በክፍል አንድ በታዋቂው ቻይና አሜሪካዊ የድርጊት ፊልሞች ተዋናይ በሆነው ብሩስ ሊ የተፈጠረው ጂት ኩንዶ ማርሻል አርት አራተኛ ዳን ደረጃ የደረሰውን እና ማስተርነት ማዕረግ ያገኘውን ማስተር ሳዳት ሀብታሙ ጋር የነበረንን ቆይታ አስነብበናችኋል:: ስፖርቱ ለወጣቱ ያለው ጠቀሜታ፣ በውድድር ስላስመዘገቧቸው ውጤቶች እና ቀጣይ እቅዳቸው ከአሰልጣኝ ማስተር ሳዳም ጋር ያደረግነው የመጨረሻ ክፍል ቆይታ እነሆ! መልካም ንባብ::
ስፖርቱ ለወጣቱ ያለው ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ምንድን ነው?
ጅት ኩንዶ የአንድን ሰው ተክለ ሰውነት እና ባሕሪ ከአዕምሮ ብስለት ጋር አጣምሮ በማስተካከል ሰብዕና መገንበት የሚችል ስፖርት ነው፤ ይህን የማድረግ ሚና አለው:: ወጣቶች ወደ ስፖርቱ ጠልቀው ሲገቡ በጥሩ የሰውነት ሚዛን እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል:: ለውጡ ረጅም ጊዜ እንኳን አይወስድም፣ በአጭር ጊዜ ጥሩ አካላዊ እና አዕምሯዊ አቋም ይይዛሉ::
ብሩስሊ “አንድ አዲስ ተማሪ ገብቶ ሦስት ወራትን በጥሩ ስልጠና ከቆየ አዲስ አይባልም” ይል ነበር:: ለምን ቢባል ተማሪው በሦስት ወራት ውስጥ የሚገባውን ትምህርት ጠንቅቆ አውቆ በመከላከልም በማጥቃትም ሙሉ ስለሚሆን ነው:: በተለይ ከአካላዊ ጥንካሬ ባሻገር ውስጣዊ ጥንካሬ ይሰጣል:: የተሻለ አስተሳሰብ እና ስብዕና ያላቸው ወጣቶችን የመፍጠር አቅም አለው::
ስፖርቱ ጸበኝነትን የሚሰብክ አይደለም:: ማሰልጠን ከጀመርኩ ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ከእኔ ተማሪዎች ውስጥ በድብድብ እና በመጥፎ ምግባር ተነስቶ የሚያውቅ የለም:: ተማሪዎቼ ጸብ እና አምባጓሮ ውስጥ ተሳተፉ ተብሎ ስሞታ መጥቶብኝ አያውቅም:: ስፖርቱ መከላከል እና ማጥቃትን የሚያስተምር ቢሆንም በዋናነት ግብረ ገብነትን እና ለሰው ማዘንን የሚያስተምር ነው:: ከዚያ ባለፈ በሕይወት ውስጥ ምን አላማ ሊኖረን እንደሚገባ እና ቀጣይ መንገድን መለየት ላይ ያተኩራል:: የሰው ልጅ አላማ እና ተስፋ ካለው ደስተኛ ሕይወት መኖር እንደሚችልም ያስተምራል::
በውድድር ስላመጣችሁት ውጤት ንገረን?
ኮሮና እና በክልላችን ያለውን የሰላም እጦት ችግር ጨምሮ ለመወዳደር የተመቸ ብዙ ጊዜ አልነበረንም:: በአንጻራዊነት የተመቼ ዓመት የነበረው 2015 ነው:: በዚሁ ዓመት ከግለሰቦችም ሆነ ከመንግሥት የሚያበረታታ ድጋፍ ነበረ:: ወደ ውድድሩ ስንሄድ የመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር ሙሉ ወጪያችንን ሸፍኖልናል::
ውድድሩ የነበረው አዲስ አበባ የስፖርት አካዳሚ ነበር:: አስር ተጫዋቾች፣ አንድ አልጣኝ (እኔ) እና የቡድን መሪ በአጠቃላይ 12 ሆነን ነበር የሄድነው:: ከ53 እስከ 57 ኪሎ የሚጫወቱ ልጆች ናቸው የያዝነው:: በዚህ ምድብ ለፍጻሜ ደርሰን የአማራ ክልልን ሁለተኛ ደረጃ እንዲይዝ አድርገን ነው የተመለስነው:: በመሳሪያ አጠቃቀምም ጥበብን በማሳየት ውድድር በተለይ በኬንዶ ሦስተኛ ደረጃን ይዘን አጠናቀናል:: ከዛ ውድድር ወዲህ ያለው መነቃቃት እና የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ነው::
የዓለም አቀፍ ውድድሮችን የመሳተፍ እድል ነበራችሁ?
አውሮፓ ውስጥ የጂት ኩንዶ ውድድር አለ፤ የእኔ ልጆች አሁን ላይ እየሠሩ ያሉት በዚህ ውድድር ለመሳተፍ ነው:: ከጥቂት ጊዜ በፊት ለ10 ልጆች እድል መጥቶ ሳንሄድ ቀርተናል:: በወቅቱ የሰሜኑ ጦርነት ነበር፤ የእኛ አካባቢ ደግሞ የጦርነቱ ቀጠና ነበር:: በዚያ በጦርነት ወቅት ደግፉን ብሎ እርዳታ መጠየቅ ለአዕምሯችን ከበደን፤ ሀገር እየተተራመሰ እንዴት ወደ ውጪ እንሄዳለን ብለን እድሉን ሰረዝነው:: የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች ተሳትፈው ውጤት አምጥተዋል:: በተለይ በማስተር የሱፍ የሚመሩት የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች በእነሱ የኪሎ ምድብ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል:: የመኖሪያ ፈቃድ ተሰጥቷቸው እዛው የቀሩም አሉ:: በእርግጥ የእኔ ልጆች በሀገራቸው እንዲኖሩ ነው የምመክራቸው:: በተፈጠረው ሀገራዊ ችግር ምክንያት ከፍተኛ እድል አምልጦናል::
ልጆቼ ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ውድድር እየተዘጋጁ ነው:: በተለይ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች አብዛኞቹ ፓስፖርት አውጥተው እየተጠባበቁ ነው:: በእርግጠኝነትም አስገራሚ ውጤት እንደሚያመጡ ሙሉ እምነት አላቸው:: እኔም በተማሪዎቼ እተማመናለሁ:: ዋናው ነገር ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን::
በግልህ ያስመዘገብካቸው ውጤቶች ካሉ ብትነግረን?
የአማራ ክልልን ወክዬ እኔ ውድድር አላደረኩም፤ በፊት ናዝሬት ሳለሁ ክለብ ወክዬ ውድድሮችን አደርግ ነበር:: በግጥሚያ፣ የተለያዩ ጥበቦችን (አርት) በማሳየት፣ በምቶች (ኪክ)፣ በመሳሪያዎች (ሻሞላ፣ ኬንዶ፣ ዱላ…) እና በሌሎች ውድድር አይነቶች ጥሩ ውጤቶችን በተለያየ ጊዜ አስመዝግቤያለሁ፤ ክለቤንም የተሻለ ደረጃ እንዲይዝ አድርጌያለሁ:: በአንድ አጋጣሚ እንዳውም ወደ ጀርመን ለውድድር እንዴሄድ እድል መጥቶልኝ ነበር፤ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያች ሳልሄድ ቀርቻለሁ::
በአማራ ክልል ስፖርቱን ለማስፋፋት ምን እየሠራችሁ ነው?
መካነ ሰላም፣ ቦረና፣ መሐል ሳይንት ዴንሳ፣ አጅባር፣ ገነቴ፣ አቀስታ ኮምቦልቻ በአጠቃላይ ወደ ሰባት ከተሞች ላይ ማዕከላት አሉን:: ተቀባይነቱ በፊት ከነበረው በጣም የተሻለ ነው:: የተማሪው ቁጥርም ከፍተኛ ነው:: እንደ ክልል ደግሞ ወቅታዊ ችግሩ ይዞን ነው እንጂ ባሕር ዳርን ጨምሮ በሁሉም የክልላችን ዞኖች አቅም በፈቀደ ቅርንጫፎችን ለመክፈት እቅድ ይዘናል:: አሁን ላይ ጥቁር ቀበቶ ያላቸው አስልጣኞች ቁጥር 61 ደርሷል:: እነዚህ አሰልጣኞች ቅርንጫፎችን ለመክፈት ዝግጁ ናቸው:: የፈቃድ አሰጣጥ፣ የጸጥታ እና የመንገድ መዘጋት ችግሮች ለጊዜው አስተጓጉለውናል::
ስፖርቱን በክልላችን ለማስፋፋት ከገጠሟችሁ ችግሮች በዋናነት ምታነሳው ካለ?
በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል የጁት ኩንዶ ማኅበራት አሉ:: በክልል አቀፍ ደረጃም ጁት ኩንዶ ውድድር አላቸው፤ ከዚያ ነው ወደ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች አሸናፊዎች የሚመረጡት:: በተመሳሳይ በክልላችን ጂት ኩንዶ ማኅበር እና ስፖርት ቤቶችን ለመመስረት እና ስፖርቱን ለማስፋፋት አቅደን ስንቀሳቀስ በዞን እና በክልል ደረጃ እንቅፋቶች ገጥመውናል:: በአሰልጣኝነት የተመረቁ ተማሪዎቼ በተለያዩ አካበባቢዎች ስፖርት ቤቶችን ለመክፈት ህጋዊ ፈቃድ ያስፈልጋቸዋል:: ከሚከፍቱበት ከተማ ጀምሮ ዞን እና ክልል ድረስ እውቅና ይሰጣል:: በተለይ በክልል ደረጃ የፍቃድ እውቅና የመስጠት ችግር እየተፈጠረብን ነው:: “ፍቃዱን አሁን ላይ አንሰጥም፤ እንደ ሌሎች ክልሎች ለጂት ኩንዶ ፍቃድ እንድንሰጥ እውቅና አልተሰጠንም፤ ፌደራል ላይ ሄዳችሁ ፈቃድ ተቀበሉ” የሚል መልስ ይሰጡናል፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን እውቅና የመስጠት መብት አለው:: ሌሎች ክልሎች ፌደራልን ጠይቀው አይደለም እውቅና የሚሰጡት::
የእኔን ፈቃድ ባሕር ዳር ነው ያወጣሁት:: በወቅቱ ስፖርቱን በደንብ የሚያውቅ ቀና አመለካከት የነበረው ሰው ነው ስፖርት ኮሚሽኑን ይመራ የነበረው:: የሌሎች ክልሎችን ተሞክሮ አጣርቶ “ሌሎች ጋ ካለ ይህ ዓለም አቀፍ ስፖርት አማራ ክልል ላይ የማይኖርበት ምክንያት የለም” የሚል አቋም የያዘ ነበር:: በእሱ አማካኝነት በሕጋዊ መንገድ ያለ ብዙ እንግልት ፈቃዴን ማውጣት ችያለሁ:: በዚህም ምክንያት ነው የስፖርቱ ታዋቂነት እና ተደራሽነት ሊሰፋ የቻለው:: ወደ 61 የሚደርሱ አሰልጣኞችን አፈራሁ:: እነሱን ከፌደራል ፈቃድ አውጡ ማለት ተገቢነት የለውም:: ለሌሎች ክልሎች የተሰጠው እድል ለአማራ ክልል እንዴት ይነፈጋል::
የኦሮሚያ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኃላፊን አነጋግሬው ነበር፤ እዛ ስለነበርኩ የክልሉን ክለብ ወክዬ እወዳደር ስለነበር በደንብ እንተዋወቃለን፤ ለአሰልጣኞቹ ክልሉ ፈቃድ አልሰጥም ማለቱን ስነግረው ተገረመ፤ ክልሉ አጣርቶ ፈቃድ መስጠት እንደሚችል ገልጾልኛል፤ በመሆኑም በተለያዩ ነገሮች ማገዝ እና ማጠናከር ሲገባ ፈቃድ መከልከል ተገቢ አይደለም::
ውድ አንባብቢያን በዚህ ጉዳይ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽንን አቋም በቀጣይ እትም በስፖርት አምዳችን የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ መግለፅ እንወዳለን!
የወደፊት እቅዳችሁ ምንድን ናቸው?
ጁት ኩንዶ እንደ ሌሎች ክልሎች በአማራ ክል በደንብ ተስፋፍቶ የተለያዩ ማኅበራት ተመስርተው የማየት እቅድ አለን:: በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ በሚደረጉ ውድድሮች አማራ ክልልን ብሎም ኢትዮጵያን ወክለን የተሻለ ውጤት ለማምጣት ወጥነናል:: በአማራ ክልል ሁሉም ወረዳዎች እና ዞኖች ጂት ኩንዶ ማዕከላት ተከፍተው ንቁ፣ ቀልጣፋ፣ ሀገር ወዳድ እና ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት መሥራት ዋነኛው እቅዳችን ነው:: ይህ እንዲሆን የሕዝባችንን፣ የመንግሥትን እና ሌሎች ፍላጎቱ ያላቸው አካላትን ድጋፍ እንፈልጋለን::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም