ትኩረት የተነፈገዉ ሊግ

0
162

የዘንድሮው የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ህዳር 16/ 2016 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል። የመክፈቻ ሥነ ስርዓቱ ልክ እንደ ባለፉት አራት ዓመታት ቀዝቀዝ ያለ በመሆኑ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ቅር አሰኝቷል።በዚህ መድረክም ዘንድሮ ከባለፈው ዓመት አንድ ክለብ ተጨምሮ 14 ክለቦች እየተፎካከሩ ይገኛሉ። ከወትሮው በተለየ ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ በሚጠበቀው በአዲሱ የውድድር ዓመት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ የሚያነሳው ክለብ በአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ላይ ሀገራችንን የሚወክል ይሆናል።
ሊጉን መቋቋም ያልቻሉት እና ጉልበታቸው የዛለ ሁለት ክለቦች ደግሞ ወደ ሁለተኛው የሊግ እርከን የሚወርዱ ይሆናል።ባሳለፍነው ዓመት አንድ ክለብ ብቻ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን እንደወረደ ይታወቃል:: በወረደው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ምትክ ሲዳማ ቡና እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ፕሪሚየር ሊጉን በመቀላቀል የውድድር ዓመቱን ጀምረዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከተጀመረ ብዙ ዓመታት አላስቆጠረም። ገና የ12 ዓመታት እድሜ ብቻ ነው ያለው። በዚህ አጭር ጊዜያት ምንም እንኳን በአፍሪካ መድረክ ውጤታማ ባይሆኑም ጠንካራ ክለቦች ግን ተፈጥረዋል።የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ጥሩ ፉክክር የሚታይበት፣ ታዳጊዎች ዕድል የሚያገኙበት እና ብሄራዊ ቡድኑን የሚወክሉ ተጫዋቾች የሚወጡበት ቢሆንም ሊጉ በብዙ ችግሮች የተተበተበ ነው። አሰልጣኞቹ፣ ተጫዋቾች፣ እና ክለቦች አወዳዳሪው አካል ትኩረት ነፍጎታል በሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ እና አቤቱታዎችን ሲያቀርቡ ይደመጣል።ነገር ግን ዘንድሮ ፕሪሚየር ሊጉ ሲጀምር አዳዲስ መልካም ነገሮችም ታይተዋል::
በየጨዋታው የተሻለ እና ድንቅ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ተጫዋቾችን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በራሱ ባለሙያ በማስመረጥ ዘንድሮ መሸለም ጀምሯል። ሽልማቱን ፍትሐዊ ለማድረግ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ እየሰራ ያለው ሥራ መልካም እና የሚበረታታ ተግባር ነው።
በየዓመቱ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሲጀመር እንደ ችግር ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል የመወዳደሪያ ቦታ እና የመለማመጃ ቦታ አንዱ ነው። ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ውድድር አርቴፊሻል ሣር በተነጠፈበት የሀዋሳ ስቴዲየም ይደረጋል ቢባልም ስቴዲየሙ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግን እያስተናገደ በመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል። ይህ መሆኑም በክለቦቹ ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል። ከልምምድ ቦታ ጋር በተያያዘ በቂ የእግር ኳስ ክለቦች የመለማመጃ ቦታ ከሌለባቸው ከተሞች መካከል ሀዋሳ ከተማ አንዷ መሆኗን ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ ክፍል ጋር ቆይታ ያደረገው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ክለብ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ይናገራል።
በከተማዋ ለልምምድ የሚሆን ሜዳ በክፍያ እንኳ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ጭምር ነው አሰልጣኙ የተናገሩት። ክለቦቹ በቂ እና ጥራት ያለው የልምምድ ቦታ ካላገኙ ተጫዋቾች በቀላሉ ለጉዳት ይጋለጣሉ፣ በታክቲክም ቢሆን አሰልጣኙ የሚፈልገውን እና የሚያዝዘውን ፣ሜዳ ላይ ተግባራዊ ለማድረግም እክል ይፈጥራል።
አሰልጣኝ ብርሃኑ ሀዋሳ ከተማ ልክ እንደ ባህር ዳር ከተማ በተጫዋቾች ፣በአሰልጣኞች እና በአጠቃላይ በሁሉም ክለቦች የምትወደድ ከተማ ብትሆንም፣ ይህ ችግር ግን አሁንም አልተቀረፈም ይላሉ። ባለፉት ዓመታት የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከተካሄደባቸው እና የሜዳ ችግር ከሌለባቸው ከተሞች መካከል ባህር ዳር ከተማ አንዷ እንደሆነች አሰልጣኙ ጠቅሰዋል። ሌላው በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከሚነሱ ችግሮች መካከል የዳኝነት ጉዳይም ይገኝበታል።
የዳኞቹ የብቃት ማነስ ከዚህ በፊት በነበሩ ውድድሮች አልፎ አልፎ ይነሳ እንደነበር ይታወሳል። የዳኞቹ ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ በክለቦቹ ውጤት ላይ በቀጥታ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደሩ በተጨማሪ የፉክክሩን ሂደትም ያደበዝዘዋል ። ታዲያ ይህ እንዳይሆን ደግሞ የአቅም ማነስ የሚታይባቸው ዳኞችን የማብቃቱ ሥራ ላይ የሚመለከተው አካል በደንብ ሊያስብበት ይገባል! የብዙዎቹ አስተያየት ነው።
የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሀገሪቱ ከፍተኛው የሊግ እርከን ቢሆንም በቂ የሚዲያ ሽፋን እያገኘ እንዳልሆነም አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ይናገራል። እንደ አሰልጣኙ አስተያየት የሀገራችን ሚዲያዎች የሴቶችን እግር ኳስ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ አለመሆኑንም ጠቁመዋል።ይህም ሊጉ በተፈለገው ልክ ለውጥ እንዳያመጣ አድርጎታል::
የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ በቀጥታ የቴሌቪዥን መስኮት በዲ ኤስ ቲቪ (DSTV) መተላለፍ ከጀመረ ዘንድሮ አራተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። ይህ የቀጥታ ስርጭትም ለእግር ኳሱ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከፊፋ ፕላስ(FIFA PLUS) ጋር በመተባበር ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በዩቲዩብ(YOUTUBE) የቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ አቅዶ ሳይሳካ የውድድር ዓመቱ መጠናቀቁ አይዘነጋም።
በዚህ ዓመት ግን የወንዶች ከፍተኛ ሊግ በቀጥታ ስርጭት እየተላለፈ ሲሆን የሴቶቹ ፕሪሚየር ሊግ ግን ሳይጀመር 3ኛ ሳምንት መርሀግብር ተከናውኗል።ባሳለፍነው ዓመት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አልፎ አልፎም ቢሆን በማህበራዊ የትሥሥር ገጽ ጨዋታዎችን ሲያስተላልፍ እንደ ነበረ አይዘነጋም።
ስቴዲየም ገብቶ የሴቶችን ጨዋታ የሚመለከተው የደጋፊ ቁጥር በባሕር ዳር እና ሀዋሳ የተሻላ ቢሆንም በአጠቃላይ ግን አነስተኛ መሆኑ አያጠያይቅም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት አብዛኞቹ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችም ያለ ተመልካች “በዝግ ስቴዲየም” እስኪመስል ያለ ተመልካች ተከናውነዋል። የሴቶች እግር ኳስ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ሴቶችን መበረታታት እና መደገፍ ይኖርባቸዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፣ ክለቦችም ብዙ ሥራ መስራት ይጠይቃቸዋል።
ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ አርባምንጭ ከተማ፣ ጠንካራ ተፎካካሪ ክለቦች እንደነበሩ አይዘነጋም። እነዚህ ክለቦች ዘንድሮም ተጠናክረው ለመምጣት የክረምቱን የዝውውር ወቅት ተጠቅመው በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ እንደነበር ይታወሳል። ክለቦቹ ከወዲሁ መልካም የሚባል አጀማመርን እያደረጉም ይገኛሉ::
በተመሳሳይ መቻልም በዚህ ዓመት የሊጉ ድምቀት ይሆናል ተብሎ በብዙዎቹ ዘንድ ትልቅ ግምትን ያገኝ ክለብ ነው። የውድድር ዓመቱን በዋንጫ በመታጀብ ያጠናቅቃል ተብሎ ግምትም ተሰጥቶታል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግን ዘንድሮም ዋንጫውን ያነሳሉ ተብለው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ክለቦች መካከል ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል።ንግድ ባንክ በ2015 ዓ.ም አስደናቂ የውድድር ዓመት በማሳለፍ ሊጉ ሳይጠናቀቅ ስድስተኛ የሊግ ዋንጫውን በማንሳት ከደደቢት ጋር እኩል በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ስሙን አስፍሯል።ክለቡ በሁሉም የሜዳ ክፍል ጥሩ እግር ኳስን የሚጫወቱ እና ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች መያዙ ትልቅ ግምት እንዲሰጠው አድርጎታል።
ክለቦቹ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ መድረክም ለመሳተፍ እና ስኬታማ ለመሆን ግን ከወዲሁ ብዙ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።
ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅም የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከሚደረገው ፉክክር ባልተናነሰ ዘንድሮ ከባድ እንደሚሆን ይጠበቃል።ባሳለፍነው ዓመት ከመውረድ ለጥቂት የተረፉት ይርጋ ጨፌ ቡና እና አዳማ ከተማም ዘንድሮ ተጠናክረው መጥተዋል። ባሳለፍነው ዓመት ደካማ አቋም ያሳየው ቦሌ ክፍለ ከተማ ጥሩ አጀማመር እያደረገ ይገኛል:: አዲስ አዳጊዎቹ ሲዳማ ቡና እና ሀምበሪቾ ዱራሜም በሊጉ ለመቆየት ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የአምናው መሀል ሰፋሪ ክለብ ልደታ ክፍለ ከተማ ግን ዘንደሮ ከወዲሁ ሊጉ የከበደው ይመስላል:: ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋንጫውን ባነሳበት የ2015 ዓ.ም የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በአጠቃላይ ክለቦቹ ተቀራራቢ ነጥብ ይዘው ማጠናቀቃቸው ግን አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን እሳከሁን ሦስት ክለቦች ብቻ አሳክተዋል:: ደደቢት ፣ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ፤ ደደቢት እና ንግድ ባንክ ስድስት ጊዜ በማሳካት ባለክብረ ወሰን ናቸው:: ዘንድሮስ የንግድ ባንክን ኃያልነት በመግታት አዲስ ሻምፒዮን ክለብ ይኖር ይሆን? የሚለው አጓጊ ሆኗል:: ፕሪሚየረ ሊጉ ዘንድሮ ምን ዓይነት መልክ እንደሚኖረውም አብረን የምናየው ይሆናል::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ታኀሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here