ጉበት በሰው ልጅ አካል ውስጥ በትልቅነቱ ከቆዳ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሰዎች በጉበት ህመም እየተሰቃዩ እና አለፍ ሲልም ለሞት እየተዳረጉ ነው፡፡
በጥበበ ጊዮን ሆስፒታል እና በእያስታ ልዩ የህክምና ማዕከል የውስጥ ደዌ እና የአንጀት ፣የጨጓራ እና የጉበት ሰብ ስፔሻሊስት ዶ/ር ክብረቴ ወልዴ እንዳሉት ጉበት በርካታ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ከተግባራቱ መካከልም በአፋችን የምንወስደው ማንኛውም ነገር ወደ አንጀት ከገባ በኋላ ለምግብነትም ሆነ ለመጣራት ወደ ጉበት ነው የሚሄደው፡፡ ማንኛውም በሰውነታችን ውስጥ የገቡ መርዛማ የሆኑ (መድሃኒቶች) ነገሮችንም ያስወግዳል፡፡ እንዲሁም ፕሮቲን እና የደም መርጋት እንዳይከሰት የተለያዩ ሆርሞኖችን ያመርታል፡፡
በየአራት ወሩ በአዲስ የሚተካው ደም /ሲያረጅ/ የሚወገደው በጉበት ነው፡፡ ጉበት ሌሎች ጥቃቅን ሥራዎችንም እንደሚያከናውን ነው ዶ/ር ክብረቴ የተናገሩት፡፡
ጉበት በተለምዶ “ገራገር” ይባላል፤ ይህን ስያሜ ሊያገኝ የቻለው ብዙ ጉዳት ቢደርስበትም መልሶ መለምለም (ሪጀኔሬት) ስለሚችል እንደሆነ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም የጉበት ንቅለ ተከላ ሲደረግ ከጤነኛው ክፍል ጥቂት ተቆርጦ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡ ይህ የሚደረገውም ከእንደገና ስለሚያድግ ወይም ስለሚለመልም ነው፡፡
እንደ ዶ/ር ክብረቴ ሙያዊ ማብራሪያ ጉበት ሲጎዳ ምልክት ሳያሳይ ለብዙ ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ በዋነኛነት ያሚያጠቃው ሂፓታይተስ የሚባለው የጉበት ቫይረስ ነው፡፡ ሂፓታይተስ የጉበት ሴል ቁስለት ማለት እንደሆነ የጠቆሙት የህክምና ባለሙያው አምስት አይነት የጉበት ቫይረሶች እንዳሉም ነግረውናል፡፡ ሄፓታይተስ ኤ፣ቢ፣ሲ፣ዲ፣እና ኢ ተብለው ይጠራሉ፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ጉዳት ብሎም ወደ ጉበት ካንሠር የሚቀየሩት ሄፓታይተስ ቢ እና ሲ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሂፓታይተስ ዲ እና ኢ ግን ያልተለመዱ እና አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ናቸው፡፡
ጉበት በመድሃኒቶች ዕክል ሊፈጠርበት እንደሚችል የጠቆሙት ዶ/ር ክብረቴ በተለይም “ወፍ” በሚል የባህል መድሃኒት የሚወስዱ ሰዎች ጉበታቸው ሊጎዳ እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡
ከፍተኛ ጉዳት በማስከተል ለሞት የሚዳርጉት ሂፓታይተስ ቢ እና ሲ የጉበት ቫይረሶች ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋሉ፡፡ መተላለፊያ መንገዶችም ስለታማ ቁሳቁሶችን በጋራ በመጠቀም፣ ልቅ በሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት፣ ከእናት ወደ ልጅ በወሊድ ጊዜ ናቸው፡፡ በንቅለ ተከላ ጊዜም ሳይመረመር የሚሰጥ ጉበት ቫይረሶቹን ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡
ሄፓታይተስ ኤ ደግሞ ከንጽህና ጉድለት የሚመጣ ሲሆን በምንመገባቸው ምግቦች እና መጠጦች አማካኝነት ቫይረሱ ወደ ሰውነት ሊገባ ይችላል፡፡ እንደ ዶ/ር ክብረቴ ማብራሪያ ሄፓታይተስ ኤ ብዙውን ጊዜ በልጆች ላይ ሲከሰት ሄፓታይተስ ኢ ደግሞ በነፍሰጡሮች ላይ ይከሰታል፡፡
ሄፓታይተስ ሲ በጊዜ ህክምና ከተደረገ ሊድን ይችላል፡፡ ይሁንና ምልክቶቹን ቀለል አድርጎ በማየት በፍጥነት ወደ ህክምና ቦታ ስለማይመጡ ለከፍተኛ ጉዳት እንደሚዳርግ ገልጸዋል፡፡ ሄፓታይተስ ቢ ግን ፈጽሞ አይድንም፡፡ ይሁንና ከሁለት ዓመት በላይ መድሃኒቶችን ሳያቋርጡ በመውሰድ በደም ውስጥ የሚገኘውን የቫይረሱን ቁጥር (viral laod) መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
በእኛ ሀገር ሁኔታ የሄፓታይተስ ቢ ቫይረስ ከአንድ መቶ ሰዎች መካከል በ10 ሰዎች ውስጥ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዶ/ር ክብረቴ ይህ አሃዝ ከፍተኛ በመሆኑ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
ሁሉም አይነት የጉበት ቫይረሶች ትኩሳት፣ የድካም ስሜት ፣ማቅለሽለሽ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ በቀኝ በኩል የሆድ ህመም፣ የሰገራ መጥቆር፣ የሆድ መነፋት፣ የሰውነት እብጠት ፣የማሰብ አቅም መቀነስ፣ የእንቅልፍ ሰዓት መዛባት… ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡ ከፍተኛ የጉዳት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ዐይን ቢጫ መሆን፣ ደም ማስታወክ እና የሰውነት እብጠት ብሎም ካንሠር ያመጣሉ፡፡
ዶ/ር ክብረቴ እንዳሉት ሰዎች እነዚህ የህመም ምልክቶች ሲያጋጥሟቸው “ወፍ ዞረችኝ” በማለት ወደ ባህላዊ ህክምና ይሄዳሉ፡፡ የሚሰጣቸው ባህላዊ መድኃኒትም የባሰ ጉበታቸው ላይ ጉዳት ሊያደርስባቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ “ወፍ የሚባል በሽታ የለም፤ ሳይንሱ አላረጋገጠውም፤ ስለዚህ ምልክቶቹን ካያችሁ ወደ ሕክምና ተቋማት መምጣት አስፈላጊ ነው!” በማለትም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
የጉበት ቫይረስ በሰውነት ውስጥ መኖር አለመኖሩን እና አይነቱን በደም ምርመራ ማወቅ እንደሚቻልም ባለሙያው አስታውቀዋል፡፡ ቫይረሱ በደም ውስጥ እንዳለ ከተረጋገጠ ጉበት ምን ያህል ተጎድቷል የሚለውን ለማወቅ ደግሞ የአልትራሳውንድ እና የሲቲስካን ምርመራዎች እንደሚታዘዙ ነው ባለሙያው ያብራሩት፡፡
ሄፓታይተስ ቢ የመከላከያ ክትባት ሲኖረው ሄፓታይተስ ሲን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ግን እስካሁን አልተገኘም፡፡ ሄፓታይተስ የተገኘበት ሰው የምግብ ፍላጎቱ ስለሚቀንስ እንደምንም ብሎ በደንብ መውሰድ አለበት፡፡ በኛ ሀገር ሁኔታ ታማሚዎች የሚመጡት ዘግይተው በመሆኑ ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት፤ ለሌላ አካሉ ትኩረት የሚሰጠውን ያህል ለጉበቱም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በየጊዜው ምርመራ ማድረግ እንዳለበት መክረዋል፡፡
በተለይም ሄፓታይተስ ሲ ምልክት ሳይኖርው ለ20 እና ለ30 ዓመታት ሊቆይ ስለሚችል በጊዜ መመርመር ከከፍተኛ ስቃይ እና ሞት ይታደጋል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የጉበት ቫይረስን ለመከላከል ልቅ ከሆነ የግብረስጋ ግንኙነት መታቀብ፣ የአልኮል መጠጥን እና ሲጋራ ማጨስ ማቆም፣ በሀኪም ካልታገዘ በቀር ማንኛውንም አይነት መድኃኒት ከመውሰድ መቆጠብ እንደሚገባ ባለሙያው መክረዋል፡፡ የባህል መድኃኒቶችን ከመውሰድ መቆጠብ፣ እንደ ጠባሳ/ሲርሆሲስ/ እና የጉበት ጮማ መኖራቸውን ለማረጋገጥ በየጊዜው ክትትል ማድረግ፣ከታማሚው ጋር በጋራ የሚኖሩ ሰዎች ካሉ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን ለማረጋገጥ የደም ምርመራ ማድረግ እንዲሁም ክትባት መውሰድ እና ህክምና ጀምረው ከሆነ ደግሞ በሃኪም የታዘዙ መድሃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፣ በተጨማሪም ያለ ሀኪም ትእዛዝ መድሃኒቶችን አለመውሰድ እንደሚገባ ዶ/ር ክብረቴ ተናግረዋል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም