– የኢላ በረድ መስዋዕት
በዓለም ታሪክ ውስጥ ጀግኖች ቶሎ እንደ አብሪ ኮከብ ብልጭ ብለው ጠፍተዋል። መልካም አሻራ ያላቸው ሰዎች እንደ ጠርሙስ ቶሎ ይሰበራሉ። ጀግኖች ጉልህ አሻራቸውን ለማስቀመጥ ቶሎ ተጣድፈው መጥተው፤ ቶሎ ይመለሳሉ። ደፋሮች ስለሚያስቀምጡት አሻራ እንጂ ስለሞት አይጨነቁም። ሕይወታቸውን ለዓላማቸው አሳልፈው ይሰጣሉ። ፈሪዎች ለሕይወታቸው ስለሚሳሱ ረጂም ዕድሜ ይኖራሉ።
በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ ቶሎ አንጸባራቂ ኮከብ ሆና ድንገት የጠፋች ሴት አለች። ለሀገሯ የሕይወት ዋጋ ከፍላለች። አሟሟቷ ዛሬም በወቅቱ ከነበሩ ሰዎች ሕሊና ውስጥ በትውስታ ተቀምጧል። ንግሥት አበበን ዛሬ እናስታውሳታለን።
ሁሉም መንግሥታት ኪነ ጥበብን ለርዕዮት ዓለማቸው ማስፈጸሚያ ቢጠቀሙበትም እንኳን እንደ ደርግ መንግሥት ሙዚቃን የተጠቀመባት አለ ለማለት ይከብዳል። ደርግ ሙዚቃን ተጠቅሞባታል፤ ሙዚቃም ዘመኑን ተጠቅማበታለች። ደርግ የመሠረታቸው ከቀበሌ እስከ አውራጃ የሚሠሩ የኪነት ቡድኖች ዛሬ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ አንጋፋ እያልን የምንጠራቸውን ድምጻዊያን እና ከያኒያንን አፍርተዋል። የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማው ዘመን 1960 ወይስ 1970 የሚለው አከራካሪ ቢሆንም እንኳን የደርግ ዘመን አሻራ ዛሬም ድረስ የሚታይ ነው። ንግሥት አበበም የዚያ ዘመን ፍሬ ናት።
የደርግ መንግሥት ከሻዕቢያ እና ሕወሐት ውጊያዎች ተከፍተውበት ነበር። ከሶማሊያም በርካታ ጆሮ ገብ የሙዚቃ ስራዎችን እንደምታቀርብ ነበር። ሙዚቃ ደግሞ ማዋጊያ መሣሪያ ነበረች። በወቅቱ ንግሥት አበበ የምስራቅ እዝ ሙዚቀኞች ኪነት አባል ነበረች። ወደ ፊት እድገቷ የሚጠበቅ፣ ወጣት፣ በሙያዋ የተዋጣላት እንደነበረች ይነገርላታል።
ንግሥት አበበ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በከፍተኛ 4፣ ቀበሌ 39፣ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል አካባቢ ታህሳስ 21 ቀን 1956 ዓ.ም ነበር የተወለደችው። የአንደኛ እና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት ተምራለች።
ከበሮ መምታት፣ መዝፈንና ማንጎራጎር የምትወደው ንግሥት ለሙዚቃ ባላት ፍቅር ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለች በከፍተኛ 4 ቀበሌ 39 በተቋቋመው ኪነት ውስጥ ተመርጣ ገባች። አባቷ አቶ አበበ ገብረአብ “ልጄ አዝማሪ አትሆንም” ብለው ቢያንገራግሩም እሷ ግን ትምህርቷን አቋርጣ ምድር ጦር በሙዚቀኛነት ተቀጥራ ወደ ሐረር ተጓዘች።
በሰራዊቱ ውስጥ እያለችም ተወዳጅ የነበረውን “አይቼው ልመለስ” የተሰኘ ካሴት በማሳተም በርካታ አድናቂ አፍርታለች። ንግሥት በሙዚቃ ክፍሏ ውስጥ ላደረገችው አገልግሎት የሃምሳ አለቅነት ማዕረግም አግኝታለች። በቅን ታዛዥነቷ፣ በታታሪነቷና በሀገር ወዳድነቷ ትመሰገን ነበር።
በታህሳስ ወር መጀመሪያ 1980 ዓ.ም የምስራቅ እዝ ኪነት ኦርኬስትራ አባላት ከሻዕቢያ ጋር ለሚፋለመው ሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ዝግጅታቸውን ለሀያ ቀናት በኤርትራ ከረን አቅርበው ነበር። ከቀናት በኋላ ታህሳስ 21 ቀን ደግሞ የኪነት ቡድኑ አባላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ላይ ሳሉ ያልታሰበ አደጋ ገጠማቸው። ከአስመራ 38 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ኢላ በረድ ሲደርሱ የተኩስ እሩምታ ተከፈተባቸው።
በተከፈተው ተኩስ ንግሥት እና 23 የቡድኑ አባላት ሕይወታቸው አለፈ። ኪነ-ጥበበኞቹን ያጀቡት ከ20 በላይ ወታደሮችም ህይወታቸውን በተኩስ አጡ። የተቀሩት ቆሰሉ። 14 ኪነ ጥበበኞች ደግሞ ቆሰሉ። በዕርግጥ ንግሥት ለህክምና ሆስፒታል ከደረሰች በኋላ ነበር ያረፈችው። ቀብሯም በሐረር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከባልደረቦቿ ጋር ተፈጽሟል። አራት ሰዎች ያ ሁሉ የጥይት በረዶ ሲዘንብ፣ የቦምብ ውርጅብኝ ሲወረወር፣ የመትረየሱ ላንቃ የጎረሰውን ያህል ሲተፋባቸው አንድም ነገር ሳይነካቸው የሆነውን ሁሉ እየተመለከቱ ተርፈዋል።
ብዙ ሙዚቃ ትሠራለች የሚል ተስፋ የተጣለባት ንግሥት አበበ በተወለደች በ23 ዓመቷ በሚያሳዝን ሁኔታ ህይወቷ አልፏል። አሟሟቷን ተከትሎ ከፍተኛ ኀዘን የፈጠረው ደግሞ በወቅቱ ክርስትና ያላስነሳች አራስ መሆኗ ነበር።
ሐምሌ 22 ቀን 1987 ዓ.ም እናቷ ወይዘሮ ማስረሻ ገብረስላሴ ለማስታወሻ ጋዜጣ ስለ ልጃቸው እንዲህ ሲሉ ነበር የተናገሩት “በእሷ ኀዘን ነው ዓይኔ የደከመው። ከወለድኳቸው ልጆቼ ቀይ እሷ ብቻ ነበረች። ቆንጆ ነበረች። የመኳንንት ልጅ ትመስል ስለነበር ነው ‘ንግሥት’ ያልኳት። ከሌሎቹ ልጆቼ ሁሉ እሷ ተለይታ ዘፋኝ በመሆኗ ቅር ተሰኝቼ ነበር።
“የቀበሌ ኪነት እያለች ወደዚያ እንዳትሄድ በመከልከሌ ‘አንቺ አድሀሪ ነሽ፣ እንዴት ትከለክያታለሽ?’ ብለው አስረውኛል። በኋላም ቀበሌው ማዘፈኑን አላቋረጠም፣ እሷም መዝፈኗን አላቆመችም። ስለዚህ መፍትሄ ይሆናል ብዬ እህቷ ዘንድ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ዲላ ላክኋት። ነገር ግን እሷ አንድ ጊዜ በዚህ ነገር ተለክፋለች። የሄደችበት ሀገር ትምህርት ቤት ገብታ ከልጆቹ ጋር ስትጫወት አይቶ የዲላ ኪነት ወሰዳት። በዚህ ጊዜ የእህቷ ባል እንደገና ከገባችበት ኪነት አስወጥቶ እቤቱ ስለደበቃት ታሰረ።
“እኔም ይህን ሰምቼ ዲላ ሄጄ ይዣት ተመለስኩኝ። ነገር ግን ለቤተሰብ ሳትናገር ምድር ጦር ሄዳ ተቀጠረች። ልንከለክላት ሞክረን ነበር። እሷ ግን ‘አሻፈረኝ’ ስላለች ተውናት። ያን ጊዜ ምድር ጦር ባትቀጠር ኖሮ እንደወጣች ቀልጣ አትቀርም ነበር” ብለዋል።
ማስታወሻ ጋዜጣ እንደዘገበው ንግሥት እናቷ ዘንድ አዲስ አበባ ሄዳ ነሐሴ 16 ቀን 1979 ዓ.ም እየታረሰች ነበር። አራስ ቤት ሆና ስልክ ተደወለ። ለሥራ ተጠራች። በወቅቱ እናት ‘ማነው የሚደውለው? ለምንድነው የሚደወለው?’ ብለው ጠይቀዋል። ንግሥትም ‘በአስቸኳይ በሥራ ገበታሽ ላይ ተገኚ፤ አለበለዚያ ከሥራ ትባረሪያለሽ ነው የሚሉኝ’ ብላ መልሳለች። እናትም ‘አይሆንም’ ቢሉም ልጃቸውን ቤት ማስቀረት አልቻሉም።
ንግሥት ተጣደፈች። አዲስ አበባ መስቀልን አክብራ ወደ ሐረር ተጓዘች። ሐረር ከተጠራች በኋላ 15 ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አስመራ እንድትሄድ መታዘዟን ለእናቷ አሳወቀች። ጉዞው የማይቀር ነበር። ክርስትና አስነሳለሁ ያለችው እናት ሁሉን ነገር በውጥኑ ትታ ለጉዞ ተዘጋጀች።
እናቷ ወይዘሮ ማስረሻ ‘ተይ፣ እንዴት ክርስትና ሳታስነሺ ትሄጃለሽ?’ ቢሏትም መልሷ ‘እንዴት ወደኋላ አፈገፍጋለሁ’ የሚል ነበር። የኪነቱ የሙዚቃ ዝግጅት ልምምድ ወራትን ወሰደ።
ንግሥት ወደ አስመራ ከመጓዟ በፊት ድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያ ለመጨረሻ ጊዜ ለእናቷ ስልክ ደውላ አነጋግራቸዋለች። በሄደች በ20 ቀኗ የመሞቷ ዜና ተሰማ።
የንግሥት አበበ እናት ከፍተኛ የኀዘን ስሜት ውስጥ ገብተው ነበር፤ ኀዘኑ አባዝኗቸው በመኪና አደጋ በ1988 ዓ.ም መጨረሻ ላይ መሞታቸውንም ቤተሰቦቿ ተናግረዋል።
የንግሥት አበበ ታላቅ እህት ዘውድነሽ መርጊያ “ታሪክ ያለው ሰው አይሞትም፤ ንግሥት አልሞተችም” ሲሉ ተናግረዋል። በአራስነቷ ለሀገራዊ ግዳጅ ከአባቱ ጋር ትታው የሄደችው የንግሥት አበበ ልጅ አንተነህ በለው ይባላል- አሰበ ተፈሪ ነው የሚኖረው።
በልጅነቷ የሒሩት እና ብዙነሽ በቀልን ዘፈኖች ታንጎራጉር ነበር። አይቼው ልመለስ፣ በሸዋ ላይ ደሴ (ልይህ እንደገና)፣ ና ዞማዬ፣ ገላ መውደድ እና ሌሎች ዘፈኖቿ ሁሌም መታዎሻዎቿ ሆነው ይኖራሉ። ለሀገር የሚከፈል መስዋዕትነትን ንግሥት አሳይታ አልፋለች።
ማረፊያ
ኬሪ ዋሽንግተን
በአሜሪካው ሆሊውድ የፊልም ኩባንያ ለአንድ ጥቁር ፊልም መስራት የገቢ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ለዘመናት የተገለለውን የጥቁር ታሪክ እና አቅም መወከልም ጭምር ነው፡፡ ያሁ ኒውስ ምርጥ ተከፋይ ሴት ተዋንያንን አስቀምጧል፡፡
በዚህም መሰረት ቀዳሚዋ ተከፋይ ኬሪ ዋሽንግተን 50 ሚሊዮን ዶላር ሀብት ፈጥራለች፡፡ በታዋቂው የስካንዳል ድራማ ላይ ኦሊቪያ ፖፕን ሆና ለመተወን 1 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏታል።
ጃንጎ አንቼይንድ እና ሬይ ባሉ ፊልሞች ላይ ጠንካራ ትወና አሳይታለች። በይበልጥ ደግሞ የሆሊውድ ምርጥ ተዋናይት ያደረጋት ስካንዳል የተሰኘው ድራማ ነው፡፡
ኦሊቪያ ፖፕ በቴሌቪዥን ላይ ያለች ጥቁር ሴት ገጸ ባሕሪ ብቻ አልነበረችም፡፡ በራሷ መተማመን ያላት፣ ክብሯን የምታስጠብቅ እና ግቦቿን በራሷ መንገድ የምታሳካ ሴት ሆና ቀርባለች።
ዝነኛዋ ኬሪ ዋሽንግተን በሙያ ሕይወቷ የኦሊቪያ ፖፕን ገጸ ባህሪ ወክላ ስትሰራ ለሁሉም ተከታይ ታዳጊ ተዋናዮች አርአያ ሆናለች ይላል ያሆ ኒውስ፡፡
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም