በሰሜን ባሕር ቀጣና ቤልጄዬም የነፋስ ኃይል ማመንጫ መቅዘፊያዎቿን በነፋስ አቅጣጫ ወይም ትይዩ ከፊት በመትከሏ ሦስት በመቶ የሚሆን ኃይል ኔዘርላንድ እንደተሰረቀባት በመግለጽ መክሰሷን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል::
የኔዘርላንድ የአየር ሁኔታ ትንበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ የቤልጄዬም የነፋስ ኃይል ማመንጫ “ተርባይኖች” ከሀገሩ ማለትም ከኔዘርላንድ አየር መስረቃቸውን ተናግረዋል:: ዋና ሥራ አስፈፃሚው ሬምኮ ቨርዚጅልበርግ ከቤልጂዬም ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ቤልጂዬም የነፋስ ሀይል ማመንጫ “ተርባይኖችን” ከኔዘርላንድ በፊት በመትከሏ ሦስት በመቶ የሚሆን የነፋስ ኃይል ከኔዘርላንድ ይሰርቃሉ::
የነፋስ ኃይል መሰብሰቢያ “ተርባይን” ነፋስ ባለበት ትይዩ ሲተከል የሚኘው ኃይል እና በነፋስ ትይዩ ከተተከለ “ተርባይን” ጀርባ ሲተከል የሚኘው የኃይል መጠን የተለያየ መሆኑን ነው፡፡
የጠቆሙት- ዋና ስራ አስፈፃሚው:: ለዚህ በማሳመኛ ነጥብነት ያነሱት ከፊት ለፊት የሚተከሉ “ተርባይኖች” ከፍ ያለ ኃይል ወይም ግፊት ሲያገኙ ከኃላ የሚተከሉት የዓየር ፍጥነትም ሆነ ግፊታቸው የቀነሰ መሆኑን ነው ያሰመሩበት::
የነፋስ ግፊት “ከተርባይን” ወይም መቅዘፊያ ማማ ከፊት እና ከኋላ ሲለካ የኃይል መጠኑ የተለያየ መሆኑን ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በአገራት መካከል የተሻለ የተቀናጀ አሰራር እንዲሰፍንም ጠይቀዋል::
ከነፋስ ኃይል መሰብሰቢያ መቅዘፊያ ማማዎች “ተርባይኖች” ጀርባ የሚለካው የነፋስ ፍጥነትም ሆነ የሚገኘው ግፊት አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል:: ለዚህ ከፊት ያሉ ተርባይኖች የነፋሱን ግፊት እንደሚቀንሱት ማረጋገጣቸውን ነው ያሰመሩበት::
የኔዘርላንድ የአየር ሁኔታ ትንበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሀገሪቱ በስተምእራብ በሚገኙ የነፋስ ኃይል መቅዘፊያ “ተርባይኖች” ባሉበት ቀጣና ሌሎች አገራትም ሊተክሉ ስለሚችሉ ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ ነው የጠቆሙት:: በመሆኑም ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት ለነገ ወይም ይደር የማይባል ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት:: በመጨረሻም የሰሜን ባህር ቀጣና ቀስበቀስ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ማማዎች በብዛት ሊተከሉበት እንደሚችል ጠቁመው የአየር ስርቆት ወደ ግጭት አድጐም በአገራት መካከል ጦርነት እንዳያስነሳ መስራት እንደሚገባ በማሳሰብ ነው ያደማደሙት::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም