ክፍል ሁለት
በመጀመሪያው ክፍል “በልጅነቴ የሰማሁት አንድ አጋጣሚ ነበር” በሚል የጀመረው ትረካ፤ ጸሐፊው ተወልዶ ባደገበት አካባቢ የሚስተዋሉ ጎጅ ልማዳዊ የአምልኮ ድርጊቶችን አስነብቦናል። በሀገራችን አንዳንድ ደራሲያን የተፃፉ ልብ ወለዶችም ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችንም የገለጹበትን ሁኔታ አስገንዝቧል። የዚህ ቀጣይ ክፍልም እንደሚከተለው ቀርቧል።
ሊቦ ከምከም ወረዳ በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ ነው:: ተጠኝው ማህበረሰብ የተለያዩ ልማዲዊ እምነቶች ተከታይ ሲሆን ከነዚህም መካከል ከዛር፣ አድባር፣ ጥንቆላ፣ ቡዳ፣ ተፈጥሮን መቆጣጠር፣ ሞት፣ በሽታን ከማባረርና ከማሸጋገር ጋር የተያያዙ እምነት መራሽ ልማዶች ጥቂቶቹ ናቸው::
“የምግብ ዓይነት ምርጫና ተያያዥ ነውሮች እውቀት፣ ልምድና ትግበራ” በሚል ምእራፍ በቀረበው ጥናት፤ ጥናቱ የተደረገበት ማህበረሰብ የጤና መታወክን የሚያስከትሉ ምግቦችን እንዴት እንደሚመለከት ተብራርቷል::
ተልባ
ፍሬው ቅባትነት ያለው እህል ነው:: ተልባ በሚቆላበት፣ በሚወቀጥበትና በሚበላበት ጊዜ ሽታው ከፍተኛ ነው:: ስለሆነም በተጠኝው ማህበረሰብ ዘንድ የተልባ ሽታ እርኩስ መንፈስን የመጥራት ኀይል አለው ተብሎ ይታመናል:: በማህበረሰቡ እምነት ተልባ የእርኩስ መንፈስ ማደሪያ ነው:: በዚህ ባህሪው ምክንያትም ትምህርት እንዲገባ፣ ጠላት እንዳያጠቃ በሚል ድግምት ያሰሩ ሰዎች፤ በአንድ ወቅት በቡዳ መንፈስ ተይዘው የዳኑ ሰዎች፣ የበረድ ደጋሚዎች በእድሜ ዘመናቸው ሁሉ ተልባን አይመገቡም:: ምክንያቱም ተልባ ድግምትን የመሻር፣ የዳነ ሕመምን የመቀስቀስ፣ በሽታን የመደበቅ ኀይል ስላለው ድግምት ያሰሩ ሰዎች እሱን ከበሉ የተደረገላቸው ድግምት አይሰራም:: በአንድ ወቅት በቡዳ መንፈስ ተይዘው የዳኑ ሰዎች ከተመገቡትም ይዟቸው የነበረው የቡዳ መንፈስ ተመልሶ ይይዛቸዋል:: ተልባን በጊዜያዊነት የሚከለከሉ የማህበረሰቡ አባላትም አሉ:: ሰዎች በቡዳ መንፈስ መያዛቸው ከታወቀ “መንፈሱ ከታማሚዎቹ ለቆ እስኪወጣ” ድረስ በመንፈሱ የታመሙት ሰዎች ተልባ እንዲበሉ አይፈቀድም:: ምክንያቱም ተልባ ከበሉ የያዛቸው የቡዳ መንፈስ ይደበቃል፣ ያደፍጣል፣ ታማሚዎቹ እንዳይለፈልፉ አፋቸውን ይዘጋቸዋል ተብሎ ይታመናል::
ራስ ምላስ
ራስ ምላስ ለሴት ልጅ የማይፈቀድ የስጋ ምግብ ዓይነት ነው:: የአካባቢው ማህበረሰብ “ምላስ” የሚለውን ቃል “ምላሰኛ”፣ “ለፍላፊ” እና “ተናጋሪ” በሚል እሳቤ ይተረጉመዋል:: ስለዚህ ራስ ምላስን መብላት “ምላሰኛ”፣ “ለፍላፊ” እና “ተናጋሪ” ያያደርጋል ብሎ ያምናል:: በማህበረሰቡ ውስጥ ሴቶች በተፈጥሯቸው ምላሰኛ፣ ለፍላፊ እና ምስጢር የማይጠብቁ ተደርገው ይታሰባሉ:: ስለሆነም ሴቶች ምላስ ከበሉ የበለጠ ለፍላፊ ይሆናሉ ተብሎ ስለሚታመን እሱን እንዲበሉ የአካባቢው ልማድ አይፈቅዳላቸውም:: ሴት ልጅ አድማጭ እንጅ ተናጋሪ እንድትሆን አይፈለግም:: ጥሩ ምግባር ያላት ሴት ዋናው መመዘኛዋ ዝምተኛነቷ ነው:: በጥናቱ መረጃ ሰጪዎች እሳቤ መሰረት ሴት ልጅ ራስ ምላስ ከበላች ጥሩ የተባለ ምግባሯን ታጣለች፣ ምላሳም ስለምትሆን ባሏንም ሆነ የአካባቢውን ማህበረሰብ ትዳፈራለች:: ስለሆነም ለሴቶች ራስ ምላስ የተከለከለ ሲሆን፤ ክልከላውን መጣስም ጥሰቱን በፈፀሙት ሴቶች ላይ አዲስ የትዳር አጋር ማጣትን፣ ይዘውት ከቆዩት ትዳርም ፍችን ያስከትላል::
በወተት እና እርጎ በልቶ እጅን መታጠብ
በተጠኝው ማህበረሰብ ውስጥ ወተት እና እርጎን (የላም ልጆችም ይሏቸዋል) ተጠቅሞ እጅን መታጠብ የእነሱ ምንጭ የሆነችው ላም እንድትነጥፍ፣ እንድትደርቅ ያደርጋል:: እንድትነጥፍ እና እንድትደርቅ ብቻ ሳይሆን እስከመጨረሻው እንዳትወልድም ያደርጋል ተብሎ ይታመናል:: ይህን በሚመለከት መረጃ ሰጪው አቶ ሙለቀን ዘውዴ ለአጥኚው የሚከተለውን መረጃ ነግረውታል::
“በወንዞች አካባቢ የሚገኝ አባ ወርቄ የሚባል ጅን (ሰይጣን) አለ:: ይህ ጅን ወተት ነገሮችን ስለሚወድና የላሞችን ወተት ስለሚጠጣ ላሞች ባሉበት አካባቢ አይጠፋም:: በመሆኑም ሰዎች በወተትና እርጎ በልተው እጃቸውን በውኃ ሲታጠቡ ይበሳጫል:: በዚህ ምክንያትም የላሟን ወተት በመስለብ ወይም በመውሰድ ድርጊቱን የፈፀሙትን ሰዎች ይቀጣቸዋል” ተብሎ ይታመናል::
አቶ አለበል ደሴ የተባሉት መረጃ ሰጭ ለአጥኚው እንደነገሩት በማህበረሰቡ ውስጥ ከላሞች አካባቢ አይጠፋም የሚባለውና አባ ወርቄ የሚል ስም የተሰጠው ጅን በወተት እና እርጎ በልቶ እጅን መታጠብ ብቻ ሳይሆን የሰዎች ጩኸትና ድምጽም ይረብሸዋል:: በመሆኑም በአካባቢው ሰዎች ላም እያለቡ ድምጽ አያሰሙም:: ድምጽ ካሰሙ በሁኔታው በመበሳጨት የላሞችን ወተት ይወስዳል ተብል ይታሰባል:: በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ይህ ጅን ከብት አርቢ እንደሆነ፣ የጅን ውላጅ (ድቅልም) እንደሚባዛ ወይም እንደሚራባ ይታመናል:: በመሆኑም የአካባቢው ማህበረሰብ ከጅን ጋር ለማዳቀል በአካባቢው አባ ወርቄ የሚባለው ጅን አለ ተብሎ በሚታመንበት ወንዝ አካባቢ ላሞቹን ያሳድራል:: ስለሆነም በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ላም ትልቅ ክብር እንዳላት ሁሉ የእሷ ውጤቶች የሆኑት ወተት እና እርጎም የተከበሩ ናቸው::
የባለዛር የተባሉ ነገሮችን መመገብ
በማህበረሰቡ ውስጥ ዛር የሰፈረባቸው ሰዎች ለዛር መንፈሳቸው ማረፊያ እና መለማመኛ በሚል በዋናነት የቤት እንስሳትን ለይቶ ማስቀመጥ የተለመደ ነው:: ከእንስሳቱ መካከልም ዶሮ እና በግ ይጠቀሳሉ:: ስለሆነም ለባለዛሮች ተብለው የተለዩ እንስሳትን ከእነሱ ውጭ የሆነ ሰው መብላት አይችልም:: ምክንያቱም የእነሱ የተባሉ ነገሮችን መመገብ የዛር መንፈሱ ተቆጥቶ ወደ ተመገቡት ሰዎች እንዲተላለፍ ያደርጋል፣ በተመጋቢዎቹ ላይ ያልተገመተ በሽታን ያመጣል ተብሎ ይታመናል::
የባለዛር ተብለው የተለዩ እንስሳትን ባለዛሮቹ እያራቡና እየሸጡ በገንዘቡ ራሳቸው ይጠቀሙበታል፤ ብዙ የተለመደ ባይሆንም ለእነሱ የተባለ እንስሳትን እራሳቸው ብቻ (በተለይም ዶሮንና እንቁላልን) ይበላሉ:: ስለሆነም በተጠኝ ማህበረሰብ ውስጥ የባለዛር የተባሉ ነገሮችን መመገብ የተከለከለ ተግባር ነው::
ሴት ልጅ ወደ ቀብር ቦታ መቅረብ
በማህበረሰቡ ውስጥ ሴት ልጅ በተፈጥሮዋ አንጀቷ ስስና ሩህሩህ፣ በቀላሉ የምትደሰትና በቀላሉም የምትከፋ፣ ሃዘንን በቀላሉ ለመርሳት የምትቸገር ተደርጋ ትታሰባለች:: በዚህ ባህሪዋ መነሻነትም ሴት ልጅ በቀብር ጊዜ ያየችውን ሟች በቀላሉ ስለማትረሳ በአዕምሮዋ እየታወሳት የአዕምሮ በሽተኛ ልትሆን ትችላለች ተብሎ ይታመናል:: በዚህ ምክንያትም በተለይም ቅርብ ቤተሰብ የሞተባት ሴት የቀብር ስነስርዓቱ ተጠናቆ አፈር የመርጨት ጊዜው ከመድረሱ በፊት ወደ ቀብር ስፍራው እንድትቀርብ በፍፁም አይፈቀድም:: በማህበረሰቡ ውስጥ ሴት ልጅ ወደ ቀብር ስፍራ እንዳትቀርብ ጥብቅ የሆነ ክልከላ የሚደረግበትን ምክንያት አስመልክቶ የሚነገር አንድ አፈ ታሪክ አለ:: አፈ ታሪኩም የሚከተለው ነው::
በድሮ ጊዜ አንዲት ሴት በጣም የምትወደው አንድ ልጇ ይሞትባታል:: ከዚያም ወደ ቀብር ቦታ ትሄድ እና ልጇ ሲቀበር ትመለከታለች:: ባየችው ነገርም በጣም ከማዘኗ የተነሳ ራሷን ስታ በሰዎች ድጋፍ ወደቤቷ ትመለሳለች:: ሆኖም ግን ሲቀበር ያየችው ነገር ራሷን ለመቆጣጠር ስላላስቻላት በነጋታው ሌሊት ተነስታ ወደ ልጇ የቀብር ቦታ በመሄድ አውጥታ ወደ ቤቷ ይዛው ተመለሰች:: ከዚህ አፈ ታሪክ በመነሳትም ይመስላል ሴት ልጅ ወደ ቀብር ስፍራ እንዳትጠጋ የተከለከለው::
በእርሻ ቦታ ላይ ዱላ መትከል/ ማቆም
በማህበረሰቡ ውስጥ አንድ ሰው እያረሰ እያለ የሚታረሰው የእርሻ ቦታ ውስጥ እራሱም ሆነ ሌላ ሰው ዱላ መትከል ወይም ማቆም አራሹ ብዙ እንዳያርስ፣ ሥራው እንዳይቀናው፣ አራሹም ሆነ የሚታረሱት በሬዎች እንዲደክሙ ያደርጋል ተብል ይታመናል:: የአካባቢው አርሶ አደሮችም በዚህ ስለሚያምኑ በእርሻ ሥራ ላይ እያሉ ሌላ ሰው ባይመጣባቸው ይመርጣሉ:: ሌላ ሰው ከመጣም ቢያንስ ግን የመጣው ሰው ዱላውን የሚታረሰው መሬት ላይ እንዳያቆም ጥንቃቄ ያደርጋል:: አንድ አርሶ አደር እያረሰ እያለ ሌላ ሰው መጥቶ ስለሁኔታው ካለማወቅም ሆነ በመርሳት ዱላውን ከሚታረሰው መሬት ላይ ተክሎ ቢቆም የሚያርሰው ሰው “ይሄን ከፊቴ አቁመህ ገትረኸኝ ልትውል ነው… እንኳን አቁመኸው እንዲያውም ቆሞብኛል (እርሻው አልገፋ ብሎኛል ለማለት ነው)” ይለዋል:: በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ዱላ ያቆመው ሰውም ለአራሹ ይቅርታ ይጠይቃል – ያቆመውን ዱላም ነቅሎ መሬት ላይ ያጋድማል ወይም በትከሻው ይይዛል:: ስለሆነም በማህበረሰቡ እምነት ዱላን የእርሻ ቦታ ላይ መትከል የእርሻ ሥራው ቀና እንዳይሆን፣ አራሹም ሆነ የእርሻ በሬዎቹ የድካም ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ድርጊት ነው::
በቡዳ መንፈስ ተበልቶ የሞተ ሰውን በጥይት ሳይመቱ መቅበር
በማህበረሰቡ ውስጥ አንድ ሰው በቡዳ መንፈስ ተበልቶ ከሞተ የበሉት ቡዳዎች ከመቃብር አውጥተው ልቡን በመስለብ ሲፈልጉ የቤት ቁሳቁስ፣ ሲፈልጉም ሰው ያደርጉታል ተብሎ ይታሰባል:: በለበቅ ወይም ልምጭ በትንሹ መታ ሲያደርጉት የሞተው ሰው ተነስቶ ያዘዙትን ማንኛውንም የቤት ውስጥም ሆነ የውጭ ሥራ ያከናውናል:: የቡዳ መንፈሱ ካለባቸው ሰዎች ውጭ የሆነ ሰው ግን ሟቹን ሊያየውና ሊለየው አይችልም::
ስለሆነም ቡዳዎች ከመቃብር አውጥተው አገልጋያቸው እንዳያደርጉትና በዚህም የሟቹ መንፈስ በቤተሰቡ ላይ ቅር እንዳይሰኝ በሚል በአካባቢው አንድ ሰው በቡዳ ተበልቶ መሞቱ ከተረጋገጠ በጀርባው በጥይት ሳይመታ አይቀበርም:: ከመቃብር አውጥተው አገልጋያቸው የሚያደርጉትና የሚያዝዙት በልቡ አማካይነት ስለሆነ በጀርባው በጥይት ተመትቶ ልቡና መሰል የሰውነት አካሉ እንዲጎድል፣ እንዲበላሽ ይደረጋል:: በጀርባው መምታት የተመረጠው ልብ ያለው ከፊት ስለሆነና ጥይት ደግሞ ጉዳት የሚያደርሰው በሚገባበት በኩል ሳይሆን በሚወጣበት በኩል ስለሆነ ነው::
በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ጥይት መተኮስ ስለተከለከለ፣ የጥይት ዋጋም ስለጨመረ በጥይት ሳይመቱ መቅበር እየተለመደ ነው:: ሆኖም የሟች ቤተሰብ ቢያንስ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ያህል (ማታ ማታ) መቃብሩን ይጠብቃል:: በማህበረሰቡ አስተሳሰብ የአንድ ሰው ልቡ የሚፈርሰው በሞተ በሰባተኛ ቀኑ ነው:: ስለሆነም ቤተሰቡ እስከ ሰባት ቀናት ድረስ ከጠበቀ የሟቹ ልብ ስለሚፈርስ፤ ልቡ ከፈረሰ ደግሞ ለቡዳዎችም ስለማይሠራላቸው አያወጡትም ተብሎ ይታሰባል::
በተጠኝው ማህበረሰብ ዘንድ ነውር የሚለው እሳቤ ራስን፣ ቤተሰብንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ከጉዳት ለመጠበቅ ሲባል በሰዎች ላይ የሚጣል ክልከላ ነው የሚል ፍች የያዘ ነው:: በመሆኑም ማህበረሰቡ አካባቢያዊ ልማድን መነሻ አድርጎ በአካባቢው የሚገኙትን ነገሮች ሁሉ ነውር የሆኑና ያልሆኑ በሚል በሁለት እንደሚፈርጃቸው በጥናቱ ተመላክቷል::
ነውሮች ተጠኝው ማህበረሰብ የአባላቱን እምነትና ባህሪ የሚቀርፅባቸው፣ ስጋዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቹን ለማርካት የሚያስችለውን እውቀትና ክሂል የሚያስታጥቅባቸው፣ የአባላቱን አስተሳስብ፣ ስሜትና ባህርይ የሚገዛባቸው ወይም የሚወስንባቸው እና በአጠቃላይም ለአኗኗሩ መርህ፣ ለግንኙነቱ ደንብ እና ሕግ አድርጎ የሚገለገልባቸው ናቸው ይላሉ ሞላ ጀምበሩ:: በመሆኑም ማህበረሰቡ ነውሮችን ያለ አንዳች ምክንያት አይፈጥራቸውም፤ ከዚህ ተነስቶም አዎንታዊ እንጅ አለታዊ ገፅታ ይኖራቸዋል የሚል እምነትም የለውም:: አሉታዊ ገፅታ ይኖራቸዋል ብሎም አያምንም፤ ይህ ሲባል ግን ሁሉም ነውሮች አዎንታዊ ሚና ብቻ ያላቸው ናቸው ለማለት አይቻልም:: በትንተናው የተገኙ የጥናቱ ውጤቶች እንደሚያሳዩት የማህበረሰቡ ነውሮች አዎንታዊም አሉታዊም ሚና ያላቸው ናቸው በማለት ሞላ ጀምበሬ በጥናቱ አስፍሯል::
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም