ትኩረት የሚያሻዉ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ

0
234

ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ 60 በመቶው በደን የተሸፈነ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። ኢትዮጵያዊያን ከረጅም ዓመታት በፊት ጀምሮ ዛፍ የመትከል ልምድ እንደነበራቸው በደን ላይ የጻፉ ምሁራን ይጠቅሳሉ። የመካከለኛው ዘመን ታሪክ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ዳዊት (ከ1375-1404) የደን ጭፍጨፋ እና የእንስሳትን አደን ለመከላከል በሀገሪቱ ሰባት የአካባቢ ጥበቃ ጣቢያዎች አቋቁመው እንደነበር በዜና መዋዕላቸው ሰፍሯል።

ልጃቸው አጼ ዘርዓ ያዕቆብም ኢትዮጵያን የደን ካባ ለማልበስ “የንጉሥ የደን ክልል” በሚል የደን ጥበቃን አጠናክረው በማስቀጠል በዘመናቸው ጥረት እንዳደረጉ ታሪክ ያወሳቸዋል። አጼ ልብነ ድንግል ደግሞ ችግኞችን አፍልተው  የማስተከል ሥራ ስለመጀመራቸው ይወሳል።

ሌላው በደን ልማት ታሪካቸው የሚነሱት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ናቸው። ንጉሡ የአጼ ዘርዓ ያዕቆብን “የንጉሥ ደን ጥብቅ ስፍራ” ጽንሰ ሃሳብን አጠናክረዋል። በዘመናቸው የደን የሕግ ማዕቀፍ አውጥተዋል፤ ለዘርፉ አማካሪም መድበዋል።  ዛሬ ሀገሪቷን የተቆጣጠረው አውስትራሊያዊው ባሕር ዛፍ (ኢካሊፕተስ) በዳግማዊ ምኒልክ የመጣ መሆኑን ልብ ይሏል።

ዳግማዊ ምኒልክ በመንግሥት ከሚለማው ደን በተጨማሪ ዜጎች በባለቤትነት በደን ልማት እንዲሳተፉም አዋጅ አውጥተው እንደነበር የመዕዋለ ዜና ዘጋቢያቸው ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ ወልደ አረጋይ ፅፈዋል።  የደን ሕግ አውጥቶ ከመጠበቅ ባለፈም በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ችግኝ በመትከል እንክብካቤ ይደረግ ነበር።

በደርግ ዘመን የተከሰተው ድርቅ እና ረሀብ ደግሞ በኢትዮጰያ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ምክንያት ሆኗል። በደርግ  መንግሥት ችግኝ ማበረታቻ የሚያሰጥ ተግባር ሆኖ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በውቅቱ የተደረገው ማበረታቻ ፍሬ አፍርቷል። የደርግ ዘመን አረንጓዴ አሻራዎች ዛሬም ድረስ አልጠፉም፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ ግን በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የደን ውድመት እንደደረሰ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በዚህ ሁኔታ የዘለቀው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ  አሁን ኢትዮጵያን በማስተዳደር ላይ ካሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት  ደርሷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም  አረንጓዴ ኢኮኖሚን፣ የአካባቢ ጥበቃን እና የተፈጥሮ ሀብት መንከባከብን ትልቅ ትኩረት ሰጥተውታል።

በ2011 የክረምት ወቅት ጀምሮ በየዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተተገበረ ይገኛል። በመላ ሀገሪቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እያሳተፈ መርሃ ግብሩ እንደቀጠለ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) የመጀመሪያው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በይፋ ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ /በ2012 ዓ.ም/ የዓለም አካባቢ ቀን በተከበረበት ዕለት “ብዝኃ ሕይወትን መጠበቅና መከባከብ ቅንጦት ሳይሆን ህልውና መሆኑን አይተናል” በማለት የአካባቢ ደህንነት የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ ሌላው ክፍላተ ዓለም ሁሉ ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መራቆት ችግር ተጋርጦባታል፤ ለጎርፍ አደጋ፣ ለአፈር መሸርሸር፣ ለደን መመናመንና ለብዝኃ ሕይወት ኪሳራ መዳረጓን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው ይታወሳል።

በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ሺህ ችግኞችን እንደሚተክሉ ቃል በመግባት ሕዝቡን ለዘመቻው አነሳሱ፡፡ አንድ ሰው 40 ችግኞችን እንዲተክል ተሰልቶ ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ዘመቻ ይፋ ሆነ። ከዚህ ውስጥም በአንድ ጀምበር ከ200 ሚሊዮን የመትከል ዕቅድ ግቡን አልፎ በቀን ከ354 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው ተበሰረ። ይህም በአንድ ጀምበር 50 ሚሊዮን ችግኞች ከተከለችው ህንድ በኋላ የዓለምን ክብረ ወሰን እንደያዘ  ተነግሯል።

መንግሥታት ቢለዋወጡም  ዛሬም ድረስ ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ የዘለቀው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ተግባር ክሎችም እንደ ሀገር የድርሻቸውን  ሲያከናውኑ ቆይተዋል – አሁንም እያከናወኑ ናቸው፡፡

የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ለሠብል፣ ለመስኖ፣ ለእንስሳት፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ዋስትና በጊዜ ሂደት ሁሉም እየተገነዘበው መጥቷል። ለዚህ ማሳያም በየዓመቱ የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠቃሽ ነው።

በዚህ ሁኔታ በየዓመቱ ጥር መባቻ  የሚበሰረው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ በአማራ ክልል ሳይቆራረጥ ቀጥሏል፡፡

የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራም በርካታ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቶ ጥር ወር 2017 ዓ.ም ይጀመራል፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ  ምክትል ኃላፊ አቶ  ደረጄ ማንደፍሮ ቅድመ ዝግጅቶችን እና ሊሠሩ የታቀዱትን አስመልክቶ ለአሚኮ በሰጡት መረጃ  በተያዘው የበጋ ወቅት በሚከናወን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ለ280 ሺህ 700 ቀያሽ አርሶ አደሮች ስልጠና፣ 212 ሺህ 999 ሄክታር መሬት በአዲስ የተራቆተ እና የተራራ መሬት ማልማት፣ 153 ሺህ 650 ሄክታር በነባር አፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ደረጃ ማሳደግ፣ የክልሉን የደን ሽፋን አሁን ካለበት 16 ነጥብ 3 በመቶ በዓመቱ አንድ በመቶ ማሳደግ፣ በሥነ ሕይወታዊ ዘዴ 384 ሺህ 504 ሄክታር መሬት በማልማት የአፈር ለምነትን ማሻሻል እና 12 ሺህ 809 ሄክታር ውኃማ እና በየብስ የተሸፈነ መሬት ከወራሪ እና አደገኛ አረም ነጻ የማድረግ ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ከሰሞኑ የተፈጥሮ ሀብር ጥበቃን አስመልክቶ በኮምቦልቻ  ከተማ በተሰጠ ሥልጠና በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተሠራ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት መመዝገቡን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ በክልሉ በተፈጥሮ ሀብት ልማት የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠልም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ካሁን በፊት በተከናወነ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ የሰብል ምርታማነት መጨመሩን፣ የአፈር ለምነት መጠበቁን፣ የእንሰሳት መኖ በቀላሉ መገኘቱን፣ ውኃ እርጥበት የመያዝ አቅሙ እንዲጨምር መደረጉን እና የደን ሽፋን መጨመሩን ኃላፊው ገልጸዋል። ይህን ውጤት አጠናክሮ ለመቀጠል  ክፍተቶችን ለማስተካከልና ጥንካሬውን ለማስቀጠል በየደረጃው ላሉ ለዘርፉ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን አክለዋል፡፡

የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ለክልሉ የህልውና ጉዳይ ጭምር መሆኑን በመረዳት ህብረተሰቡና ሙያተኛው አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ በቁጭት ተግባሩን ሊያጠናክር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የሥነ ሕይወት ሳይንቲስቱ ፕሮፌሰር ለገሰ ነጋሽ  ለቢቢሲ እንደደተናገሩት በየዓመቱ የሚከናወን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ መሠረቷ በተለይም በዝናብ ላይ የተመሠረተ ግብርና ላላት ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ተራሮች ደን መልበስ አለባቸው። ደኖች ዝናብ ይስባሉ፣ ውኃ ወደ ከርሰ ምድር እንዲሰርግ ያደርጋሉ። ደኖች ለትነት መቀነሻ መሣሪያም ናቸው።

ደን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ፋይዳው ድንበር ዘለል  መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፤  የአካባቢ ደን ልማትና አየር ንብረት ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጀት /ተመድ/ አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል። ከብዙ ዐሥርት ዓመታት በፊት ጀምሮ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሳይንሳዊ ጥናቶች እየቀረቡ ውይይቶች መደረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ሳይንቲስቶችም ፕላኔታችን አደጋ ላይ በመውደቋ የሀገራት መግሥታት መፍትሔ እንዲያበጁ፣ በደን ልማትና አካባቢ ጥበቃም እንዲያተኩሩ ጥሪ አቅርበዋል።።

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here