በፓርኩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዝሆኖች መኖራቸው ተጠቁሟል:: ይህም በዓለም በርካታ የዝሆኖች መገኛ ከሆኑ ከቀዳሚዎች ረድፍ አሰልፎታል:: በፓርኩ ክልል በሚገኙ ትልልቅ ዛፎች እና ሣር ውስጥ በቅርበት የሚተራመሱ ታዳኞችን የሚቃኙ አናብስት የጐብኚዎች የዓይን ማረፊያ ናቸው::
በደረቅ ወቅት ወይም በበጋ የዱር እንስሳት ውኃ ለመጠጣት ሲሰባሰቡ አናብስቱ አድብተው ግዳይ ሲጥሉ መመልከት ለጐብኚዎች ድንቅ በአእምሮ የሚቀር ትርኢት ነው::
በፓርኩ ክልል በሺህዎች የሚቆጠሩ በጥቁር እና ነጭ ቀለማት የተዋቡ የሜዳ አህያዎች በዝናብ ወቅት ከአንዱ ቀጠና ወደ ሌላው ሲፈልሱ ይታያሉ::
ዓመቱን በሙሉ በቾቤ ወንዝ ዳርቻ የማይጠፉት ጉማሬዎች በሳቢነታቸው ተጠቃሽ ናቸው:: የፓርኩን ለጥ ያሉ ሜዳዎች በብዛት ከሚርመሰመሱባቸው መካከል በቁመት ዘለግ ያሉት ቀጭኔዎችም ይገኙበታል::
ቾቤ ፓርክን ከሚያደምቁት ግዙፍ የዱር እንስሳት ጐሽ፣ ጅብ እና አቦሸማኔ ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደሉም::
በፓርኩ 450 የዓእዋፍ ዝርያዎች እንደሚገኙ ድረ ገፆች አስነብበዋል:: ከጥር እስከ ሚያዚያ በመንጋ ወደ ቀጠናው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ስለሚገቡ ለአእዋፍ አድናቂ እና ጐብኚዎች ተመራጭ ወቅት ነው::
ቾቤ ብሔራዊ ፓርክን ለመጐብኘት ሰሜናዊ ክልል መግቢያ በቅርበት በሚገኘው “ካሰኔ” ዓየር ማረፊያ መድረስ ተመራጭ መሆኑን ድረ ገፆች በማጠቃለያነት አስፍረዋል::
ለዘገባችን ቾቤ፣ አፍሪካን ትራቭል ካንቫስ፣ ቦትስዋና ቱሪዝም ድረ ገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም