“ነውር ነው”

0
251

በልጅነት የሰማሁት አንድ የሚገርመኝ አጋጣሚ ነበር:: ለዓመታት መልስ ያላገኘሁለት ግርምቴ ነው:: በሰፈራችን የእማ ውዴ ልጅ ስትዳር የጣለው ዝናብ ዛሬም ድረስ አይረሳኝም:: ዝናቡ በረዶ ጭምር የቀላቀለ ነበር:: ወሩ ሙቀት የሚበዛበት ሚያዝያ ወር ነው:: በእኔ አካባቢ ደግሞ ሚያዝያ ወር በጣም ከፍተኛ ሙቀት የሚታይበት እንጂ ዝናብ የሚጥልበት አልነበረም:: እና የእማ ውዴ ልጅ ትዕግሥት ስትዳር ግን ዝናቡ  በረታ:: ጎርፉ ዳሱን እና ቤቱን  በጭቃ ሞላው:: የሰርጉን ድባብ ቅዝቃዜ ሞላው:: “ሃይ ሎጋ” የሚለው ወጣት ሰርገኛ  ጠላውን እየጠጣ አልዘፍን አለ:: የሙሽሪት አጎት “አይ ይች ልጅ ደረቆቱን (ደረቆት በቆሎው ለጠላ እህል ሲዘጋጅ የሚቆላው ቆሎ ነው) ስትቅም ከርማ ሰርጓ በዝናብ ያበስብሰን”  ብሎ ተገረመ:: ሰርገኛው ሳቀባት:: እውነት ነውም አለ:: በልጅነቷ የጠላ እህል በመብላቷ የሰርጓ ቀን ዝናብ ዘነበ ብሎ ያምናል ማህበረሰቤ::ሰርግሽ ተበላሸ ነው የሚባለው::

እንዲሁ በተመሳሳይ ልጆች ሆነን በክረምት ዝናብ አበስብሶን እሳት ለመሞቅ ወደ ምድጃ ጠጋ ስንል “ተነስ ደሀ ትሆናለህ እሳት አትሙቅ” ተብየ ቁጣ ይደርስብኝ ነበር:: ቢፈቀድልን እንኳን ከምድጃው ጠጋ እንዳልን ጭሱ ወደ እኛ ሲመጣ “ተነስ አንተ ባለጌ መንገድ ላይ ሸንተሃል አይደል?” እባላለሁ:: በብዙ ማህበረሰባዊ እምነቶች መሐል ነው ያደግነው ማለት እችላለሁ::

አባቴ ወንድሜ በግ ለመሸጥ ገበያ ሲወስድ ያሰረበትን ገመድ በጉን ለገዛው ሰው ሰጥቶት በመምጣቱ ለምን ተቆጣ? ጥቁር በግ ለምን ይጠላል? ነጠላ ክንታት ዶሮ ለምን አይመረጥም? በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ሲጥል ለምንድን ነው ብረት ወደ ውጪ የሚጣለው? እናቴ ለምንድን ነው ስጦ ስታሰጣ ቢላዋ ስጦው ላይ የምታስቀምጠው? እንዲሁ የጠላ ድፍድፍ ያለበት ጋን ላይ ለምንድን ነው ብረት የምታስቀምጠው? በአካባቢያችን በውል የማንረዳቸው ልማዳዊ እምነቶች አሉ:: የሰው ልጆች ከመደበኛ ሃይማኖታቸው በተጨማሪ ሌሎች በማህበረሰቡ የተገነቡ በልምምድ ያደጉ እምነቶች አሉት:: አንድ ማህበረሰብ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚያሻግራቸው እና የሚፈጥራቸው ልማዳዊ ድርጊቶች አሉት:: እነዚህ ልማዳዊ ድርጊቶች አንድ ጊዜ ሲያድጉ፤ ሌላ ጊዜ ሲጠፉ ወይም ሲለወጡ ይስተዋላሉ፤ ባሉበት የቀጠሉም አሉ::

በፍቅር እስከ መቃብር ልብ ወለድ መጽሐፍ ውስጥ ፊታውራሪ መሸሻ  ባላገሮች ላይ  ረቡዕ ዕለት ለመዝመት ሲነሱ ወይዘሮ ጥሩ ወርቅ “እባክዎትን ረቡዕ ጦርነት አይቀናዎትም” ሲሉ ይደመጣሉ:: በዚህም ፊታውራሪው  አርብ እና ረቡዕ  አዳኞች እና ጦረኞች ዘመቻ ከወጡ አይቀናቸውም የሚለውን ማህበረሰባዊ እምነት ያምኑበት ስለነበር እሽ ይላሉ:: ወደ ጦርነት ለመሄድ ሌሊት በተኙበት ጊዜ ቀበሮ ሦስት ጊዜ ስታለቅስም “መጥፎ ምልኪ” ሆኖ በመቆጠሩ ውጊያውን አናሸንፍም ሲሉ በመጽሐፉ  ተጠቅሷል::

ጋዜጠኛና ደራሲ ታደሰ ጸጋ የመናፍስቱ መንደር፣ ግዞተኛው ጅኒ እና መናፍስቱ በሸለቆ ውስጥ በተሰኙት ተከታታይ መጽሐፍት ማህበረሰባዊ ልማዶችን በስፋት ተመልክቷል::

በሌሎችም መጽሐፍት ውስጥም ይሁን በሌሎች ጥናቶች ውስጥ ማህበረሰባዊ ልማዳዊ ድርጊቶች በብዛት ይገኛሉ:: ብዙዎቹ በጥናት አልተደገፉም እንጂ:: ዛሬ የተጠኑትን ለእናንተ እናደርሳለንለን::

ፀዳለ ታደሰ አዲስ በአበባ ዩኒቨርሲቲ የሂዩማኒቲ፣ የቋንቋዎች ጥናት፣ የጆርናሊዝምና የኮሚዩኒኬሽን ኮሌጅ የአማርኛ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍና የፎክሎር ትምህርት ክፍል ድኅረ ምረቃ መርኀ ግብር በቀይት ንዑስ ወረዳ የሚከወኑ ሀገረሰባዊ እምነቶች በሚል ርእስ ለአማርኛ ቋንቋ ሥነ ጸሑፍና ፎክሎር የኤም.ኤ ዲግሪ ማሟያነት ጥር 2007 ዓ.ም. ጥናት አቅርበዋል::

በዚህም ፈቃደ አዘዘን በመጥቀስ (ሀገረሰባዊ ባህል) የፎክሎርን የጥናት ዘርፎችን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች አስቀምጠዋቸዋል:: አራቱም ስነቃል፣ ሀገረሰባዊ ልማድ፣ ቁሳዊ ባህልና ሀገረሰባዊ ትውን ጥበባት በመባል ይታወቃሉ:: ዛሬ የምናስነብባችሁ ሀገረሰባዊ ዕምነት ከሀገረሰባዊ ልማድ ውስጥ የሚመደብ ነው::

በተመሳሳይ ሞላ ጀምበሬም በ2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሂዩማኒቲስ፣ ቋንቋዎች ጥናት፣ ጆርናሊዝምና ኮሚዩኒኬሽን ኮሌጅ የአማርኛ ቋንቋ፣ ሥነጽሐፍና ፎክሎር ትምህርት የድህረ ምረቃ መርኀ ግብር “የነውር እሳቤ በሊቦ ከምከም ወረዳ ማህበረሰብ እምነት” በሚል ጥናት አድርገዋል::

ሞላ ጀምበሬ “ልማዳዊ እምነቶች እራሳቸውን የቻለ እውቀቶች ሳይሆኑ እንደ አመለካከት ሂደት እና የእውቀት መንገድ የሚቆጠሩ፣ ብዙ ጊዜ ተጨባጭ የሆነ ሳይንሳዊና ሃይማኖታዊ ማስረጃ የማይቀርብባቸው፣ ተቀባይነታቸውም እምነቱ ባለበትና በሚፈፀምበት አካባቢ የሆነ እምነት መራሽ ልማዶች ናቸው” በማለት ይተረጉሙታል:: አንድ ማህበረሰብ በረጅም ዘመን የሕይወት ተሞክሮው ያዳበራቸው፣ የክስተቶችን መፈጠር ከጥሩ ወይም ከመጥፎ አጋጣሚዎች ጋር በማያያዝ የራሱን ማብራሪያ የሚያቀርብባቸው ዘልማዳዊ እምነቶች ናቸው በማለትም ያብራራሉ:: ነውር የሚለውን ቃል “የተከለከለ” በሚል ተቀራራቢ ትርጉም የሚሰጡት ሞላ ጀምበሬ “አንድ ህዝብ የሚመራባቸው መደበኛ የሆኑ ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ ሕጎች ከመፈጠራቸው በፊት ነውሮች እንደ ሕግ በመሆን አገልግለዋል” ይላሉ::

እንደ ሞላ ጀንበሬ ጥናት ነውሮች በአብዛኛው በአንድ ውስን አካባቢ ባህል የታጠሩ ሲሆኑ፤ የተወሰኑት ግን ለምሳሌ በዘመዳሞች መካከል የሚፈፀም የግብረ ስጋ ግንኙነት፣ ስርቆት፣ ሰው መግደል አይነት ድርጊቶች በአብዛኛው የዓለም አቀፋዊነት ባሕርይ የሚታይባቸው ናቸው::

ሞላ ጀምበሬ በዚሁ ጥናት ዶክተር ዋልተ ንጉሥ መኮንን ያደረጉትን ጥናት እንዲህ ጠቅሰውታል “በጨለማ ዋሽንት መንፋትም ሆነ ክራር መምታት፣ በክረምት ጋብቻ መፈፀም፣ ማዕድ ላይ ምንም ሳያስቀሩ ወይም ሳያስተርፉ መብላት፣ የከብትንም ሆነ የበግን የመጀመሪያ ግልገል ገበያ አውጥቶ መሸጥ፣ በግራ እጅ ማንኛውንም ስራ ማከናወን፣ ወዘተ. በማህበረሰቡ እምነት ነውር እንደሆነ አስፍረዋል:: ነውር የሆኑበት ምክንያትም የተጠቀሱት ነገሮች ለክፉ ዓይን አጋላጭ የሆኑ ክስተቶች ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው” በማለት ገልፀዋል:: በዚህም ጥናት ማህበረሰቡ የክፉ ዓይን ጥቃትን የሚከላከልባቸው በርካታ መንገዶች እንዳሉት ያነሱ ሲሆን ከመከላከያ መንገዶች መካከልም “የማህበረሰቡን ነውሮች ማክበር ነው” በማለት አንስተዋል::

በመጠኑ የምንቃኘው በሊቦ ከምከም ወረዳ ማህበረሰብ ነውሮች ላይ ያተኮረው የሞላ ጀምበሬ ጥናት  ነውሮችን የሚመለከቱ መረጃዎችን ከቤተ መጻሕፍት፣ ከመረጃ መረብና በዋነኛነትም ከመስክ በመሰብሰብ ተጠኝው ማህበረሰብ ስለእነሱ ምንነት ያለውን እሳቤ በተጠኝው ማህበረሰብ ዘንድ ተዘውታሪ የሆኑትን ነውሮችና የሚሰጡ ምክንያቶችን በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ሚና እና የማህበረሰቡን ፍልስፍና በማሳየት ረገድ ያላቸውን ቦታ መርምሯል::

 

… ይቀጥላል

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here