የግብርናዉ ዘርፍ የኢኮኖሚ መሰረት በመሆኑ ዘርፉን በማዘመን እና ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄደዉን ህዝብ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የዉዴታ ግዴታ ነዉ።
የግብርናዉ ዘርፍ ለአጠቃላይ ሐገራዊ ኢኮኖሚዉ እና ለሰዉ ልጆች በሙሉ የኑሮ መሰረትም ነዉ። እናም የግብርናዉን ዘርፍ ማጠናከር ዜጎች በምግብ ራሳቸዉን እንዲችሉ ፣አግሮ ኢንዱስትሪዎችን መመገብ እንዲችል እና የኤክስፖርት ምርቶችን በጥራት እና በብቃት ለማምረት ያግዛል፡፡
የአግሮ ኢንዱስትሪዉን ፍላጎት ለማሟላት እንዲሁም ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና በዉጭ ገበያ ተፈላጊ ምርቶችን በማምረት የዉጭ ምንዛሬን ለማምጣት ዘርፉ ጉልህ እና አይተኬ ድርሻ አለዉ።
የግብርናዉ ዘርፍ ጠቀሜታዉ የላቀ መሆኑ እና ጉልህ ድርሻ እንዳለዉ የተረጋገጠ ቢሆንም ዘርፉ በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ ይገኛል፡፡
እነዚህ ተግዳሮቶችም ዘርፉ በሚጠበቅበት መጠን እንዲሁም በሚፈለገዉ ጥራት ልክ እንዳያመርት ወይም ምርት እና ምርታማነቱ እንዳያድግ እንቅፋት ፈጥረውበታል።
በመሆኑም እነዚህን ችግሮች በመለየት እና በቅደም ተከተል በማስቀመጥ ለችግሮቹ ዘለቄታዊ መፍትሄ መስጠት እና አሰራርን ማዘመን ተገቢ እንደሆነ ያደጉ ሃገራት ተሞክሮ ያሳያል።
ግብርናዉ ሲዘምን ህዝቡን እና ሃገርን ከድህነት ለማላቀቅ የሚኖረዉ ሚና ከፍተኛ ስለሆነ ለግብርናዉ ዘርፍ ስኬታማነት በዘርፉ ያሉ ተመራማሪዎች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚና ጉልህ በመሆኑ ትብብራቸዉ ማጠናከር እና ቅንጅታዊ አሰራርን ማስቀጠል ቁልፍ ተግባር ነዉ።
ከዚህ እውነታ በመነሳትም የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ ዉይይት ከሰሞኑ በባህር ዳር ከተማ አካሂዷል። የክልሉ ግብርና ቢሮ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመለየት እና ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት ምርት እና ምርታማነትን ለማረጋገጥ ያስችሉኛል ያላቸዉን መፍትሄዎች አስቀምጧል።
እርግጥ የግብርና ችግሮች ብዙ ቢሆኑም ሁሉንም ችግሮች በአንዴ መፍታት እና መፍትሄ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ይሆናል። ቢሆንም በግብርናዉ ዘርፍ በጣም አንገብጋቢ እና አስቸካይ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸዉን በመለየት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ይታመናል።
በግብርናዉ ዘርፍ ከተደቀኑ ችግሮች መካከልም የቅድሚ ቅድሚያ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸዉን መለየትም ችግሩን ለመፍታት አንድ እርምጃ ነዉና ከሰሞኑ በተካሄደዉ ምክክር ላይ ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል ቅድሚያ መፍትሄ እንዲፈለግለት የተነሳዉም የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀምን በአዲስ ማሻሻል እና የምርጥ ዘር ማምረት እና አቅርቦትን ካለፉት ዓመታት በተሻለ ደረጃ ተደራሽ ማድረግ መሆናቸዉን ተጠቅሷል።
የክልሉን ምርታማነት ለማሳደግ በየወቅቱ መመካከር፣ አሰራሮችን ማሳደግ፣ የምርምር ዉጤቶችን መፈተሽ እና ተግባር ላይ ማዋል ከተመራማሪዎች የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ተቋም አዲስ ምክረ ሃሳብን ለምክክር መድረኩ አቅርቧል፡፡
የቀረበዉ ምክረ ሃሳብም የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ምክረ ሃሳብ እንዲሻሻል የሚል ሲሆን የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ማሻሻያ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትም ተብራርቷል፡፡ በአዲስ የተሻሻለዉ የአፈር ማዳበሪያ የያዘዉ ንጥረ ነገር አፈሩ በተፈጥሮዉ ከያዘዉ ንጥረ ነገር ጋር ተመሳሳይነት ያለዉና ተጨማሪ ባለመፈለጉ እንደሆነ በአማራ ክልል ግብርና ምርምር የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ዓለማሁ አሰፋ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል።
የምርምር ማእከሉ እንዳረጋገጠዉ አዲሱ የአፈር ማዳበሪ ዚንክ፣ቦሮን እና ፖታሽየም የገባባቸዉ ቅይጥ ማዳበሪያወች በምርምር ሲረጋገጡ ምርታማነትን በመጨመር ረገድ አስተዋጽኦ አልነበራቸዉም፡፡ ስለሆነም በምርታማነት ላይ የጎላ ተጽእኖ በማይፈጥሩ ማዳበሪያዎች ዙሪያ አርሶ አደሩ ዋጋ እንዳይከፍል እና ቀድሞ ወደ ነበረዉ የአፈር ማዳበሪ እንዲመለስ አሳስበዋል፡፡
ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ከሚያግዙት መካከልም የምርጥ ዘር አቅርቦት እና ስርጭትን ማሻሻል አንዱ በመሆኑ በዋና ዋና ሰብሎች በዘር ራስን ለመቻል እና ለአግሮ ኢኮሎጂዉ ተስማሚ የሆኑ ዝርዎችን ለማምረት ከፍተኛ ስራን ይፈልጋል።
በመሆኑም በምርምር የተገኙ አሰራሮችን ትኩረት በመስጠት፣ አዳዲስ አሰራሮችን እና ቴክኖሎጅወችን ተግባራዊ በማድረግ የክልሉን የማምረት አቅም ከዓመት ዓመት በማሻሻል በምግብ ራስን ለመቻል የሚያስችሉ ሰብሎችን በማምረት፣ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን በመከተል የግብርና ምርትን የሚጠቀሙ አግሮ ኢንዱስትሪዎች በስፋት በመገንባት ለዉጤታማ ስራዎች በር ከፋች በመሆናቸዉ ልንተገብራቸዉ ይገባል።
በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም