የመማር ማስተማሩ ሂደት የተለያዩ ችግሮች ተጋርጠውበት ይገኛል፡፡ ከችግሮቹ ደግሞ ግጭቶች በግምባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በግጭቶችና ተያያዥ ችግሮች በኢትዮጵያ ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዜጎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ደግሞ የዚህ ችግር ግምባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ሆኖ ይገኛል፡፡ በትምሀርት ገበታቸው መገኘት ካልቻሉት ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዜጎች ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡
ግጭቶች መፍትሄ በማጣታቸው መምህራን የመማር ማስተማር ሂደቱን በነጻነትና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲያከናውኑ እንቅፋት ፈጥረውባቸዋል፡፡ በግጭቶች ምክንያት በሚታቀደው ልክ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር አልተቻለም፡፡
እንደምሳሌ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ በ2017 የትምህርት ዘመን በስድስት ወራት ውስጥ በአንድ ሺህ 71 ትምህርት ቤቶች 896 ሺህ 165 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ ነበር፡፡ ይህ መረጃ ከመምሪያው ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ መዝግቦ ማስተማር የቻለው ግን 249 ሺህ 879 ተማሪዎችን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው 646 ሺህ 286 ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳልተመለሱ ነው፡፡
ከስድስት መቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ 410 ትምህርት ቤቶችም ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በ2017 የትምህርት ዘመን በተያዘው የስድስት ወር ዕቅድ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ፣ 46 የዳስ ትምህርት ቤቶችን እና 243 መማሪያ ክፍሎችን ደረጃቸውን በጠበቁ ክፍሎች ለመተካት ታስቦ የነበረ ቢሆንም የሰላም መደፍረሱ ዕቅዱ እንዳይሳካ አድርጓል፡፡
በጦርነቱ በአማራ ክልል አራት ሺህ 200 ትምሀርት ቤቶች ወድመዋል፡፡ በጦርነቱ ሙሉ ለሙሉ ትምህርት ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው 136 ሺህ ተማሪዎች አሁንም ወደ ትምህርት ገበታ አልተመለሱም፡፡ በክልሉ የተከሰተው ግጭትም በ2016 ዓ.ም ብቻ 42 በመቶ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
ይህ ችግር የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ነገን በተስፋ እንዳይመለከቱ አድርጓቸዋል፡፡ የሰላም እጦቱ ብዙዎች ነገን በተስፋ እንዳይመለከቱና ህልማቸውን ከዳር እንዳያደርሱ እንቅፋት ስለመሆኑ የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሾች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ወዳልተፈለገ ሕይወት የገቡትንም ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በባሕር ዳር ከተማ አዘጋጅቶት በነበረው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ የተገኙ የማኅበረሰብ ወኪሎችም ግጭቱ በትምህርት ዘርፉ ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ አውስተዋል፡፡
በትምሀርቱ ዘርፍ እየደረሰ ያለው ይህ ጉዳት የሁላችንም ጉዳት እንደሆነ መገንዘብ ያሻል፡፡ ልጆቻችን ዛሬ ከትምህርት ገበታቸው ከተለዩ ነገ ይህቺን ሀገር የሚረከብ ዜጋ ማጣታችን አይቀሬ ይሆናል፡፡
ዛሬ በአግባቡ ያላስተማርነው ዜጋ ነገ ሀኪም ሆኖ ከህመማችን አይፈውሰንም፤ ዛሬ በአግባቡ ያላስተማርነው መሀንዲስ ነገ ከተሞቻችንን አይገነባም፤ በጥቅሉ በየሙያ ዘርፉ እኛን ከተቀረው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርጉን ዜጎች እናጣለን፡፡
ስለሆነም ግጭቱ ከዚህ በላይ ይቀጥል ዘንድ ልንፈቅድ አይገባም፤ ነገን ልናልም ግጭቱን ልናቆም ግድ ይለናል፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት በዕቅዱ መሠረት እንዲከናወንና ሀገራችን የተተኪ ዜጎች ድሃ እንዳትሆን ሁላችንም ለሰላም ትኩረት መስጠትና ሰላምን ማስፈን ይኖርብናል፡፡
ሀገር የምትገነባው ብሎም ዕድገቷን የምታረጋግጠው፣ ትውልድ የሚቀጥለው በትምህርት በረከትነት መሆኑን ተገንዝበን ግጭቱ እንዲቀጥል ከሚያደርግ አስተሳሰብም ሆነ ተግባር ፈጥነን መውጣት ይጠበቅብናል፡፡ በተለይም በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኅይሎች እና መንግሥት ሰላምን በማስፈን ረገድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አምነው ለሰላም መስፈን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡
ስለሆነም ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ልጆቻችን ወደ ትምህርት ቤት በመመለስ፣ ለመምህራን ጥላ ከለላ በመሆን፣ የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ በመገንባት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡
በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም