የአማራ ክልል ምቹ የተፈጥሮ ሃብት እና ለተለያዩ ሰብሎች ምርታማነት ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት የታደለ ክልል ነዉ። ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ምርት እና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ ይቻል ዘንድ ግብአትን ባግባቡ ማቅረብ እና የቀረበውን ግብአትም በተገቢው ሁኔታ መጠቀም ያስፈልጋል።
ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በወቅቱ እና በፍትሐዊ መንገድ ለአርሶ አደሩ ማድረስ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራትም አንዱ የምርት ማሳደጊያ መንገድ በመሆኑ የግብአት ስርጭት እና አቅርቦት ላይ መረባረብ ለቀጣዩ የምርት ዘመን ዋስትና ነዉ።
ግብርና በአገራችን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እና ሽግግር ዉስጥ ያለዉን ሚና በሚፈለገው ልክ መጫዎት ይችል ዘንድ ከፍተኛ ድርሻ ከሚያበረክቱት ግብአቶች መካከልም አንዱ ቴክኖሎጅ ነዉ። ክልላችንም አሁን አሁን ቴክኖሎጅዉን እና አሠራሮችን በመጠቀሙ የምርታማነት ደረጃዉን ማሳደግ ጀምሯል።
በዚህም ከተለመደዉ አሠራር በመዉጣት የተጀመሩ የግብርና አሠራሮችን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ በኩታ ገጠም በማረስ፣ በመስመር በመዝራት፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም፣ አሲዳማ አፈርን በማከም እና የመሳሰሉትን አሠራሮች በማስቀጠል እንዲሁም የተሻሻሉ ቴክኖሎጅን በመጠቀም ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የግብርናዉ ዘርፍ ላገራችን ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት የሚኖረዉን ድርሻ ከፍ ማድረግ ያሻል።
የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያዎች እና ምርጥ ዘሮች የምርታማነት መሠረቶች በመሆናቸዉ ከሰዉ ሰራሽ ማዳበሪያ በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት እንዲመረት እና ይህም የዘወትር ስራ እንዲሆን በማድረግ በኩል ከባለሙያዎች የሚጠበቅ ታላቅ አገራዊ ሃላፊነት ነዉና ይህንኑ ተግባር ለማስተግበር ቀጠሮ አያስፈልገዉም።
ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ለአርሶ አደሮች የማቅረቡ ስራ ወቅቱ የሚጠይቀዉ ተግባር ነዉ።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በመኸር ወቅቱ አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬትን ክልሉ በሚታወቅባቸው ሰብሎች ለመሸፈን እቅዶ እየሠራ ሲሆን ከዚህም 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ በእቅዱ ላይ የሰፈረዉ መረጃ ያመላክታል።
ይህ እቅድ እንዲሳካ ታዲያ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እገዛ በእጅጉ አስፈላጊ ነዉ። አርሶ አደሮች እርሻን በድግግሞሽ በእንዲያርሱ በማበረታታት ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ምርጥ ዘሮችን በስፋት በማቅረብ፣ የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያዎችን በሚፈለገው መጠን በወቅቱ ወደ አርሶ አደሩ እጅ እንዲገቡ በማድረግ፣ የሜካናይዜሽን አስተራረስን በሰፊው ተግባራዊ እንዲሆን በማገዝ፣ አሲዳማ አፈርን በማከም አርሶ አደሩ እንዲጠቀም የባለሙያዎች እገዛ በእጅጉ ያስፈልጋሉ ።
በበጀት ዓመቱ ለሚከናወነው የመኸር እርሻ ሥራ ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ኩንታል ሰዉ ሰራሽ ማዳበሪያ ያስፈልጋል፡፡ እስካሁንም ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ለአርሶ አደሩ የተሰራጨው ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል መሆኑን የግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡
በበጀት ዓመቱ በመኸር ወቅት ይተገበራል ተብሎ የተነደፈው እቅድ እንዲሳካ በዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎችም ሆኑ ሌሎች አካላት የግብርና ግብዓት በወቅቱ እንዲደርስ እና አርሶ አደሩ ፈጥኖ ወደ ዘር እንዲገባ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀዉ ተግባር መሆኑን አውቀው ለተግባራዊነቱ መፍጠን ይኖርባቸዋል!
በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም