ነዳጅ አላቢዎች

0
293

በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ከሰሞኑ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት ችግር አጋጥሟል:: ምናልባትም ችግሩ ከክልሉ የሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ወደ ክልሉ የመግባት ሥጋት አድሮባቸው ይሆናል፤ ምናልባትም ደግሞ የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመጨመሩ ነዳጅን እንደልብ ማግኘት ባለመቻሉም ይሆናል::

በነዚህ መሰረታዊ ችግሮች ምክንያት በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ እና በሌሎችም የክልሉ ከተሞች የነዳጅ እጥረት  የመፈጠሩ አሳሳቢነት እንዳለ ሆኖ፣ ችግሩን እንደመልካም አጋጣሚ በሚቆጥሩ አሽከርካሪዎች ምክንያት ግን ኅብረተሰቡ በእጅጉ እየተሰቃየ ይገኛል::

ለአብነት በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታክሲዎች እና ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) “ነዳጅ የለም” በሚል ምክንያት የራሳቸውን ታሪፍ እስከማውጣት ደርሰዋል:: እነዚህ አሽከርካሪዎች በራሳቸው ፍላጐት ከጨመሩት ታሪፍ በተጨማሪ 11 ሰው በሚይዝ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ከ18 እስከ 20 ሰው በመጫን በኅብረተሰቡ የኑሮ ውድነት ስቃይ ላይ የራሳቸውን ቤንዚል እያርከፈከፉበት ይገኛሉ::

ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እና በተለምዶ ‘ዳማስ’ እየተባሉ የሚጠሩት ተሽከርካሪዎችም በከተማው መንገድ እና ትራንስፖርት የአምስት ብር ታሪፍ የወጣላቸውን አጫጭር መንገዶች 10፣15 እና መሸት ሲል ደግሞ 20 ብር በማስከፈል የኅብረተሰቡን የኑሮ ውድነት ምሬት ከፍ እንዲል እያደረጉት ይገኛሉ::

የከተማዋ ነዋሪዎች ታክሲዎች ነዳጅ በማጣት የሚያባክኑትን የሥራ ጊዜ ግምት ውስጥ በማስገባት በትርፍ ተጭኖ መሄድን ተለማምደዋል፤ ያም ብቻ ሳይሆን የሁለት እና የሦስት ብር መልስ የነበራቸውን አጫጭር ‘ፌርማታዎች’ መልስ ባለመቀበል አሽከርካሪዎቹን እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶችን ለማገዝ ጥረት ሲያደርጉ አስተውያለሁ::

ችግሩ ያለው የኅብረተሰቡን ሀዘኔታ እና ውለታ በሞኝነት የቆጠሩት አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው ጋር ነው:: አሥራ አንድ ሰው በሚይዝ ታኪሲ ውስጥ 18 ሰው ተጨናንቆ መሄድ (በባሕር ዳር ሙቀት) ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ የሚገነዘበው እንደኛ አዘውትሮ ታክሲን የሚጠቀም ሰው ነው:: የሁለት እና የሦስት ብር መልስም ተጠራቅሞ አንዲት ትንሽዬ ቀዳዳን እንደሚደፍን ይታወቃል::

አሁን በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በባለ ታክሲዎች ተጨምሮ የሚገኘው የታክሲ ታሪፍ ወደፊት የነዳጅ እጥረቱ መፍትሔ ሲያገኝም እንዳይቀጥል ሥጋታችን ነው:: ይህ ሲሆን ደግሞ ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚ እና ሕግ አስፈፃሚ የሚባሉት የመንግሥት አካላት ሚና ላይ አመኔታ ይታጣል:: ይህ በመሆኑ የከተማዋ ትራፊክ ፖሊሶች እና የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ማሳሰብ እወዳለሁ::

ከዚሁ የነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በስፋት እየታየ ያለው ጉዳይ ደግሞ ነዳጅ አላቢነት ነው:: “ነዳጅ እንዴት ይታለባል?” የምትሉ አንባቢዎች ካላችሁ ጉዳዩን በገባኝ ልክ ላስረዳችሁ እሞክራለሁ:: ባሕር ዳር ውስጥ ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች ነዳጅ በብዛት አይገኝም፤ ነዳጅ ከገባላቸው ማደያዎች ነዳጅ ለመቅዳት ያለው ወረፋም በጣም የበዛ እና አስቸጋሪ እንደሆነ  እያየን ነው::

ይሄንኑ አጋጣሚ ለዘረፋ የሚጠቀሙበት ባለ ተሽከርካሪዎች መኖራቸው ደግሞ ነዳጅ በወጣለት ዋጋ ከመግዛት ይልቅ ያለወረፋ በጥቁር ገበያ እና በውድ ዋጋ የሚገዙ አሽከርካሪዎችን ፈጥሯል:: በርከት ያሉ ባለ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ከመጣበት ማደያ ሁሉ ወረፋቸውን ጠብቀው ነዳጅ ይቀዳሉ፤ ይሄ የሚያስገርም ጉዳይ አይደለም:: አስገራሚው ነገር ከማደያዎች በተሽከርካሪያቸው የሚሞሉት ነዳጅ ለትራንስፓርት አገልግሎት የማይውል መሆኑ ነው::

እነዚህ ባለ ተሽከርካሪዎች ከየማደያዎቹ ወረፋ ይዘው ነዳጅ የሚቀዱት ለታክሲ ወይም ለሌላ የትራንስፓርት ሥራ ሳይሆን ነዳጁን ከመኪናቸው ውሰጥ እያለቡ ለመሸጥ ነው:: መኪናቸውን እንደ ሆላንድ ላሞች በመቁጠር ከማደያ የቀዱትን ነዳጅ መልሰው እያለቡ በጥቁር ገበያ ይቸበችቡታል:: በዚህ የወንጀል ሥራቸው የሚያተርፉት ብዙ ነገር ነው::

የመጀመሪያው ትርፋቸው ከነዳጅ ማደያዎች በመንግሥት የነዳጅ ተመን የገዙትን ነደጅ በጥቁር ገበያ ከእጥፍ በላይ ትርፍ የሚያገኙበት መሆኑ ነው:: በሌላ መንገድ ደግሞ እነዚህ ታክሲዎች ነዳጅ ከማደያ እየቀዱ መሸጥ እንጂ በታክሲ ሥራ ላይ ስለማይሰማሩ የታክሲዎቻቸው ጐማ እና ሌሎችም ዕቃዎች የሚያልቁ አይሆኑም::

ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የታክሲዎች እጥረት ያጋጠመንም ቢሆን ከነዳጅ እጥረቱ ጋር በተያያዘ ብቻ አይመስለኝም:: ታክሲዎች ከየማደያዎቹ ወረፋ ጠብቀው ነዳጅ ከቀዱ በኋላ፣ ያንን ነዳጅ ከታክሲያቸው ውስጥ እያለቡ በመሸጥ እነሱ ሥራ ላይ የማይሰማሩ ከሆነ የታክሲ እጥረት ማጋጠሙ የግድ ይሆናል::

ይሄው የነዳጅ ማለብ ተግባር በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ለሚታየው የታክሲ ዋጋ መወደድ ቀዳሚው ምክንያትም ነው:: ይሄንን እውነታ በአብነት ለማስረዳት ያህል፣ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) ከነዳጅ ማደያዎች ወረፋ ጠብቀው የሚቀዱት የነዳጅ መጠን ስምንት ሊትር ብቻ ነው:: ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የባጃጆቹ የነዳጅ መያዣ ታንከሮች የሚይዙት ይህንኑ ያህል ነዳጅ ብቻ በመሆኑ ነው::

ቀኑን ሙሉ ወረፋ ጠብቆ ስምንት ሊትር ነዳጅ ከመቅዳት ይልቅ ከነዳጅ አላቢዎች ላይ በጥቁር ገበያ ሁለት ሊትር ቤንዚል በ350 ብር ገዝተው ኅብረተሰቡ ወይም የታክሲ ተጠቃሚው ላይ ታሪፍ በመጨመር የታክሲ ሥራቸውን ሲሰሩ የሚውሉት በርካቶች ናቸው:: እነዚህ ባለ ባጃጆች የነዳጅ ዋጋ ሳይጨምር እነሱ ለምን ታሪፍ እንደሚጨምሩ ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ “ቤንዚሉን የቀዳነው ከጥቁር ገበያ ነው” የሚል ነው::በነገራችን ላይ ከማደያዎች የአንድ ሊትር ቤንዚል ዋጋ 77 ብር ከ80 ሳንቲም መሆኑን ልብ ይሏል::

በባሕር ዳር የበዛው የታክሲ ወረፋ ለሌቦችም  ትልቅ የገቢ ምንጭ ሆኗቸዋል። በታክሲ ወረፋ ስም ከእውነተኛ ተሳፋሪዎች ጋር እየተጋፉ የብዙዎቻችንን ኪሶች እና ቦርሳዎች የራሳቸው ኪስ እና ቦርሳ አድርገውብናል::

ለባሕር ዳር ከተማ የታክሲዎች እጥረት እና የታሪፍ መጨመር ምክንያት ከሆኑት ነገሮች ውስጥ ጥቂቶቹን ለመጠቆም ሞክሬያለሁ:: ጉዳዩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመለከታችሁ አካላት ደግሞ ችግሩን ከሥር መሰረቱ በማስወገድ ወይም በማርገብ ሥራ ላይ እንድትሰማሩ ሃሳቤን አጋርቻለሁ:: የኅብረተሰቡ የኑሮ ውድነት ሁለንተናዊ እንዳይሆንም ሁሉም የየድረሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ::

ከሰሞኑ ደግሞ ለባለ አሽከርካሪዎች የነዳጅ ድጐማን የተመለከቱ የስልክ ጥሪዎች ካልታወቁ ሰዎች እየተላኩላቸው መሆኑንም ሰምቻለሁ:: እነዚህ ደዋዮች የባለ አሽከርካሪዎችን ስልክ በተለያየ መንገድ በመፈለግ ይደውሉ እና የደወሉት ከትራንስፓርት ቢሮ መሆኑን ገልፀው በቅርቡ የመቶ በመቶ የነዳጅ ድጐማ ተጠቃሚ እንደሚሆን ከምሥራች ጋር ይገልጹለታል:: ለዚህ አሠራር ያመች ዘንድም ባለ መኪናው ‘አካውንቱን’ ቀድሞ እንዲያሳውቅ ይነገረዋል::

በዚህ ዓይነት የማጭበርበሪያ ዘዴ የሰዎችን የቁጠባ ሂሳብ የሚበረብሩ ወይም የሚነድፉ ሌባዎች እየተፈጠሩ ነውና ባለ ተሽከርካሪዎች ከወዲሁ ጥንቃቄ እንድታደርጉም ምክር አለኝ:: ባንክ ቤቶችም ደንበኞች እንደነዚህ ካሉ ዘራፊዋች የሚጠበቁባቸውን አሠራሮች በማበጀት ችግሩ ሥር ሳይሰድ መፍትሔ ቢፈለግለትም እላለሁ::

ነዳጅ አላቢዎች ሆይ! የሀገር እና የኅብረተሰብን ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ ከመውሰድ ይልቅ፣ ሀገር እና ሕዝብ ከችግር በሚወጡበት ተግባር ላይ የድርሻችሁን ጠጠር ብትጥሉ ይሻላችኋል:: በእናንተ ስግብግብነት እና ለሕዝብ ችግር ቦታ ነፋጊነት ምክንያት መንግሥት ብቻውን የቅሬታ ባለቤት ይሆናል ብላችሁ ማሰቡም ስህተት ነው:: ስህተትን አርሞ ለሕዝብ ችግር የመፍትሔ አካል መሆን ደግሞ ከምንም በላይ አዋቂነት ነው:: እኔ ይሄንን አልኩ፤ እናንተስ? ሃሳብ እና አስተያየታችሁን ለበኲር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ማድረስ ትችላላችሁ፤ ፈጣሪ ለሀገራችን ሰላምን ያድልልን!!

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here