የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል እና የማቋረጥ ምጣኔን ለመቀነስ የሚኖረውን አበርክቶ በተመለከተ በ2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማን መሠረት አድርጎ አንድ ጥናት ተሠርቶ ነበር:: ጥናቱ እንዳመላከተው በታዳጊ ሀገራት በየዕለቱ 60 ሚሊዮን ተማሪዎች ሳይመገቡ ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ፤ ትምህርታቸውን የሚከታተሉትም ከረሃብ ጋር እየታገሉ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በምግብ እጦት እና ተያያዥ ምክንያቶች 58 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ስለመሆናቸው ነው ጥናቱ የሚያሳየው። ይህ ደግሞ ማኅበረሰቡ ለትምህርት ትኩረት እንዳይሰጥ ያደርገዋል፤ የትምህርት ጥራትንም በእጅጉ ያጓድላል::
ጥናቱ ለተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆን እና የማቋረጥ ምጣኔ ሁለተኛ ምክንያት ነው ብሎ ያስቀመጠው ምጣኔ ሀብታዊ ችግርን ነው። ይህም ወላጆች ልጆቻቸውን በአግባቡ መመገብ እና አስፈላጊውን የትምህርት ቁሳቁስ አሟልተው መላክ እንዳይችሉ በማድረግ አሉታዊ ተጽዕኖን ይፈጥራል።
በኢትዮጵያም በአብዛኛዎቹ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች አስፈላጊው መሠረታዊ ፍላጎት (ምግብ እና የትምህርት ቁሳቁስ) ሳይሟላላቸው እንደሆነ ጥናቱ ጠቁሟል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሀገራት ረሀብን እና ረሀብን ተከትለው በሚመጡ በሽታዎች ተማሪዎች እንዳይጎዱ፣ የተማሪዎችን የማስታወስ አቅም በማሳደግ ብቁ ለማድረግ ለተማሪ ምገባ ትኩረት ሰጥተዋል።
በሀገራችን የተማሪ ምገባ እንደ ሀገር ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፤ የአማራ ክልልም ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል:: በዚህ ዓመትም በትምህርት ቤቶች እየተተገበረ ይገኛል፤ ለአብነትም በኮምቦልቻ እና በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደሮች ያለውን ምገባ በተለያዩ ጊዜያት አስነብበናችኋል::
ሌሎችም በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና የፈጠራ አቅማቸው ከፍ ያሉ ልጆችን ማፍራት የሚቻለው ከታች መሥራት ሲቻል መሆኑን ተገንዝበው የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባን እያስጀመሩ ነው::
በክልሉ የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባን ካስጀመሩ አካባቢዎች መካከል የጎንደር የከተማ አስተዳደር ይገኝበታል:: ከተማ አስተዳደሩ በትምህርት ዘመኑ 40 ሺህ ተማሪዎችን ለመመገብ የሚያስችል መርሀ ግብርን በአየር ጤና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስጀምሯል።
በምገባው ከአንድ ሺህ በላይ የቅድመ እና አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ሳሙኤል አታላይ ተናግረዋል። ርእሰ መምህሩ እንዳሉት ማኅበረሰቡ ለምገባ ቁሳቁስ ማሟያ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል። ይህም ትውልድ ግንባታ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑ የተረጋገጠበት እንደሆነ ያሳዬ ተግባር ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ትምህርት ባለሙያ አቶ ሚዛኑ ነቅሎ የምገባ መርሃ ግብሩ በ44 ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው ያስታወቁት። ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ፣ የማቋረጥ ምጣኔን በመቀነስ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ የምዕራብ ጎጃም ዞን መናገሻዋ ፍኖተ ሰላም ከተማም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታለች:: አንድም ተማሪ በምግብ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ አይሆንም በሚል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ነው ከተማ አስተዳደሩ ያስታወቀው፤ በተጨማሪም ተማሪዎች ከራዕያቸው እንዳይሰናከሉ ምገባው መጀመሩ ተጠቁሟል::
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ታደሰ እንደተናገሩት በትምህርት ዘመኑ 650 ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የትምህርት ቤት ምገባ ተጀምሯል፤ ለዚህም ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል። ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ እና ጅምሩን ለማስፋት ደግሞ የማኅበረሰቡ እና የአጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በማንሳት “እገዛችሁ አይለየን” ብለዋል።
ሌላው ለተማሪ ምገባ ትኩረት በመስጠት እየሠራ የሚገኘው ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነው። ምገባው ከአሁን ቀደም በወልቃይት እና በቃብትያ ሁመራ ወረዳ ባሉ ትምህርት ቤቶች የተጀመረ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ የሁመራ ከተማ አስተዳደር አስጀምሯል።
የከተማ አስተዳደሩ ትምርት ጽ/ቤት እንዳስታወቀው ምገባው በአምስት ትምህርት ቤቶች ነው የተጀመረው። የሕብረት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ ምገባው ከተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል ነው። የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ወይዘሮ የሻለም አየሁ የምገባ ፕሮግራሙ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወላጆች ከፍተኛ እገዛ መሆኑን አስታውቀዋል።
እንደ ርእሰ መምህሯ ማብራሪያ ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ አካላዊ እና አዕምሯዊ ዕድገታቸው የተስተካከለ እንዲሆን ያስችላል። የትምህርት አቀባበላቸውን በማሻሻል ተወዳዳሪ ያደርጋል።
የሰቲት ሁመራ ከተማ አስተዳደር ተወካይ ከንቲባ እና የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ታደለ ለምገባው አምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ነው የተጀመረው። በአምስት ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የምገባ ፕሮግራሙ 727 ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል።
ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ ከማድረግ ባለፈ የተለያየ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ተማሪዎች የበታችነት ስሜት ያስቀራል:: በእኩልነት ስሜት ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩም ያደርጋል።
ምገባው ዓመቱን ሙሉ እንዲዘልቅ ታሳቢ ተደርጎ መጀመሩንም አቶ ተስፋሁን አስታውቀዋል።
ለምገባው ቀጣይነት ሁሉም ተሳትፎ እንዲያደርግ ተጠይቋል:: ሌሎችም ተሞክሮውን በመውሰድ የምገባ ፕሮግራሙን እንዲያስጀምሩ ተመላክቷል::
በክልሉ ድርቅ እና እርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች የተጀመረው የተማሪ ምገባ ከዐሥር ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ የአማራ ክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመለክታል:: የምገባ ፕሮግራሙ እንደ ክልል በተደራጀ መንገድ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነም መረጃው ጠቁሟል::
ምገባ የተማሪዎችን ከትምህርት ቤት የመቅረት እና የማቋረጥ ምጣኔን ይቀንሳል፤ የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል በእጅጉ ያሻሽላል:: ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ በሁሉም ነገር የበቃ ዜጋን ለመፍጠር ያስችላል፤ ብቁ ዜጋ ደግሞ የሀገር የሁሉም ነገር መሠረት ይሆናል።
በ2018 የትምህርት ዘመን በክልሉ ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን በትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ ቢሮው አቅዷል። ለፕሮግራሙም 500 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡ ታውቋል፤ የትምህርት ቤት ምገባን እንደ አንድ የትምህርት ግብዓት በመውሰድ ማኅበረሰቡ፣ ባለሃብቶች እና ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።
ግዕዝ በአማርኛ
መኑ- ማን
እሉ – እኒህ
ኩሉ – ኹሉ
ዝንቱ – ይህ
እሙንቱ – እነሱ
ዛቲ – ይህች
እንታክቲ – ያች
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


