ነዋሪዎችን ያስቆጣው ማሻሻያ

0
132

በቻይና ሄናን ግዛት የሚገኘው 314 ሜትር ከገደል ላይ ቁልቁል የሚወረወረው ፏፏቴ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሰው መጠን እንዳይቀንስ በሰው ሰራሽ ቱቦ በሚደገፍ ውሀ መታገዙ በነዋሪዎች ቁጣ ማስነሳቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ  አስነብቧል::

የዩንታይ ፏፏቴ በዩንታይ ተራራ ቁልቁል የሚወረወር ለጐብኚዎች ድንቅ እይታን የሚለግስ ተፈጥሯዊ የመስህብ ስፍራ ነው:: ለአብነትም በ2019 ተፈጥሯዊ ፏፏቴው 11 ሚሊዮን ጐብኚዎችን አስተናግዷል::

የግዛቱ ባለስልጣናት ከጐብኚዎች ለተሰነዘረው ቁጣና ትችት ዝናብ በሌለባቸው ወራት የውሀው መጠን ስለሚቀንስ ይህንኑ ለማካካስ እና ለጐብኚዎች ድንቅ እይታ ለማስገኘት መጠነኛ ማሻሻያ ማድረጋቸውን አምነዋል::

የግዛቱ ባለስልጣናት የሰጡት መልስ የተቀሰቀሰውን ቁጣ አላበረደውም:: ለምን ቢሉ ይህንን መልስ ሰዎች አውቀው ጥያቄውን ከማንሳታቸው፣ ሁነቱን ከማውገዛቸው በፊት ሊገለጽ ይገባ ነበር ሲሉም ሞግተዋል::

ስሜታቸው በእጅጉ መጐዳቱን  የገለፁት ጐብኚዎቹ ሁሉም ተፈጥሯዊ መስህቡን ለማየት እንጂ በቱቦ ወይም በቧንቧ የሚሳብ ውሀን ለመመልከት አለመጓጓዛቸውን በአጽንኦት አስምረውበታል::

ከሁሉም በላይ ተፈጥሯዊ መስህቡ ማለትም ፏፏቴው በሄናን ግዛት የሚገኝ ሲሆን የፏፏቴው ምንጭ  ወይም የውሀው መነሻ ሻንታይ ግዛት ነው:: ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደተናገሩት የሻንታይ ግዛት ባለስልጣናት የውሀ ማጠራቀሚያ ገንብተዋል:: የውሀ ማጠራቀሚያው ከዩንታይ ፏፏቴ ይሄድ የነበረውን ወንዝ አግዶ መጠኑ እንዲቀንስ አድርጓል::

የዩንታይ ግዛት ባለስልጣናት የፏፏቴውን ውሀ መጠኑ እንዳይቀንስ ሰው ሰራሽ ማጐልበቻ መስራታቸውን በግልጽ ሳይናገሩ መግለጫ ሳይሰጡ ማሻሻያውን በመፍትሄነት መገንባታቸው ትክክል አለመሆኑ ነው የተገለጸው።

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here