ትውልዱን የማዳን ሥራ መሠራት እንዳለበት ተገለፀ

0
148

በሀገራችን ባህል ቋንቋ እና ተግባቦት ላይ በመመሥረት ትውልዱን ከመገናኛ ብዙሃን እና ማኅበራዊ ሚድያ ተፅእኖ መታደግ እንደሚገባ ተገለፀ።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ 10ኛውን ዓመታዊ ሀገር አቀፍ ዐውደ ጥናት ግንቦት 30 አካሂዷል።

የዩንቨርስቲው ሂውማኒቲስ ትምህርት ክፍል ዲን ዋልተ ንጉስ መኮንን (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ መሆኑን እና በርካታ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ በየዓመቱ የሚካሄዱ የምርምር ጉባኤዎች እውቀት መካፈያ መድረክ ነው ብለዋል፡፡ በመድረኩ በቋንቋ፣ ባህል እና መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ በተመለከተ 15 ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የአውደ ጥናቱን ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት የዕለቱ የክብር እንግዳ  ገጣሚ፣ ደራሲ፣  መምህር እና ተመራማሪ በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) አሁን ላይ ያለው ትውልድ ባህሉን ፣ ወጉን እና ሀገራዊ የማኅበረሰብ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ በሚያየው እና በሚሰማው ለኛ በማይጠቅመን ዘመነኛ ዲጅታል ግንኙነት ስለቀየረው ትውልዱን የማዳን ሥራ መሰራት እንዳለበት እና ተግባቦት ከባህልና ከቋንቋ ጋር መጣጣም እንዳለበት ገልጸዋል። ይሄንን ለማምጣት አሁን ላይ በተጨባጭ ያለው የትምርህት ሥርዓት መቀየር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የባህር ዳር ዩንቨርሲቲ  ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ እና ኮሙኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዘውዱ እምሩ (ዶ/ር) በተለያዩ  ጊዜዎች የሚደረጉ ዓውደ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች ተቋማት ጋር የመገናኛ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረጊያ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል ።

የባህል እና ቋንቋ ተግባቦት ጉዳዮች የማኅበረሰቡን የአስተሳሰብ ደረጃ በመምራት በኩል ያላቸውን አስተዋጽኦ ምን እንደሆነ እና  የምርምር ሥራዎች በማኅበረሰቡ ያመጡትን ለውጥ ደግሞ ወደ ታች ወርደው የመመርመር ተግባር መገናኛ ብዙኃን ሊደግፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here