንድፉን ወረቀት እና ኮምፒውተር ላይ መስራት መቻላቸውንም አብስረዋል:: የመጀመሪያውን ስራ ለማጠናቀቅ 2300 ሰዓታት ወይም 95 ቀናት ነው የወሰደባቸው::ጆናታን አቦት እና ቡድናቸው ትንሿን “ኤክስካቫተር” በብዛት ለማምረት እና በበርካቶች እጅ ለማስገባት ባካሄዱት የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻም በ70 ቀናት ውስጥ 268 ሺህ ዶላር ማሰባሰባቸው በማጠቃለያነት ለንባብ በቅቷል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም)