ኒዩንግዌ ብሔራዊ ፓርክ

0
17

ብሔራዊ ፓርኩ በሩዋንዳ የሚገኝ በብዝሃ ህይወቱ ተጠቃሽ ነው:: ፓርኩ በግምት ከ500 እስከ 600 ሄክታር ደን ለበስ ስፋትም አለው::

በፓርኩ ከሚገኙ 1,100 የእፅዋት ዝርያዎች 265ቱ በፓርኩ ተራራማ ቀጣና ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ ናቸው:: ከ345 የዓእዋፍ ዝርያዎች 30ዎቹ በሌላ ቀጣና የማይገኙ መሆናቸውም ተረጋግጧል::

ኒዩንግዌ ብሔራዊ ፓርክ በዓለም አቀፍ የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ሁለንተናዊ እሴት ያለው አስፈላጊ ሥነምህዳር እና ስነ ህይወታዊ ሂደት መጠበቂያ መሆኑም ታምኖበታል:: በዚህም ጥበቃ እና እንክብካቤ ከሚሹ ቀጣናዎች አንዱ ሆኗል:: የአፍሪካ ፓርኮች ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር ኒዩንግዌን ለማስተዳዳር የ20 ዓመት ስምምነት እንዲፈራረሙ ተደርጓል:: በዙሪያው የሚገኙ ሰፋሪዎች ሀብቱን የመንከባከብ ስሜትን በመገንባት እና ስነምህዳሩን ራሱን ለማስቻል እየተጉ መሆኑንም ነው ድረገፆች አስነብበዋል::

በኒዩንግዌ 86 አጥቢ የዱር እንስሳት ተመዝግበዋል:: ከነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ  ብርቅዬ ናቸው::

ከዱር አራዊቱ 12 የዝንጀሮ ዝርያዎች ጦጣ፣ ጐሬላ፣ ቺምፓንዚ የመሳሰሉት ይገኛሉ- በፓርኩ::

በፓርኩ ከ40 ሺህ የሚበልጥ አገር በቀል ችግኞችን በማባዛት 30 ሄክታር የሚሆን የተራቆተ ቀጣናን በመትከል የደን መመናመን ለመግታት የፓርኩ አስተዳደር ጥረት እያደረገ ነው:: ከዚህ ባሻገር በዙሪያው በሚገኙ ኗሪዎች እና በዱር አራዊቱ መካከል የሚከሰት ግጭት እና የሚደርሰውን  ጉዳት ለመቀነስ እና ለማልማት በህብረተሰቡ ጥረት እየተደረገ ነው::

ለኒዩንግዌ ብሔራዊ ፓርክ የብዝሃ – ህይወቱን ደህንነት ለማስቀጠል ፈተናዎች ገጥመውታል- ከስጋቶቹ መካከል አደን፣ ህገወጥ ማእድን ማውጣት እና ለእርሻ ስራ መሬትን ማስፋፋት ተጠቅሰዋል:: ለዚህ ለተደቀነው ለችግሮቹ የጥበቃ ሰራተኞች በካሜራ ክትትል እንደሚያደርጉም ድረ ገፆች አስነብበዋል:: ፓርኩን ተዘዋውሮ ለመጐብኘት ደረቅ ወቅት ማለትም ከሰኔ እስከ መስከረም ተመራጭ መሆኑም ነው የተጠቀሰው::

ለዘገባችን አፍሪካን ፓርክስ፣ ቪዚት  ኒዩንግዌ እና ሳፋሪ ቡኪንግስ ድረ ገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ 26  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here