ትኩረት ለሰብዓዊ ድጋፍ!

0
97

በያካባቢው የሚከሰቱ  ግጭቶች እና ጦርነቶች እጁን ለሰብአዊ ድጋፍ የሚዘረጋው ያለም ሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር እያደረጉ ነው፡፡ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2019  ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገለት 152 ሚሊዮን ያለም ሕዝብ ኑሮውን ይገፋ የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር  በ2024   ወደ 733 ሚሊዮን አሻቅቧል፡፡ ይህም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ስለመሄዱ ማሳያ ነው፡፡

ግጭት እንዲሁም ጦርነት ወለድ ችግሮች ለኢትዮጵያም ፈተና ሆነዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ዓመት በገጹ ያሰፈረው ጽሑፍ እንደሚጠቁመው በኢትዮጵያ 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ የዕለት ደራሽ ምግብ ይፈልጋል፡፡ ጦርነት፣ ግጭት እና የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ ለሰብዓዊ ተረጂዎች ቁጥር ከፍ ማለት በአብነት በጽሑፉ ላይ የተወሱ ችግር አባባሽ ክስተቶች ናቸው፡፡

የአማራ ክልልም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ከጦርነቶች አንዲሁም ግጭቶች ሊወጣ አልቻለም፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ድርቅ፣ ከፍተኛ ዝናብ፣ በረዶ እና የመሬት መንሸራተትም የክልሉን ምርታማነት በመቀነስ፣ ሰዎች እንዲፈናቀሉ በማድረግ እርዳታን እንዲጠብቁ ምክንያቶች ሆነዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን በቅርቡ ባካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው ክልሉ ባጋጠመው የሰላም እጦት እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት እጆቻቸውን ለዕለት ደራሽ እርዳታ የዘረጉ ወገኖችን የመደገፍ ሥራው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

እነዚህን ወገኖች ከመደገፍ በመለስም ከእርዳታ ጠባቂነት ማውጣት እና ክልሉ ይታወቅበት ወደ ነበረው ከፍተኛ የማምረት እንቅስቃሴ እንዲገባ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚያሻም ተጠቁሟል፡፡ “ማን ምን ኃላፊነት ይወጣ?” ለሚለው ጥያቄም ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ በዚሁ ጊዜ  ተጠይቋል፡፡

በጉባኤው እንደተጠቀሰው በሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ከሚገኙት የአማራ ክልል ዞኖች የዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አንዱ ነው፡፡ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ምርታማ የሆኑ ደጋማ እና ወይና ደጋማ የአየር ንብረት ያላቸው አካባቢዎች በጎርፍ፣ በበረዶ እና በመሬት መንሸራተት አደጋ መጎዳታቸው ተወስቷል፡፡ በዚህ የተነሳም በብሄረሰብ አስተዳደሩ 242 ሺህ ሕዝብ ለዕለት ደራሽ ምግብ እጦት መዳረጉ ተገልጿል፡፡

ችግሩን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ  ስለመሆኑ በጉባኤው ተወስቷል፡፡ ሆኖም ለተረጂዎች እየተደረገ  ያለው ድጋፍ ከተረጂው ቁጥር  እና እየፈጠረ ካለው ተጽእኖ አኳያ  በቂ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡ ስለሆነም የክልሉ መንግሥት በተለይም  ዝናብ አጠር አካባቢዎችን በመለየት እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም በተለያዩ ምክንያቶች ሊያጋጥም በሚችል ችግር የተነሳ ሰብአዊ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን  በራስ አቅም ለመደገፍ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡    ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት ፍሬያማ ይሆን ዘንድ ከመንግሥት ጎን መቆም ያስፈልጋል፡፡

ለተረጅዎች ለመድረስ ከሚደረገው ርብርብ ባሻገር  ክልሉ ራሱን ከመመገብ አልፎ እንደ ሀገር የሚጠበቅበትን ይወጣ ዘንድ በክረምት ወቅት ከማምረት በተጨማሪ ለበጋ መስኖ ልማት ትኩረት መስጠት እንዲሁም ያመራረት ዘዴን ማዘመን ይገባል፡፡ የአመራረት ዘዴውን ማዘመን (የኩታ ገጠም አስተራረስን ማስፋት፣ የእርሻ ትራክተር እና የሰብል መሰብሰቢያ ኮምባይነሮችን ቁጥር ማሳደግ፣ የግብርና ግብዓትን በበቂ መጠን እና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ፣ የገበያ ትስስር መፍጠር እና ሌሎችንም የምርት ማሳደጊያ አሠራሮችን እንደ መውጫ መጠቀም ይገባል፡፡

በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here