በቻይና ሄናን ግዛት ከ47 ሃገራት ከተሰባሰቡ የ“ሻኦሊን ኩንግፉ” ወይም “የማርሻል አርት” ተወዳዳሪዎች የዘጠኝ ዓመቷ ታዳጊ በመተጣጠፍ ብቃቷ እና ባቀረበችው ትርኢት ከምርጦቹ አንዷ ኮከብ ለመሆን መብቃቷን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል፡፡
የ2024 እ.አ.አ የ“ሻኦሊን” ውድድር በቻይና ሄናን ግዛት ነበር የተካሄደው፡፡ በዚሁ የአክሮባት እና ልዩ የአካል ቅልጥፍና በሚከወንበት ሐምሌ 14 ቀን 2024 እ.አ.አ በተካሄደው ውድድር ከ47 ሀገራት የተውጣጡ 144 የ“ሾኦሊን” ከዋኞች ተሳትፈዋል፡፡
የ “ሻኦሊን” ጨዋታ በቻይና ጥንታዊነት ያለው ከ1500 ዓመታት በፊት የነበረ ሲሆን ውድድሩ ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነትን ማጠናከር የሚያስችል ነው ተብሎለታል- በአዘጋጆቹ፡፡
ለውድድሩ የተሳታፊዎች ምርጫን በተመለከተ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ እጩ ተወዳዳሪዎች በየቀጠናው እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ ተመዝግበው 2400ዎቹ በሄናን ለሚካሄደው መመረጣቸው ነው የተብራራው፡፡
በዚህ አህጉር አቀፍ ውድድር በክህሎት ብልጫ አላቸው ተብሎ የታመነባቸው በሄናን – ቀደምት ደቀ መዝሙሮቹ ቤተእምነት “ሻኦሊን ቴምኘል” 20 ሺህ ተሳታፊዎች በርከት ላሉ ቀናት እንደተወዳዳሩ ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡
“የሻኦሊን” ተወዳዳሪዎቹ የየግል ችሎታቸውን በቅደም ተከተል በተሰበሰቡ ተመልካቾች እና ዳኞች ፊት አቅርበዋል፡፡ በሐምሌ ወር የተካሄደው የ2024 ዓመታዊ ትርኢት ባህላዊ ትስስር እና ዓለም አቀፋዊ አንድነት፣ ወንድማማችነት የተንፀባረቀበት እንደነበረም ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ከቻይና ሄናን ግዛት በውድድሩ ላይ የተገኘችው የዘጠኝ ዓመቷ ዛንግ ሲቹዋን ባቀረበችው ትርኢት በአካል ቅልጥፍናዋና ባለመሰልቸት ከአራት ዓመቷ ጀምሮ ባደረገችው ልምምድ በኮከብነት ለመመረጥ መብቃቷን አሰልጣኟ አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም “ሻኦሊን ኩንግፉ” የቻይና ባህላዊ መገለጫ ብቻ ሳይሆን በዓለም 100 ሚሊዬን ከዋኝና ተከታዮች ያሉት መሆኑ ነው በማጠቃለያነት የሰፈረው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም