ንቅሳት

0
749

አንዲት ወዳጄ ኢትዮጵያ አየር መንገድ በአስተናጋጅነት ያወጣውን ማስታወቂያ ትመለከታለች። አየር መንገዱ አካላዊ ውበትን በማስቀደም ቆነጃጅትን ይመርጣል። ይህንንም የምልመላ መስፈርቱን ለዓመታት አስቀጥሎታል። እናም ይህች ወዳጄ አካላዊ ውበቷን ገምግማ ሄዳ ትፈተናለች። “በጣም አሪፍ ቁመና እና ፈገግታ አለሽ፣ፊትሽም ውብ ነው ግን ግንባርሽን  ተነቅሰሻል፣በሌላ ጊዜ አስጠፍተሽ ነይ” እንዳሏት አጫውታኛለች።

ሳይኮሎጂ ዶት ኮም የሰው ልጆች ሰውነታቸውን ለምን ይነቀሳሉ በማለት ምክንያቶችን አስቀምጧል። ኢትዮጵያዊያን ንቅሳት እንበለው እንጂ ሌላው የዓለም ክፍል “ታቶ”   በሚል ያውቀዋል፣ ይጠቀምበታል። ንቅሳት በባህሪው ቋሚ ወይም ጊዜያዊ ሊሆን ይችላል፤ የወደዱትን ለማግኘት፣የጠሉትን ለመቀየር፣የጎደለውን ደግሞ ለመሙላት እና ለሌሎች ጉዳዮች ንቅሳት ጥቅም ላይ ይውላል።

ሲጠቃለል ግን ንቅሳት ሰዎች ለስሜት፣ ፍላጎት፣ማንነት እና ሌሎች ሁነቶችን ለመግለጽ የሚጠቀሙበት የእጅ ሥራ ጥበብ ነው። ንቅሳት በኢትዮጵያ ቀደምት ባህል አለው። አሠራሩ በተመረጡ ሰዎች የሚከወን ሆኖ እንደ ምልክት እና መለያነት ያገለግላል። በተለይም ንቅሳት በቀያይ ሰዎች ላይ ጎልቶ የመታየት ዕድል አለው። እስከ አንድ ሳምንት ድረስ የሚፈጀው ቀደምት ኢትዮጵያዊው ንቅሳት  በአጋም እሾህ፣ መርፌ እና ጥቀርሻ ዘመኑ የሚፈልገውን ጥንቃቄ ሳያደርግ ይከናወናል።

የጥርስ ድድን ያህል ስስ የሰውነት ክፍል ለእሾህ ሰጥቶ ለተከታታይ ቀናት መወጋት ምን ያህል ጥንካሬን እንደሚጠይቅ አስቡት። በቀደመው የኢትዮጵያ ባህል በተለይም ሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል (አማራ እና ትግራይ) ጠንካራ የንቅሳት ባህል አለ።

በንቅሳት ልማድ የትኛውም ሰው አይነቀስም።ሰው ይመረጣል። ለንቅሳት ቆንጆ መልከ መልካም፣ቀይ ረዘም ያለች ዓይን ውስጥ የምትገባ ቆንጆ ሴት ትመረጣለች። በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወንዶችም ይነቀሳሉ። ደረት፣ አንገት፣ ቅንድብ፣ እግር፣ እጅ እና ጥርስ በንቅሳት ውስጥ የሚያልፉ የሰውነት ክፍሎች ናቸው።

ሰዎች የመስቀል፣ ፀሐይ፣ ኮከብ፣ የስም፣ የዘንዶ፣ የእባብ እና ሌሎችንም  ቅርጾች በገላቸው ላይ ይነቀሳሉ። ከጠቀሜታ አንጻር ካየነው ንቅሳት ውበትን ለማጉላት፣ የጥርስ ሕመምን ለማስታገስ፣ የእንቅርት ሕመምን ለመቀነስ፣ እምነትን ለመግለጽ፣ ፍቅርን ለማሳየት በጥቅም ላይ ይውላል። አንገታቸውን የተነቀሱ ኢትዮጵያዊያን  ሴቶች መስቀልን ከግንባር እስከ ደረት ድረስ ተነቅሰው ስናስተውል ማንነታቸውን እናይበታለን። የአምላካቸውን ስም እጃቸው ላይ ጽፈው ስናይ የየትኛው እምነት ተከታዮች እንደሆኑ እንገነዘባለን። “የእናቴን  ስም እጄ ላይ የተነቀስሁት ፣እሷን በጣም ስለምወዳት ለማስታወስ ነው” ያለችኝን ልጅ አስታውሳለሁ።

ከዓመታት በፊት ዘጠኝ እና አስረኛ ክፍል ተማሪዎች በነበርንበት ዘመን አንድ ፋሽን ጎብኝቶን ነበር። ከሰፈራችን ራቅ ብለን ወደ ወንዝ አካባቢ ሄደን ኳስ እንጫዎት ነበር። ያን ጊዜ ወርቁ የምንለው አንድ የሰፈራችን ልጅ ቴኳንዶ ይሰራ ነበር። የእጅ ጡንቻው ላይ ደግሞ ምላሱን አውጥቶ ሊባላ የሚመስል እባብ ተነቀሰ። ከቅርብ ጓደኛችን አንዱ አሌክስ እጁ በጣም ወፍራም ስለነበር ያንን እባብ ተነቀሰው። የሚገርመኝ ንቅሳቱ ነው። ምንም ጥቀርሻ በሌለበት በእሾህ እየጫሩ እባብን መሳል። በደንብ እየደማ የሚፈለገው ቅርጽ እስኪመጣ ድረስ አሁንም ማድማት፣ ማቁሰል ይቀጥላል። ከቀናት በኋላ የአሌክስ እጅ ቆስሎ ቆዳው ተልጦ የሚፈለገው እባብ ጡንቻው ላይ ታዬ።እያንዳንድሽ በጡንቻ አትደርሽብኝም ብሎ እኛንም ይጎተጉተን ጀመር ።

አንድ ቀን እኔም እሾህ ይዤ ቀጫጫ ጡንቻየን እያደማሁ ራሴው መንቀስ ጀመርሁ ።የልብ ቅርጽ ነበር የነቀስሁት። ለሚያየው ሰው ኤም (M) ፊደል ሆኖ ነበር። ቤት ስሄድ የሰፈር ሴቶች ለእናቴ ሄደው “ኧረ ልጅሽ አፍቅሮ፣ደግሞ ኤም ማናት?” ብለው ያሳጡኝ ጀመር። ገላችን ጥቁር በመሆኑ እናም ንቅሳቱ ማድማት ብቻ በመሆኑ ከዓመታት በኋላ የአሌክስ እባብም የእኔዋ ኤም ም ከንቅሳትነት ደብዝዘው ጠፍተዋል።

ንቅሳት ረጂም ዓመታት ያስቆጠረ ዓለም አቀፍ ጥበብ እና ጌጥ ነው።ኢትዮጵያዊው ንቅሳት የራሱ መልክ እና ቅርጽ አለው፤የሚወደድ እና የሚያስደንቅ ጥበብም ነበር።

“የግንባርሽ መስቀል የአንገትሽ ድርድር

ያኑራት ዘላለም ነቃሺን በምድር”

በሚል እንኳን የተነቀሰችውን ነቃሿንም ጭምር የዘላለም ህልውነት ምርቃት የሚያሰጥ ስነ ቃልን ያስደረድራል። ንቅሳቱ ከጉንጭ እስከ አንገት ድረስ ይደረግ እና እንደገና ደግሞ መልካም ጥርስ ኖሯት ድዷ ቀይ በመሆኑ ፈገግታዋን እንዳትጠቀም እንቅፋት ሲሆንባት፤ወላጆቿ እና አካባቢዋ ድዷን እንድትነቀስ ያበረታታል። የበለጠ ውበት እና ፈገግታን ለማግኘት ድዷን ትነቀሳለች።

“ላምባዲና የለኝ ኩራዝ አላበራ

እስኪ አንዴ ሳቂና ራታችን እንብላ”

ብሎ ባላገሩ የጥርሷን ንጣትና ድምቀት ይናገርላታል። በተለይ ቀደምት ንቅሳቶች የኢትዮጵያዊያንን ሃይማኖት እና እምነት የሚናገሩ ናቸው። መስቀልን በብዛት በደረት፣ አንገት፣ እጅ፣ እግር እና ግንባር ላይ መነቀስ የተለመደ ነው። ለዚህ ነው ቆንጆዋ የት እንደተወለድሽ ንቅሳትሽን ማየት በቃኝ፣ ሌላ ነገር አያሻኝም በሚል ስንኝ የሚቋጠርላት።

“የአንገትሽ ውቅራት የተዥጎረጎረው

ከየት እንደበቀልሽ ሁሌ ሚያሳብቀው”

እሁን ዘመኑ ንቅሳትን ባህላዊ እና ዘመናዊ ብሎ በሁለት ይከፍለዋል። የድሮውን ባህላዊ ነው፣አይረባም የሚል አዲስ ትውልድና ዘመን መጥቷል። ግንባር እና አንገታቸውን የተነቀሱ ሴቶችን “ንቅሴ፣ጋዜጣ ፊት” እያሉ ማሸማቀቅ፣ እንዲጸጸቱ ማድረግ አሁን ከተሞች የደረሱበት የዘመናዊ ውበት መልክ ሆኗል። ወይዛዝርቱ ገጠር በልጅነታቸው ተነቅሰው ከተማ ሲገቡ መሳቂያ እና መቀላጃ ሲሆኑ እናያለን።

ይህንን ጫና መቋቋም ሲያቅታቸው ተነቃሾቹ ንቅሳቱን ለማስጠፋት ድጋሜ ነቃሽ ቤት ይሄዳሉ። ማጥፋት እስከ ሰባት ዙር ይወስዳል። እንደ መነቀሱ ቀላል አይደለም። ገንዘብንም ጊዜንም ይፈጃል። የተለመደን ምልክት ከሰውነት ላይ ማጥፋት በሚያውቁት ሰው ዘንድ የእንግድነት ስሜት ፈጥሮ ባእድነትን ይፈጥራል።

“በእጅ ሲነቀሱ ፋራ፣ በማሽን ሲነቀሱ አራዳ” እሳቤ እግር ሰዷል። የከተሜነት እና ምዕራባውያን መጤ ልማዳዊ ድርጊት መስፋፋት ቀደምቱን ኢትዮጵያዊ የውበት ዘይቤ እየቀየረው ነው። ዘመናዊ እና ባህላዊ በሚለው ክፍፍል ውስጥ ግጭቶች አሉ። ዘመናዊ ነኝ የሚለው እኔ ልደግ፤ ባህላዊው ደግሞ እኔ ልቆይበት በሚል ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። መስቀል፣ስም፣ምልክት ወይም ሌሎች የንቅሳት ንድፎች አሁን ትልልቅ ሴቶች ላይ ሲታዩ መሳለቂያ የሆኑት በምዕራባዊያን መጤ ልምዶች መስፋፋት ምክንያት ነው። አሁን በኢትዮጵያ ከተሞች በማሽን የሚደረገው ዘመናዊው ንቅሳት በፋሽን መልክ እየተስፋፋ ነው።

በውጪው ዓለም የስፖርት፣ የሙዚቃ፣ ፊልም ኢንዱስትሪው ከዋክብት የሚነቀሱትን ምልክት አድናቂዎቻቸው ለማድረግ ይሞክራሉ። ያ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያዊያን ዝነኞችም ተላልፎ እነሱም ተነቅሰው ሌሎችንም እንዲነቀሱ ምክንያት ሳይሆኑ አልቀሩም። የአምላካቸውን ምስል፣ የፈጣሪያቸውን ስም፣የሚወዱትን ነገር፣ ማስታወሻነት እና ሌሎችንም ይነቀሳሉ።

ንቅሳት በዚህ ዘመን ከጌጥነት ያለፈ ምክንያት ይኖረዋል። አንበሳን ጀርባው ላይ የሚነቀስ ሰው ተግባሩ ከጌጥነት ያለፈ ይሆናል።አንገቱ ላይ የሙዚቃ ምልክት የሚነቀስ ሰው ሙዚቃ መውደዱን ለመግለጽ ሊሆን ይችላል። የንቅሳት ሂደቱ በዘመናዊ ማሽን የሚከናወን በመሆኑ ወጣቶች ያለ ሕመም ስሜት፣ በአጭር ጊዜ፣ በጥንቃቄ የሚፈልጉትን ይነቀሳሉ። እምነታቸውን፣ ፍላጎታቸውን፣ አስተሳሰባቸውን፣ ታሪካቸውን እና ሌሎች ማንነታቸውን በንቅሳት ይገልጻሉ።

ሁሉም በወቅቱ ያምራል እንዲሉ፣ንቅሳት በአንድ ወቅት የሚመኙትን፣የሚፈልጉትን ሌላም ነገር ያስተላልፉበት እና ከጊዜ በኋላ ስሜት ይቀየራል።እንደ ቀልድ የተነቀሱት የሆነ ወቅት ላይ አላስፈላጊ ሆኖ ሊታይ ይችላል።  አንድ ወዳጄ የነገረኝን የንቅሳት ጸጸት ላስከትል። ልጅቱ በአፍላ ወጣትነት እድሜዋ ቅዱስ የሚባል ልጅ ታፈቅርና ስሙን እጇ ላይ ትነቀሳለች። ፍቅረኛዋም በአንጻሩ የልጅቱን ስም  ቅድስት ብሎ ይነቀሳል። ቅዱስ እና ቅድስት ፍቅረኛሞች ሆኑ። ከዓመት በኋላ ሁለቱ ፍቅረኛሞች ክፉኛ ይጣላሉ።

እሷ የእሱን ስም ስታይ መብገን፣ እሱም የእሷን ስም እጁ ላይ ሲመለከቱ ብስጭት አልተዋቸው ይላል። አንዱ የሌላውን ፍቅር ከልቤ አወጣሁ ቢልም እጃቸውን ሲያዩ ቋሚ የንቅሳት ማስታወሻ እጃቸው ላይ አለ። ንቅሳቱን ማጥፋት ቀላል አይደለም። ቢያንስ እስከ 7 ጊዜ በየወሩ የንቅሳት ማጥፊያ ቦታ መሄድን ይጠይቃል። ለማጥፋት የሚወስደው ገንዘብም ኪስን ይነካል።

እናም እነዚህ ጥንዶች ወደ ንቅሳት ቤቱ ተመልሰው በቶሎ ማጥፋት ባለመቻላቸው፣ ደግሞም ከሌሎች ሰዎች ንቅሳቱን ለምን አጠፋህ/ሽ የሚል ጥያቄ ለመሸሽ በንቅሳቱ ተጨማሪ ስም አከሉበት። ሴቷ ቅዱስ በሚለው ስም ሚካኤል የሚል ስም ጨመረችበት። የፍቅረኛውን ስም ወደ መልዓክ ለወጠችው። ወንዱ ደግሞ ቅድስት በሚለው ስም ማርያም የሚል ስም ጨምሮ ከሰው ወደ አምላክ እናት ተለወጠ። ቅድስት ማርያም  እና ቅዱስ ሚካኤል የሁለቱን ፍቅረኛሞች የንቅሳት ስም የለወጡ ስሞች ሆኑ ብሎ ወዳጄ አጫውቶኛል።

የንቅሳት ጉዳይ ሲነሳ አሁን ዓለም አቀፍ ተግባራዊነቱ ድንበር የለውም።የትኛውንም ዓይነት ንቅሳት፣ በየትኛውም ቦታ ሰዎች ተነቅሰው እናያለን። የዘመኑ ንቅሳት አስገራሚ፣ አስፈሪ፣ አሰቃቂ ሆኖ እናያለን። ሙሉ ሰውነታቸውን በዘንዶ፣ በሰይጣን ምልክቶች የሸፈኑ ሰዎችን ማየት አስፈሪ ነው። ንቅሳትን ተመልካቾች በተለያዬ መልኩ ይረዱታል። ብዙ ንቅሳት የሚያበዙ ሰዎችን ፣ሰዎች ሲመለከቱ በፍርሀት እና ጥርጣሬ ያያሉ። ብዙ ጊዜ እባብ እና ዘንዶን ከሰይጣናዊ እምነት  ጋር የማያያዝ ልማዶች አድገዋል። የእጅ ጡንቻዎቻቸውን በአስፈሪ ንቅሳት ያንቆጠቆጡ ሰዎች በቀማኛነት እና ዘራፊነት ሲፈረጁ እናያለን።

ንቅሳት እና ስነልቦናዊ ጉዳቱን በሚመለከት በቀደሙት ዓመታት በርካታ ሐተታዎች እንደነበሩ የሚያስታውሰው ሳይኮሎጂ ዶት ኮም የሚነቀሱ ሰዎችን ከመጥፎ ተግባራት ጋር ማያያዝ የተለመደ ነበር ይላል። ሰውነታቸውን የተነቀሱ ሰዎችን ከወንበዴ፣ጠብ አጫሪ እና ወንጀለኛነት ጋር ማያያዝ በእኛም ሀገር ወደ ህሊናችን የሚመጣ ልምምድ ነው።

የአዕምሮ ጤና  ባለሙያዋ ሮዛልቫ  ቫልሴታ ይህ እሳቤ አሁን ንቅሳት የትውልዱ ፋሽን በመሆኑ እየተለወጠ መምጣቱን  ጽፋለች። ንቅሳት ሰዎች ስሜት እና ፍላጎታቸውን  የሚገልጹበት ቢሆንም እንኳን በተግባር ግን ሰዎች የተነቀሱትን ናቸው ማለት አይደለም ብላለች። “የትኛውም ሰው ስለንቅሳቱ ቢጠየቅ  ከንቅሳቱ ጀርባ የሚነገር ታሪክ አለው፣ አንድን ስዕል አይቶ በብዙ እንደሚተረጉሙት ሁሉ ለብዙ ትርጓሜ መጋለጥ አለ። ትክክለኛውን ትርጓሜ ማወቅ የሚቻለው ከባለቤቱ በመጠየቅ ነው” ትላለች። “መልዓክ የተነቀሱትን ጥሩ፤ ሰይጣን የተነቀሱትን መጥፎ ማለት አይቻልም” ም ብላለች።

በሀገራችንም በንቅሳት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ቀድመው የሚያስጠነቅቁት፤ ተነቃሽ ለመነቀስ ሲመጣ ለምን እና ምን እነቀሳለሁ የሚለውን ከስሜት ነጻ ሆኖ እንዲያስብ ነው። ብዙዎች የዚህ ፋሽን ተከታዮች አፍላ ወጣቶች በመሆናቸው ከወራት እና ሳምንታት በኋላ ንቅሳቱን አጥፋልኝ የሚል አቤቱታን ይዘው ስለሚመለሱባቸው ነው።  ተነቃሾች በወቅቱ በደረሱበት ብስለት እና እሳቤ  በንቅሳቱ ምቾት ያጣሉ፤መነቀሳቸው ለስነልቦና እና አዕምሮ እረፍት አልባነት ሲዳርጋቸው ለማጥፋት  ይሞክራሉ።

በውጪው ዓለም እንደምናስተውለው ሰይጣንን በሰውነታቸው የሚነቀሱ አሉ። በእኛ ሀገር ደግሞ መልዓክን የሚነቀሱ አሉ። ሁለቱም ወገን እምነቱን ለማንጸባረቅ ንቅሳትን እንደሚጠቀሙበት ያሳያል። የውጪው ዓለም ሰይጣንን እንደ አምላክ ለሚቀበሉ ሰዎች እውቅና ይሰጣል፤ በእኛ ሀገር ደግሞ ሰይጣን የመጥፎ ነገር ሁሉ ስር ተደርጎ ነው የሚወሰደው። የአዕምሮ ጤና  ባለሙያዋ ሮዛልቫ  ቫልሴታ የሚሉት ሐሳብ እውነት የማይመስለን የደረስንበት የዲሞክራሲ እና የእምነት አረዳድ ልዩነት ሰፊ መሆን ነው። ለሮዛልቫ ሰይጣን ወዳጅ መስሎ ይታያታል፤ ለእኔስ? አጥፊ ጠላት ሆኖ። ስለዚህ የሰይጣንን ምስል ሰውነቱን የተነቀሰ ሰው ሳይ እፈራዋለሁ።

ንቅሳት በእኛም ሀገር በወረርሽኝ መልኩ  ተስፋፍቶ ሁልጊዜ አዳዲስ ፈጠራዎችን ያልፋል። ማንም ሰው የፈለገውን መነቀስ ይችላል ነቃሹ ባለሙያ እስከ ቻለ ድረስ። እንደ ድሮው መስቀልና ፀሐይን እየተነቀሰ አይጸናም። አዳዲስ ፈጠራዎች በየጊዜው ይመጣሉ። የዛሬ ፋሽን ነገ ይጠላል። በአዲስ ይተካል። ጉጉቱንም፣ ነብሩንም፣ ሰይፉን፣ ቢላዋውን፣ ሸረሪት እና ሌሎችንም በገባው እና በተረዳበት አግባብ ይነቀሳል።

የመነቀስ ሒደቱ ሁልጊዜ ከስህተት ነጻ አይደለም። “ሲያጌጡ ይመለጡ” እንዲሉ እመው (አበው ብቻ እስከመቼ) ለጌጥ የተባለ ንቅሳት ለሕመም የሚሆንበት ዕድል አለ። እንደ ድሮው በንቅሳት ወቅት በሕመም መሰቃየት ባይኖርም ዛሬም ስጋቶች አልተለዩትም። መቁሰል፣ ማመርቀዝ(ኢንፌክሽን)፣የቆዳ መቆጣት (አለርጂክ)፣ የቆዳ ካንሰር ምልክቶችን መደበቅ፣ በደም ልገሳ ወቅት ለቫይረስ መጋለጥ ስጋቶች ናቸው።

የአሜሪካ ምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣን ንቅሳትን በሚመለከት ሕጎችን አውጥቷል። አንድ ሰው ከተነቀሰ ሦስት ወራት በኋላ ደም መለገስ እንዲችል ሕግ አውጥቷል። ይህም በደም ውስጥ  በቫይረስ የሚተላለፉ እንደ ኤች አይ ቪ፣ጉበት መሰል በሽታዎችን ለመከላከል ነው። በተጨማሪም አሜሪካ ለነቃሾች እውቅና ሰጥታለች። እውቅና ከተሰጣቸው  ሰዎች ውጪ ተነቅሰው የሚመጡ ሰዎች ደም አይለግሱም ብሏል።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here