ነፃ እና አሳታፊ ምክክር-ለሀገራዊ አንድነት!

0
189

የግማሽ ምዕት ዓመቱን ብቻ የሀገራችንን ፖለቲካ ስንቃኝ የተደጋገመ ክስተት ይበዛበታል። መልካም ነገር ተፈጽሞ እንደማያውቅ ሁሉ መጥፎ ታሪክ እየተመረጠ እና እየተደጋገመ ያለማሰለስ እየተተረከ የሀገራችንን ምስል ክፉኛ አጠይሟል። የሩቁን ትተን የቅርቡን የ1966ቱን አብዮት ተከትሎ የተፈጠሩ የፖለቲካ አንጃዎችን ብናወሳ እንኳን ትርክቶቻቸው መገዳደልን፣ መፈራረጅን እና  ልዩነትን ያሰፉ ነበሩ ማለት ይቻላል።

በዘመነ ደርግ በፖለቲካዊ አሰላለፍ ምክንያት  ዘመድ ከዘመዱ፣ ወንድም ከወንድሙ፣ በተቃራኒ ጎራ በመሰለፍ መገዳደል የበዛበት የታሪክ ሂደት አሳልፈናል። ከበላይ ዘለቀ እስከ ሀይለ ስላሴ፣ ከራስ አበበ አረጋይ እስከ ሌተናል ጀኔራል ተፈሪ በንቲ፣ ከዋለልኝ መኮንን እስከ ጌታቸው ማሩ፣ ከሌተናል ጀኔራል አማን አንዶም እስከ ሌተናል ጀኔራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳን ሕይዎታቸው በግድያ ተጠናቋል።

የተገደሉትን አነሳን እንጂ የተሰደዱት፣ በእስር የተሰቃዩት፣ በማንነታቸው እንዲሁም በፖለቲካዊ አቋማቸው የተፈረጁት በርካቶች ናቸው። ይህ ሁሉ መገዳደል ግን  ለውጥ ማምጣት ይቅርና ገዳዮቹን አሸናፊ አድርጎ አልቆመም። ድሮውኑም ቢሆን በጠብመንጃ አፈ ሙዝ  እና በርስ በርስ ጦርነት የሚመጣ ዘላቂ ሰላም ሳይሆን ዘላቂ ዕዳ ነው። ይህ በደም  ልምምዱን ያደረገው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁንም ከደም ወደ ሐሳብ አላደገም።

ፖለቲካችን ከመገዳደል ወጥቶ ወደ ሐሳብ እና ምክንያታዊ ፖለቲካ እንዲያድግ  አካታች እና አሳታፊ ፖለቲካዊ እና መንግሥታዊ መዋቅር በእጅጉ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ  በሃምሳ ዓመት ውስጥ  በአስተዳደር ብልሽት እና በፖለቲካዊ ጦርነት ምክንያት ያለቁ ዜጎች ቁጥር ቢሰላ ጅቡቲን ከሚያክሉ ሀገራት የሕዝብ ቁጥር ቢበልጥ እንጂ አያንስም።

ይህ አሳዛኝ ክስተት መቆም አለበት:: ሀሰተኛ ትርክትን በማራገብ ከራስ ወደ ራስ በሚተኮስ ጥይት እየተገዳደሉ የመሞት ምዕራፍ ሊዘጋ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ብሄራዊ ምክክር እና ተግባቦት ወሳኝ ነው። ለመመካከር እና ለመግባባት ደግሞ በመጀመሪያ ጣት ከመቀሳሰር መውጣት እና ወደ ራስ መመልከት፣ ተኩስ ማቆም፣ ፍትሐዊ እና ገለልተኛ  ተቋም መገንባት እና በእርቅ ለችግሮች እልባት መስጠት አስፈላጊ የሰላም እና የምክክር አላባውያን ናቸው። ይህ ሲሆን ተማምኖ መመካከር፣ ተመካክሮም መግባባት፣ ተግባብቶም  ሀገራዊ ፍቅርን እና አንድነትን ማምጣት ይቻላል። የሀገር ፍቅር የሚወለደው ከሀሰተኛ የጥላቻ ትርክት እና ማስመሰል ሳይሆን ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት እና ከእኩልነት ነው። ዜጋው በሀገሩ ፍትሕ ካገኘ፣ በሕግ ፊት እኩል ከሆነ፣ በሀገሩ ተቋም እና ሐብት በፍትሐዊነት ከተጠቀመ አያምፅም፤ ይልቁንም ጊዜውን በሥራ ላይ ለማዋል ይተጋል ይሰራል፣ ያለማል።

ምክክር የመሳሪያ አፈ ሙዝን አጥፍቶ፣ ፖለቲካዊ  ሴራ እና ፍረጃን፣ ማህበራዊ ምስቅልቅልን ያስቆም ዘንድ በመጀመሪያ ሂደቱ ሕዝቡንም ሆነ ፖለቲካዊ ልሂቃኑን በተቻለ መጠን  ማሳመን ይኖርበታል። ሂደቱ ካላማረ ውጤቱ ስለማያምር   አወያዮችም ሆኑ አወያይ ተቋሙ ገለልተኛ፣ ነፃ፣ አሳታፊ እና እውነተኛ  ሆነው መታየት ይኖርባቸዋል። ይህ ሲሆን መተማመን ይቻላል። መተማመን ካለ መግባባት፣ መግባባት ካለ ሰላም፣ ሰላም ካለ ልማት፣ ልማት ካለ ሥልጣኔ መኖሩ ሳይታለም የተፈታ ይሆናል። ምክክሩ ማስመሰያ፣ መነታረኪያ እና አግላይ  መስሎ ከታየ ግን ትርፉ ድካም ይሆንና የኢትዮጵያ ሁኔታ አዙሪት ውስጥ ይገባል። ይህ እንዳይሆን ነው ምክክሩ ብዙኃኑን አሳምኖ እና አሳትፎ   ለሀገራችን የትስስር ገመድ መሆን አለበት የምንለው።  ሀገር ግንባታ ሴራን፣ ማስመሰልን፣ ቸልተኝነትን፣ አግላይነትን አይፈልግም። ይልቁንም አሳታፊነትን፣ ጥልቅ ትንታኔን፣ ጠንካራ ተቋም እና አስተዳደርን ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ምክክሩ መሰረት ሊሆን ይገባዋል!!

በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here