ችግኞችን በመንከባከብ፤ ለፍሬ እናብቃ!

0
77

ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን እየተገበረች ትገኛለች፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት 40 ቢሊዮን ችግኞችን የተከለችው ኢትዮጵያ፤ በ2017 የክረምት ወቅትም ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብታለች፡፡

 

ከእነዚህ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተተከሉት 40 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥም 63 በመቶ የሚሆኑት ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከተተከሉት 40 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ 63 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸው በምግብ እህል ራሷን ለመቻል ጥረት ለምታደርገው ሀገራችን ትልቅ ትርጉም አላቸው፡፡ እናም ችግኞችን ከሚሰጡት ጠቀሜታ አንጻር እየመዘኑ በዚህ መልኩ መትከል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡

 

በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የታየው ሌላው መልካም ነገር ችግኞችን ተንከባክቦ በማጽደቅ ረገድ የተሠራው ሥራ እና ለውጥ ነው፡፡  ክረምት በመጣ ቁጥር ችግኞች በዘመቻ ይተከሉ እንጂ ተንከባክቦ ማጽደቅ ላይ ብዙም ትኩረት እንደማይሰጥ ሲነገር መስማት የተለመደ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከ2011 ጀምሮ የተተከሉትን ችግኞች ተከትሎ የመጡትን ለውጦች ስናይ የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ያለማጽደቅ ችግርን እየፈታን ወደ ፊት እየተራመድን ስለመሆናችን የሚያረጋግጡልን ናቸው፡፡  ባለፉት ዓመታት በሀገራችን የተተከሉ ችግኞች በተደረገላቸው እንክብካቤ ጸድቀው ከምርት ውጭ የነበረ መሬት ወደ ምርት እንዲመለስ እያደረጉ ነው፡፡

 

የ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በተካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው ባለፉት ዓመታት የተተከሉት ችግኞች የአፈር ለምነት እንዲጠበቅ ከማድረግ እስከ ተፋሰስ ደኅንነት መረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

 

እየተተከሉ ያሉ ችግኞች የአረንጓዴ አሻራ ተፋሰሶች አረንጓዴ ሆነው ለጎብኝዎች ምቹ እንዲሆኑ፣ ለም አፈራችን እየተጠረገ እንዳይሄድ፣ የኅይል እና የመስኖ ግድቦቻችን በደለል እንዳይሞሉ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ የደን ሽፋኑም  በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ አሁን ላይ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡

 

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው ከ43 በመቶ በላይ የሚሆነው መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ ነው፡፡ በአሲዳማነት የተጎዳን መሬት በኖራ በማከም ምርታማነትን በሦሥት እጥፍ ማሳደግ እንደሚቻልም መረጃው ይጠቁማል፡፡  ሆኖም ለኖራ ለግዥ የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ ነው፡፡ እናም ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጥ የሚችለው ደን ልማት ላይ በስፋት መሥራት እንደሆነ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጎርፍ እየታጠበ የሚሄደውን ለም አፈር ከማዳን ባለፈ ለኖራ ግዥ የሚወጣውን ገንዘብ በማስቀረት ረገድ  የሚያበረክተው አስተዋኦ ከፍ ያለ ነው፡፡

 

የአማራ ክልልም የአረንጓዴ አሻራን መነሻ አድርጎ ችግኞችን በመትከል ላይ ይገኛል፡፡ የሚተከሉ ችግኞች የደን ልማት ሽፋንን የሚያሳድጉ፣ የጥምር ደን ልማትን የሚያበረታቱ እና በፍራፍሬ ምርት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

 

የተተከሉ ችግኞችን የጽድቀት ምጣኔ ከፍ ለማድረግ የሚተክለው አካል ለተተከሉ ችግኞች ባለቤት እንዲሆን ከማድረግ  ከፍተኛ ክትትል እና ቁጥጥር እንደሚደረግም ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኜነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ችግኞች የተተከሉበት ጉድጓድ እርጥበት ይዞ እንዲቆይ ጉድጓድ የማልበስ ሥራ ይከናወናል፡፡ የአረም እና ኩትኳቶ ሥራ በትኩረት ይሠራል፡፡

 

በአጠቃላይ “መትከል ምግብም ነው፤ ውበትም ነው፡፡ የምንተክለው ምግባችንን ነው፤የምንተክለው ለዐይናችን የሚያምር እና የሚመቸን መስክ ለመፍጠርም ጭምር ነው፡፡ ዛሬ ላይ የተራቆቱ እና የሚያስፈሩ ተራሮች አረንጓዴ ለብሰው መታየታቸው የአረንጓዴ  አሻራ ውጤት እያመጣ  ስመሆኑ  ማሳያ ነው፡፡  ይህ ውጤት ዘለቄታ ኖሮት አገራችን ደንን ከማልማት ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም ታገኝ ዘንድ እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አጠናክሮ መቀጠልና ለሚተከሉ ችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ለፍሬ ማብቃት ይገባል፡፡

 

በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here