እ.አ.አ በ2013 ስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ማንቸስተር ዩናይትድን በጡረታ ከተሰናበቱ በኋላ በኦልትራፎርድ በርካታ አሰልጣኞች ተፈራርቀዋል። ዴቪድ ሞይስ፣ ሊዊስ ቫንሀል፣ ጆዜ ሞሪንሆ እና ኦሊጉነር ሶልሻየር የኦልትራፎርድን ሥራ ሞክረዋል። ሪያን ጊግስ፣ ማይክል ካሪክ እና ራልፍ ራኝክም በጊዜያዊነት በአሰልጣኝነት አገልግለዋል። ይሁን እንጂ ሁሉም አሰልጣኞች በኦልትራፎርድ አንዳች ለውጥ ማምጣት ተስኗቸው ከዙፋናቸው ወርደዋል።
አሁን ደግሞ ተራው የኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ሆኖ ክልቡን እያሰለጠነ ይገኛል። የ54 ዓመቱ አሰልጣኝ በ2022 እ.አ.አ ነው ማንቸስተር ዩናይትድን የተቀላቀለው። በአያክስ አምስተርዳም ቤት ቡድኑን በወጣት ኮከቦች በመገንባት በተከታታይ ዋንጫውን በማንሳት ሦስታት (ሀትሪክ) ሠርቷል። በአያክስ አምስተርዳም የሠራው ገድል እና የገነባው አስደናቂ ቡድንም ለኦልትራፎርድ ሥራ አብቅቶታል።
የክለቡ የአክሲዮን ባለድርሻ የሆኑት የግሌዘር ቤተሰቦች አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግን ወደ ማንቸስተር ከተማ ሲያመጡት እንደ ታሪኩ ማደር የተሳነውን ክለብ ወደ ቀድሞ ኃይልነቱ እንደሚመልሰው እምነትን አሳድረው ነው። ህልም እውን በሚሆንበት መንደር (ቲያትር ኦፍ ድሪምስ) ቀናቶች ተቆጥረው ወራቶች ሲነጉዱ ግን ደጋፊዎች እና የክለቡ ባልሀብቶች የሚፈልጉት ለውጥ በቀያይ ሰይጣኖቹ መንደር አልመጣም።
በአሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ እምነትን ያሳደሩ የክለቡ ደጋፊዎችም ችግሩ ከአሰልጣኙ ሳይሆን ከግሌዘር ቤተሰቦች እንደሆነ በማመን “ክለባችንን ልቀቁ” የሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ አሰምተዋል። ተቃውሞው ሲበርታ በ2023 አ.አ.አ አሜሪካውያን ባልሀብቶቹ 25 በመቶ የአክሲዮን ድርሻውን ለእንግሊዛዊው ሰር ጂም ራትክልፊ አሳልፈው ሸጠዋል። ውሳኔውም ለክለቡ ደጋፊዎች እፎይታ የሰጠ እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል።
እንግሊዛዊው ቢሊየነር በክለቡ ያላቸው ተሰሚነት እና ውሳኔ ሰጭነት ክለቡን ወደ ቀደመ ስም እና ዝናው እንዲመለስ ያግዘዋል የሚል ተስፋ ተሰንቆም ነበር። ነገር ግን የቀያይ ሰይጣኖቹ ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ስለመምጣቱ በስፋት እየተዘገበ ነው። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድርሰ በፕሪሚየር ሊጉ ሰባት ጨዋታዎችን በማድረግ ስምንት ነጥቦችን ብቻ ሰብስቧል።
በደረጃ ሰንጠረዡም 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አሁን ላይ የማንቸስተር ዩናይትድ ውጤት ከመሪዎቹ ይልቅ ለወራጅ ክለቦች እንደሚቀርብ ቁጥሮቹ ይናገራሉ። እ.አ.አ ከ1989/90 የውድድር ዘመን በኋላ ዘንድሮ መጥፎ የተባለውን አጀማመር አድርጓል። እንደ ብዙዎቹ ገለጻ ኤሪክ ቴን ሀግ በኦልትራፎርድ ግራ ተጋብቷል። ቋሚ ተሰላፊ ተጫዋቾችን እስካሁን አለማወቁ፣ በየጨዋታው አዳዲስ ታክቲኮችን መሞከሩ አሰልጣኙን እቅድ አልባ ነው አስብሎታል። በዚህ ዓመት እያሳየ ባለው መጥፎ አጀማመር ከአምናው የባሰ ውጤት እንዳያስመዘግብ ከወዲሁ ስጋትን ፈጥሯል።
የክለቡ የቆየው የእግር ኳስ ባህል ጠፍቶ ቅርጽ አልባ ሆኗል። ለዚህ ማሳያ ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ በሜዳው በቶትንሀም ሆትስፐርስ ሦስት ለባዶ የቀመሱበትን እና ከፖርቶ ጋር አቻ የተለያየበትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። ይሁን እንጂ የአሰልጣኙ ሥራ አደጋ ላይ እንደማይወድቅ የአክሲዮን ባለድርሻው እንግሊዛዊው ባለሀብት ተናግሯል።
የስልጠና መንገዱ ለተጫዋቾች ምቹ ካለመሆኑ በተጨማሪ ግትር እንደሆነ ይነገራል። ከክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ጀደን ሳንቾ ጋር መግባባት ያልቻለውም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ጋዜጦች አስነብበዋል። አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ማንቸስተር ዩናይትድን ከተረከበ በኋላ እስካሁን 125 ጨዋታዎችን አከናውኗል። ከዚህ ውስጥ በ69ኙ ጨዋታ፤ በተለያየ አሰላለፍ እና ታክቲክ ጨዋታዎችን መጀመሩን የስፖርቲንግ ኒውስ መረጃ ያሳያል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሪሚየር ሊጉ በታሪኩ አነስተኛ ነጥብ ያስመዘገበበት፣ ትንሽ ጨዋታዎችን ያሸነፈበት እና ብዙ ግቦች የተቆጠሩበት ባለፉት ሁለት ዓመታት በአሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ዘመን ነው። ባሳለፍነው ዓመት በ60 ነጥቦች ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ዓመቱን መጨረሱ አይዘነጋም። ይህ ውጤትም በክለቡ ታሪክ መጥፎ ሆኖ በታሪክ ማህደሩ ሰፍሯል።
በ2021/22 የውድድር ዘመን አነስተኛ ነጥብ ይዞ የጨረሰበት ወቅት ሲሆን በውድድር ዘመኑ መጨረሻ 58 ነጥቦችን ብቻ ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ከዚህ በፊት በአሰልጣኝ ዴቪድ ሞይስ የመጀመሪያ ዓመት የኦልትራፎርድ ቆይታው ያስመዘገበውን መጥፎ ክብረወሰንም ሰብሯል። ዴቪድ ሞይስ ስኮትላንዳዊውን የቀድሞውን አሰልጣኝ በመተካት ማንቸስተር ዩናይትድን በተረከቡበት የመጀመሪያው የውድድር ዘመን 64 ነጥቦችን ነበር ይዘው የጨረሱት።
ይህ ብቻ ሳይሆን ማንቸስተር ዩናይትድ በታሪኩ 49 ግቦችን ብቻ በማስቆጠር መጥፎ ታሪክ ያሰመዘገበው በ2015/16 የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ሊዊስ ቫንሀል ዘመን ነበር። ኤሪክ ቴን ሀግ በፕሪሚየር ሊጉ በአንድ የውድድር ዘመን አነስተኛ ግቦችን ያስቆጠረ ሁለተኛው አሰልጣኝ መሆን ችሏል። ባሳለፍነው ዓመት ደግሞ በተጋጣሚዎቹ ላይ ካስቆጠራቸው ግቦች የበለጠ በራሱ መረብ ላይ ግቦች ተቆጥረውበት ዓመቱን ጨርሷል። ይህም ሌላኛው መጥፎ ክብረ ወሰን ሆኖ ነው የተመዘገበው።
ማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግን በኃላፊነት ከሾመ በኋላ 700 ሚሊዮን ዩሮ ገንዘብ በላይ ለተጫዋቾች ዝውውር አውጥቷል። አንቶኒ፣ ካስሜሮ፣ ማውንት፣ ዚርከዚ፣ ዮሮ፣ ማርቲኔዝ፣ ኦናና፣ ሆይሉንድ፣ ዴሊት እና ኡጋርቴን የመሳሰሉት ኤሪክቴን ሀግ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ወደ ኦልትራፎርድ ካስኮበለላቸው መካከል ተጠቃሾች ናቸው። ምንም እንኳ ክለቡ በተጫዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ገንዘብ ቢያወጣም ሜዳ ላይ የሚታይ ለውጥ ግን ማምጣት አልቻለም። እንዲያውም ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ብዙዎቹ ተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጧቸዋል።
335 ሚሊዮን ፓውንድ የሚገመት ዋጋ ያላቸው ተጫዋቾችን ተጠባባቂ ወንበር እንዲያሞቁ ማድረጉ ዝውውሩን ያልተጠና እና እብደት ሲሉ ብዙዎች ገልጸውታል። አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ የማንቸስተር ዩናይትድ አቋም መዋዠቅ ምክንያቱን ሲያስረዱ የአዳዲስ ተጫዋቾችን የግል ታሪክ ማግኘት ፈታኝ እንደሆነ ተናግሯል። እርሱ ይህን ይበል እንጂ በአያክስ አምስተርዳም አብረውት የሠሩት ማቲያስ ደሊት እና አንቶኒ በላንክሻየሩ ክለብ ተሰጥኦቸውን አውጥቶ መጠቀም ተስኗቸዋል።
አሁን ላይ በማንቸስተር ዩናይትድ ስብስብ ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች በተለይ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ልምድ እና ብስለት ይጐላቸዋል። በቡድኑ ውስጥ ያሉት ካስሜሮ፣ ጆኒ ኢቫንስ እና ሀሪ ማጉየር ምንም እንኳ ልምድ ያላቸው ቢሆንም ከዚህ በኋላ ከክለቡ ጋር መቀጠላቸው ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል። ታዲያ የማንቸስተር ዩናይትድን የቀድሞ አስፈሪ ሞገሱን እና ኃያልነቱን ለመመለስ የክለቡ መዋቅራዊ ጉዳዮች መስተካከል ይኖርባቸዋል።
አሁን ያለው የተጫዋቾች ስብስብ ጥራት እና ጥልቀት ይጎለዋል። ታዲያ የተጨዋቾችን የምልመላ ሂደት እንደገና በማጤን ሊሠራ እንደሚገባም የቀድሞው የሊቨርፑሉ ተጫዋች ጂሚ ካራገር ተናግሯል። አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግም በእርሱ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች በፍጥነት መፍትሄ ካልሰጠ ዕጣ ፈንታው ከእርሱ በፊት እንደነበሩ ሌሎች አሰልጣኞች ሊሆን ይችላል ተብሏል።
መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም የክለቡ ባለቤቶች እና ኃላፊዎች በክለቡ መጪው ዕጣ ፈንታ በጠረጴዛ ዙሪያ በተነጋገሩበት ወቅት ምንም እንኳ ክለቡ አስቸጋሪ ጊዜ እያሳለፈ ቢሆንም አስልጣኙ ሥራውን እንደማያጣ አረጋግጫለሁ ሲል ስካይ ስፖርት አሰነብቧል። ባሳለፍነው ዓመት ክለቡ አዲስ አሰልጣኝ ይቀጥራል ተብሎ ከብዙ አሰልጣኞች ጋር ስሙ ተያይዞ ነበር። ጋሪዝ ሳውዝጌት፣ ቶማስ ቱህል፣ ግራም ፖተር እና የኢንተር ሚላኑ አለቃ ሲሞኒ ኢንዛጊ ከቀያይ ሰይጣኖች ጋር ስማቸው እንደተነሳ የሚታወስ ነው።
አሁን ላይ የሊግ ጨዋታዎች አቁመው የዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ተጀምረዋል። ይህም ለአሰልጣኙ እና ትችት ለወረደባቸው ተጫዋቾቹ እፎይታን ይሰጣል ተብሎ ይገመታል። ማንቸስተር ዩናይትድ ከዓለም አቀፍ ጨዋታዎች መልስ በሜዳው ብሬንት ፎርድን የሚያስተናግድ ይሆናል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም