ነጋችን እንዳይጨልም ውይይትን እናስቀድም!

0
112

ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ችግር እየተቃለለ፣ ሰላም እየሰፈነ ስለመምጣቱ ሲገለጽ ይደመጣል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ችግሩ አሁንም ሥር ነቀል መፍትሔ አላገኘም፡፡ አሁንም ቢሆን ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ከሰላም እና ደኅንነት ስጋት ነጻ አልሆኑም፤ በዚህ የተነሳም የክልሉን ማኅበራዊ እንዲሁም ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ በተረጋጋና በሰከነ መንገድ ማድረግ አዳጋች እየሆነ መጥቷል፡፡
ከማኅበራዊ ዘርፎች አንዱ የሆነውን የክልሉን የትምህርት እንቅስቃሴ ብንመለከት በሚፈለገው ደረጃ እየተከናወነ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸምን ለክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች
ባቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው ክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፤ እያደረሰም ይገኛል፡፡ በትምህርት ዘመኑ 2 ሚሊዮን 543 ሺህ 128 ተማሪዎች በመማር ላይ ቢሆኑም በግጭቱ ምክንያት ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አልተመለሱም፡፡
ግጭቱን ተከትሎ የተማሪ መጻሕፍት ለዝርፊያ እና ለውድመት ተጋልጠዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ መምህራንም ለጥቃት ተጋልጠዋል፡፡
እነዚህ በትምህርቱ ዘርፍ ላይ የተከሰቱ ችግሮች የትምህርት ጥራት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባና በክልሉ የትውልድ ክፍተት እንዲፈጠር የማድረግ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ሰላምን ማስፈንና በትምህርት ዘርፉ ላይ የደረሱትን ፈርጀ ብዙ ችግሮች ለመፍታት ብዙ የቤት ሥራዎች ያሉብን ስለመሆኑ ነው፡፡ ወደ ግጭት ያስገቡንን ችግሮች በውይይት መለየትና በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ ሕዝቡን እና መንግሥታዊ መዋቅሩን በማወያየት ትምህርትን የትኩረት ነጥብ ማድረግ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች በመጠገን ወደ ሥራ ማስገባት፣ የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ማስከፈት፣ ተማሪ ማስመዝገብ እና መማር ማስተማሩን ማስቀጠል ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
የንግድ እንቅስቃሴዎችም ቢሆኑ በግጭቱ ምክንያት ከስጋት ነጻ አልሆኑም፡፡ በዚህ የተነሳም የንግዱ ማኅበረሰብ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ አልገባም፡፡
እነዚህ ሁሉ ችግሮች የሰላም መደፍረስ ችግሩ ዘላቂ እልባት ላለማግኘቱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ግጭቱ የአማራ ክልል የትውልድ ክፍተት እንዲያጋጥመው፣ በምጣኔ ሐብት ወደ ኋላ እንዲመለስ፣ ማኅበራዊ መስተጋብሩ እንዲላላ እና ርስ በርሱ በመጥፎ እንዲተያይ ለሚያደርጉ ቁርሾዎች እየዳረገው ይገኛል፡፡
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በክልሉ ገቢ አሰባሰብ ላይም ከፍተኛ ጫና ስለመፍጠሩ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ጠቁሟል፡፡ ቢሮው እንዳስታወቀው በ2015 በጀት ዓመት 119 ሺህ 605 ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር አልከፈሉም።
በተያዘው በጀት ዓመትም በየደረጃው ያሉ የገቢ ተቋማት የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የሚጠበቀውን ግብር እያስከፈሉ ቢሆንም 80 በመቶ የሚሆኑት ግብር ከፋዮች የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸው ግብር የመሰብሰብ ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
እነዚህ ግጭቱ የወለዳቸው ችግሮች የሚጠቁምን የግጭት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በጉልበት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ሰላማዊ መንገድን መሻት ያለብን ስለመሆኑ ነው፡፡ እናም እስከ ዛሬ የሄድንበት ችግሮችን በመሣሪያ ኃይል የመፍታት አማራጭ በብዙ መልኩ እንደጎዳንና በዚህ የኃይል መንገድ ከቀጠልን የመረጥነው መንገድ የበለጠ እንደሚጎዳን፣ ነጋችንንም እንደሚያ ጨልምብን ተገንዝበን ውይይትን በማስቀደም ችግሮችን መፍታት ይኖርብናል፡፡

በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here