ችግሩ ከክለቡ ወይስ ከአሰልጣኙ?

0
181

ስኮትላንዳዊው የቀድሞው አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከኦልትራፎርድ በጡረታ ከተገለሉ በኋላ ዴቪድ ሞይስ፣ሊዊዝ ቫንሀል፣ጆዜ ሞሪኒሆ እና የቀድሞ ኮከባቸው ኦሊጉነር ሶልሻየር በቋሚነት የኦልትራፎርድን ሥራ የሞከሩት አሰልጣኞች ናቸው። በጊዜያዊነት ኦልትራፎርድ ደርሰው የተሰናበቱ አሰልጣኞችም አሉ::
ነገር ግን አንዳቸውም ውጤታማ ሳይሆኑ ሥራው ከብዷቸው መሰናበታቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ ሌላኛው ባለ ተረኛ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ሆነዋል። ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ወጣቶችን ይዞ በአያክስ አምስተርዳም የፈፀመው ገድል ለማንቸስተር ዩናይትድ ሥራ አብቅቶታል።
የማንቸስተር ዩናይትድን የቀድሞ አስፈሪ ሞገስ እና ዝና ለመመለስም ህልሙ እውን ወደ ሚሆንበት መንደር ቲያትር ኦፍ ድሪምስ በ2022 እ.አ.አ ነው የደረሰው። የ53 ዓመቱ አሰልጣኝ በአያክስ እያለ የእግር ኳስ ፍልስፍናው፣ የታክቲክ እውቀቱ፣ ጠንካራ እና ታታሪነቱ፣ ተጫዋቾችን የሚያሻሽልበት መንገድ በወቅቱ በብዙዎቹ የማንቸስተር ደጋፊዎች እና ኃላፊዎች እንዲወደድ አድርጎታል።
ሆላንዳዊው አሰልጣኝ አሁን ላይ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ቤት ከመጣም ሁለተኛ የውድድር ዘመኑን እያሳለፈ ይገኛል። ምንም እንኳ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ መጠነኛ መረጋጋት እና መሻሽል ቢታይበትም በአውሮፓ መድረክ እና በሌሎቹ ውድድሮች ግን አሁንም የአቋም መዋዠቅ ይታይበታል።
ኤሪክ ቴን ሀግ ማንቸስተር ዩናይትድን ከተረከበ በኋላ ለተጫዋቾች ዝውውር 400 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ ገደማ አውጥቷል። 16 አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረምም ቡድናቸውን እንደገና በሚፈልጉት መንገድ ለመገንባት ሞክረዋል። ግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና፣ አንቶኒ ፣ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ፣ ሜሰን ማውንት፣ ጄደን ሳንቾ፣ ክርስቲያን ኤሪክሰን እና ሶፊያን አምራባት ከአዳዲሶቹ መካከል ይገኙበታል። ለተጫዋቾች ግዢ ከፍተኛ ገንዘብ ያወጣው ቴን ሀግ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ ሜዳ ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ማምጣት አልቻለም። እንዲያውም የውድድር ዘመኑ አጋማሽ ሳይደርስ ገና ከወዲሁ በርካታ መጥፎ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘገበ ነው።
የቱርኩ ክለብ ጋላታሳራይ ከ117 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ክለቦችን በማሸነፍ አዲስ ታሪክ መፃፍ ችሏል።ጋላታሰራይ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊጉ ማንቸስተር ዩናይትድን በመርታት ነው መጥፎ ታሪኩን መሰረዝ የቻለው። በተጨማሪም በዚሁ በሻምፒዮንስ ሊጉ ፣የመጀመሪያዎቹን ሁለት የምድብ ጨዋታዎች በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸንፏል -ማንቸስተር ዩናይትድ። በእነዚህ ጨዋታዎች በድምሩ ሰባት ግቦች ሲቆጠሩበት ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ማንቸስተር ዩናይትድ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ከ1992 እ.አ.አ በኃላ በፕሪሜርሊጉ መጥፎ የሚባል አጀማመር ነው ያደረገው። ከመጀመሪያዎቹ ሰባት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በአራቱ ተሸንፏል።ከ1989 እ.አ.አ በኋላ በሰባት የሊግ ጨዋታዎች አነስተኛ ነጥብ በመሰብሰብም መጥፎ ነው የተባለውን ታሪክ ጽፏል።
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ኦልትራፎርድ እስከሚደርስ የላንክሻየሩ ክለብ በቶተንሀም ሆትስፐርስ ሜዳ ነጥብ ጥሎ አያውቅም ነበር። በአሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ዘመን ግን ይህ ታሪክ ተቀይሯል። ከ1973/74 እ.አ.አ የውድድር ዘመን በኋላ ክለቡ በተከታታይ በሜዳው ያደርጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፈዉ በአሰልጣኝ ኤሪክቴን ሀግ እየተመራ ነው።
በሮቤርቶ ዲዘርቢ የሚመራው ብራይተን ሆብ አልቢዮን ወደ ኦልትራፎርድ በመጓዝ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ያሸነፈውም ዘንድሮ ነው። ለአብነት እነዚህን አነሳን እንጂ ሌሎችም መጥፎ ክብረ ወሰኖች እንዳሉ መረጃዎች አመልክተዋል።
የተመዘገቡት ደግሞ በኤሪክ ቴን ሀግ የ18 ወራት የአሰልጣኝነት ጊዜው መሆኑ አሰልጣኙ ጫና ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ተጫዋቾችም በራስ መተማመናቸው ዝቅ ብሏል። ተነሳሽነት እና የማሸነፍ ወኔያቸው ም ተሰልቧል። በዚህ ምክንያትም የመልበሻ ቤቱ የቡድን መንፈስም መረበሹን የዘ ቴሌግራፍ መረጃ ያመለክታል።
አስልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ የኦልትራፎርድ ሥራውን በጀመረበት ማግስት ከክለቡ ታላላቅ ተጫዋቾች ጋር እሰጣ አገባ ውስጥ ገብቶ ነበር:: ይህ ደግሞ የእርሱን እና የተጫዋቾችን ትኩርት የሚያሳጣ ፣ የመልበሻ ቤት ክፍሉን የሚረብሽ ነው ሲሉ ብዙዎቹ ይኮንኑታል፡።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከአሰልጣኙ ጋር ባለመስማማቱ ወደ ሳውዲ አረቢያው ክለብ አልናስር አቅንቷል::በወቅቱም በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ፖርቹጋላዊውን ኮከብ ጥፋተኛ አድርገውት ሲያወግዙት እንደነበር ይታወሳል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ እንግሊዛዊው አጥቂ ጄደን ሳንቾ የሮናልዶ ዓይነት ችግር ገጥሞታል። አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ወጣቱን አጥቂ ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት የሚሳነው ደካማ አጥቂ ነው ብለው በአደባባይ መወረፋቸው ከተጫዋቹ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲሻክር አድርጎታል። በዚህ ምክንያትም የተጫዋቹ ስነ ልቦና ክፉኛ ስለመጎዳቱ የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋቾች ተናግረዋል። በቀጣይ በሚከፈተው የጥሩ የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት የእንግሊዛዊው ተጫዋች ዕጣ ፈንታም እንደ ክርስትያኖ ሮናልዶ ክለቡን መልቀቅ ሳይሆን እንዳልቀረ በስፋት እየተዘገበ ነው

ጥቂት ተጫዋቾች ከፍተኛ ጉልበት የሚያስወጣውን የኤሪክ ቴን ሀግ የልምምድ ስልት አልወደዱትም።ይህም ሜዳ ላይ ለሚመዘገበው ውጤት አንደኛው ምክንያት ተደርጎ ይነሳል። የክለቡ ወሳኝ የሚባሉት ተጫዋቾች ማርከስ ራሽፎርድ፣ ካስሜሮ፣ ራፋኤል ቫራን፣ ጄደን ሳንቾ፣ የመሳሰሉት ደካማ አቋም ማሳየታቸው ችግሩን ከኤሪክ ቴን ሀግ የልምምድ ስልት ጋር የሚያያይዙትም አሉ። በተለይ የራሽፎርድ ከጊዜ ወደ ጊዜ አቋም መውረድ ሰበቡ አሰልጣኙ እንደሆኑ በብዙዎች እየተነገረ ነው::
የውድድር ዘመኑ ገና ባለመጋመሱ አሁን ላይ የአሰልጣኙ እና የተጫዋቾችን ብቃት መገምገም ባይቻልም ሁሉም በሚባል ደረጃ ተጫዋቾች ከአምናው የተሻለ ብቃት ማሳየት አልቻሉም።
አሰልጣኙም ቢሆን በየ ጨዋታው ሜዳ ላይ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ እየተጋባ መሆኑን በቀላሉ ሜዳ ላይ መረዳት ይቻላል። እንደ ታሪኩ ማደር የተሳነው ማንቸስተር ዩናይትድ አሁን ላይ 50 በመቶ የማሸነፍ ምጣኔ አለው። ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድርስ ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች ሰባቱን አሸንፎ በአምስቱ ደግሞ ተሸንፏል። ከአራት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ነው ያሸነፈው።
በተጨማሪም ሁለት የሊግ ጨዋታዎችን ሲያደርግ አንዱን በመርታት በአንዱ ተረቷል።ምንም እንኳ በየጨዋታው አንድ አንድ ግብ እያስቆጠረ ከሜዳ ቢወጣም ቢያንስ አንድ ግብ ደግሞ ይቆጠርበታል። ይህ አኃዝም ማንቸስተር ዩናይትድን ለመሰለ ገናና ክለብ ጥሩ ክብረወሰን አለመሆኑን የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች ጋሪ ኔቭል ይናገራል።
ኤሪክ ቴን ሀግ በአያክስ አምስተርዳም የአምስት ዓመታት ቆይታው የሚፈልገውን ቡድን ገንብቷል::ውጤታማ ሆኖም አሳይቷል::ያንን ተሞክሮ እና ልምዱን ግን በእንግሊዙ ክለብ ለመድገም አስቸጋሪ እንደሆነበት ነው ዘ ኢንድፔንት የዘገበው::
የክለቡ የቆየ እና የገነገነ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ደጋፊዎቹ የሚፈልጉትን ለውጥ ለማምጣት ከባድ ሆኖበታል። ሰውዬውም ቢሆን የተረከበው ፕሮጀክት አስቸጋሪ በመሆኑ ክለቡን ለማሻሻል እንዳሰበው ቀላል አለመሆኑን ተናግሯል:: ደጋፊዎቹም የክለቡን የአጨዋወት ስልት እንዳልተረዱት እና እንዳልገባቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ክለቡ በኒውካስትል ዩናይትድ እና በማንቸስተር ሲቲ ከመሸነፉ በፊት ሦስት መርሀ ግብሮችን ብሬንትፎርድን ፣ሼፊልድ ዩናይትድን እና ኮፐን ሀገንን ሲያሸንፉ በዲያጎ ዳሎት እና በአንድሬ ኦናና ትክሻ ላይ ተንጠልጥሎ ማሸነፉን ደጋፊዎቹ አስታውሰዋል።
በኤሪክ ቴን ሀግ የሚመራው ቡድን አሳማኝ በሆነ መንገድ ዘንድሮ ያሸነፈው በካራባው ዋንጫ ክሪስታል ፓላስን ብቻ መሆኑ በአሰልጣኙ ላይ ብዙ ጣቶች እንዲቀስሩበት ምክንያት ሆኗል። የክለቡን የሜዳ ላይ ችግሮች ካባባሱት ምክንያቶች ደግሞ የግሌዘር ቤተሰቦች የክለቡን ሽያጭ ማጓተታቸው ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳል።
ማንቸስተር ዩናይትድን ለመግዛት እንግሊዛዊው ቢሊየነር ሰር ጂም ራትክሊፍ እና የኳታሩ ባለሀብት ሼክ ጃሲም ቢን ሀሚድ አልታሀኒ ፍላጎት አሳይተው እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ ባሳለፍነው የክረምት ወር የሽያጭ ሂደቱ ሳይሳካ ቀነ ገደቡ ተጠናቋል።
የማንቸስተር ዩናይትድ ገዢዎች እንዲርቁ ካደረጉት ነገሮች መካከል ከፍተኛ የገንዘብ እዳ መሸከሙ አንዱ ነው። ሌላው የክለቡ የአክሲዮን ዋጋ 25 በመቶ መቀነሱን ተከትሎ የሽያጭ ሂደቱ በቅርቡ እውን ይሆናል የሚል ግምት እንደሌለ በእንግሊዝ ጋዜጦች በስፋት እየተነበበ ነው።
እንግሊዛዊዉ ባልሀብት ሰር ጂም ራትክሊፍ ማንቸስተር ዩናይትድን ሙሉ በሙሉ የመግዛት ፍላጎቱን ትቶ የክለቡን 25 በመቶ ድርሻ በመግዛት ከግሌዘር ቤተሰቦች ጋር አብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳለው በቅርብ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
ደጋፊዎችም ባለሀብቶቹን የግሌዘር ቤተሰቦች “ክለባችንን ልቀቁ” የሚል ድምፅ ማስተጋባታቸውን አሁን ድረስ በየጨዋታው ቀጥለዋል።
የደጋፊዎቹ የተቃውሞ ድምፅ እርሱን እና ተጫዋቾችን እንደማይረብሻቸው አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ቢናገርም፣ የቀድሞ ኮከባቸው ጋሪ ኔቭል ግን በዚህ ሀሳብ አይስማማም። ይህ አደገኛ ነገር ነው። አሰልጣኙ እና ተጫዋቾችን ይቅርና ሁሉንም የክለቡ ኃላፊዎች የሚረብሽ ነው በማለት ጋሪ ኔቭል ያስረዳል።
እንደ እግር ኳስ ተንታኙ ላውረንስ ትንታኔ አሰልጣኙ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ከመጣ ጀምሮ በክለቡ አቋም እንደዚህ መዋዠቅ ምክንያት እንቅልፍ ቢያጣም ሥራውን ግን የክለቡ ኃላፊዎች ሊያሳጡት እንደማይችሉ ያስረዳል::

(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here