ንግሥት ዘውዲቱ

0
212

ንግሥት  ዘውዲቱ ከዐፄ ምኒልክ እና ከወረኢሉ ባላባት ልጅ ከወይዘሮ አብችው በእነዋሪ ከተማ ጅሩ ሚያዝያ 22 ቀን 1866 ዓ.ም ነበር የተወለዱት። ከዘውዲቱ በፊት ወይዘሮ ሸዋረጋ እና ልጅ አስፋ ወሰንን ወልደው ስለነበር ሦስተኛ ልጅ ነበሩ፤ በወቅቱ የተለመደ እንደነበረው ለትግራዩ ገዢ ለዐፄ ዮሃንስ ልጅ ለራስ አርአያ ተድረው እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡

ወደ ንግሥና

ንግሥት ዘውዲቱ ወደ አባታቸው ዙፋን የመጡት መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ከስልጣን ሲሻሩ ነበር፡፡ ዐፄ ምኒልክ ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም ቢሞቱም የመሞታቸው ሁኔታ ይፋ ስላልሆነ ቤተ መንግሥት ውስጥ ቆይተው የዐፄ ምኒልክ የልጅ ልጅ አቤቶ ኢያሱ በጥር ወር 1908 ዓ.ም እቴጌ ጣይቱን ከቤተ መንግስት በግዞት ወደ እንጦጦ ሲልካቸው ዘውዲቱንም ወደ ሸዋ ፉሌ ላኳቸው።

አቤቶ ኢያሱን ከመንግሥት ስልጣን ለማውረድ በመኳንንቱ በኩል ስምምነት ቢደረስም  የህዝቡን ተቃውሞ ለማብረድ ሲባል ወይዘሮ ዘውዲቱ ንግሥተ ነገሥት እንዲሆኑ ታጩ። ሹመቱንም ተቀብለው በ43 አመት እድሜያቸው ዙፋን ላይ ተቀመጡ። ንግሥተ ንግሥት ዘውዲቱ መንፈሳዊነታቸውን የሚያጠብቁ ስለሆኑ ባለቤታቸውን ራስ ጉግሣ ወሌን ትተው በብትህና ለመኖር መርጠዋል ተባለ። ራስ ጉግሣም ጎንደር እንደገና ተሹመው ከቤተ መንግስት እንዲርቁ ተደረገ። ደጃች ተፈሪ መኮንን (በኋላ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ) ራስ ተብለው እና አልጋ ወራሽ ሆነው ተሾሙ።

ስኬታማ ስራዎች

በንግሥተ ንግሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት በርካታ ታላላቅ እና አዳዲስ ስራዎች መከናዎናቸውን ራስ ከበደ ተሰማ የታሪክ ማስታወሻ በተሰኘ መፅኃፋቸው ላይ እንደጻፉት የኢትዮጵያ ከፍተኛ  የሆነ የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ውጤታማነት የተመዘገበበት ወቅት ነበር።

ይልቁንም በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያን ሲያሰሩና ሲያሳድሱ፣ በተጨማሪም የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤትንና የንግሥት ዘውዲቱ ማዋለጃ ሆስፒታልን ማሰራት ላይ ትኩረታቸውን አደረጉ።  በእርሳቸው ዘመን ነበር ኢትዮጵያዊ ጳጰስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሾመው።

የዓለም ማኅበር አባልነት

የዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ጠቅላላው ጉባዔ መስከረም 17 ቀን 1916 ዓ.ም ስብሰባው ላይ ኢትዮጵያ ማኅበርተኛ እንድትሆን ፈቃዱ መሆኑን ገለጸ። በዚህ ጊዜ ዋናው መልእክተኛ ደጃዝማች ናደው የደስታ ስሜታቸውን ለመግለጥ ንግግር ማድረጊያው ስፍራ ላይ ቆመው የሚከተለውን ዲስኩር ተናገሩ፤ “ጠቅላላው ጉባኤ በበጎ ፈቃደኝነትና በትክክለኛ ፈራጅነት፣ በጥልቅ አስተሳሰብ መርምሮ ወደ ማኅበሩ ስለመግባት ያቀረብነውን ጥያቄ ስለ ተቀበለው፣ የኢትዮጵያ መልእክተኞች በግርማዊት ንግሥተ ንግሥት ዘውዲቱና በልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለ ሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ስም፣ እንዲሁም በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋና ያቀርባሉ።

“የሰውን ልጅ ወንድማማችነት የመመሥረት ዓላማ ባለው ውሳኔያችሁ የተሰማንንም ልባዊ ደስታ እንድገልጽላችሁ ይፈቀድልኝ ዘንድ እለምናለሁ። ኢትዮጵያ ባለፈው የጀግንነት ታሪክና በከፍተኛ ሥልጣኔዋ የምትኮራ አገር መሆንዋ፣ የዘመናዊ ድርጅቶች ከሚያስገኙላትም ፍሬ ተካፋይ ለመሆን ብርቱ ጥረትና ሙሉ ፈቃደኛነት እንዳላት የታወቀ ነው። መንግሥታችንም ይህን ጥረት ወደ መልካም ግብ ለማድረስ የዓለም መንግሥታትን አንድነትና ኅብረት የሚያስፈልግ መሆኑን በጥብቅ ያምንበታል።”

ስለ ባሮች ነፃነት

ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መጋቢት 16 ቀን 1916 ዓ.ም በግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱ ፈቃድ ስለ ባሮች ነፃነት አንድ ደንብ አወጡ። ደንቡ «ስለ ባሮች አስተዳደርና ነፃነት የቆመ ደንብ» የሚል አርእስት ተሰጥቶትና እንደ መጽሐፍ ሆኖ በልዑል አልጋ ወራሽ ማተሚያ ቤት ታትሞ ወጣ። መጽሐፉ ባለ 10 ገጽ ሲሆን የደንቡ ቃል በ45 ቁጥሮች ተመድቧል፡፡

የአፄ ቴዎድሮስ ዘውድ መመለሱ

ከእንግሊዝ  ሀገር የመጣው የዐፄ ቴዎድሮስ ዘውድ ሐምሌ 4 ቀን 1917 ዓ.ም ቅዳሜ ለግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱ ተመለሰ። በዚህም ጊዜ የተፈጸመውን ሥነ ሥርዓት በተመለከተ ከጧቱ በ4 ሰዓት የግቢ ሚኒስትር ደጃዝማች ወልደ ገብርኤል በሻህ በጦር ልብስ ያጌጡ ጭፍሮች አስከትለውና በአራት ፈረሶች የሚሳብ ሠረገላ አሲዘው ከአቶ ሣህሌ ፀዳሉ ጋር ወደ እንግሊዝ ሌጋሲዮን ሄዱ። የእንግሊዝ መንግሥት ሚኒስትር ሚስተር ቻርልስ ቤንቲንክም ዘውዱን በሠረገላው ላይ አስቀመጡትና ሁሉም ዘውዱን አጅበው ወደ ቤተ መንግሥት መጡ።

“ግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱና ልዑል አልጋ ወራሽ በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ በተለይ በተሰናዳው ስፍራ ከመኳንንት ጋር ተቀምጠው ይጠብቁ ነበር። የግቢ ዘበኞችም በግቢው ውስጥ በቀኝና በግራ ተሰልፈው ነበርና ሠረገላው በሰልፉ መካከል አልፎ ከመንግሥት ፊት ደረሰ። እዚያም አንድ ጠረጴዛ ተዘጋጅቶ ነበርና ሚስተር ቤንቲንክ ዘውዱን ከሠረገላው አውርደው በጠረጴዛው ላይ አስቀመጡትና ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ቃል ተናገሩ፤ “ግርማዊት ሆይ በንግሥት ቪክቶሪያ መንግሥት በ1860 ዓ.ም ከመቅደላ  የተወሰደውን የአፄ ቴዎድሮስን ዘውድ የታላቂቱ ብሪታንያና የአየርላንድ፣ ከባሕር ማዶ ያሉት ግዛቶች ንጉሥና የህንድ ንጉሠ ነገሥት በሆኑት በግርማዊ ጌታዬ በንጉሡ ትዕዛዝ ለግርማዊት ንግሥት በማክበር መለስሁ።“

ንግሥት ዘውዲቱ እጅግ መንፈሳዊ ስለነበሩ የተለያዩ ተቋማትን አስገንብተዋል።  ካሰሩዋቸው ቤተ ክርስትያኖች ውስጥ ሰባቱ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጭ ደግሞ ሰባት አብያተ ክርስቲያናትን አስገንብተዋል።

ንግሥተ ንግሥት ዘውዲቱ አባታቸው ዐፄ ምኒልክ የምእራባውያንን ስልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የነበራቸውን ፍላጎት በሚገባ የተገነዘቡ ስለነበሩ በበኩላቸው ትምህርት እንዲስፋፋ አዋጅ አወጡ። አዋጁም እድሜው ከ7 እስከ 21 ዓመት ድረስ የሆነ ልጅ ያለው በአንደኛ ደረጃ የንባብና የፅሕፈት ትምህርት፣ በሁለተኛ ደረጃ በሀገራችን ካለው የእጅ ሥራ ውስጥ ልቡ የወደደውን ለልጁ እንዲያስተምር የሚደነግግ ነበር። ካላስተማረ ግን 50 ብር ቅጣት እንዲቀጣ የሚልም  ሀሳብ ተካቶበት ነበር። ይህንንም የመቆጣጠሩ ሃላፊነት የንሥሐ አባት ፣ የገጠር መሪጌታ እና የደብር አለቃ ሁሉ ግዴታ ተጥሎባቸው ነበር ይባላል።

የፖለቲካ ውዝግብ

አንዱ የንግሥተ ንግሥቲቱ አገዛዝ ዘመን ችግር ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ውዝግብ ነበር፤ ዘውዲቱ   ስልጣኔን ልጠቀም ብለው ሳያስቸግሩ ለ12 ዓመት ከግማሽ አልጋው ላይ ቢቀመጡም አልጋ ወራሹ ራስ ተፈሪ የንግሥት ዘውዲቱን ደጋፊዎች በማግለልና የራሳቸውን ደጋፊዎች በየቦታው በመሾም ኃይላቸውን አጠናክረው የመንግስቱን ስልጣን ለመውሰድ እየተዘጋጁ ይሄዱ ጀመር። ተፈሪንም ለማንገስ ውስጥ ውስጡን በደጋፊዎቻቸው ሲጠነሰስ ከቆየ በኋላ ቀኝ አዝማች ባንትይዋሉና ግራዝማች ይገዙ የሚመሩት ቡድን ንግሥተ ንግሥት ዘውዲቱን “ራስ ተፈሪን ያንግሱልን” ብለው ሲጠይቁ “እስቲ ልዋል ልደርና መክሬ መልሱን እሠጣችኋለሁ” ሲሉ ቢመልሱላቸውም “አይሆንም አሁኑኑ መልሱን ካልሰጡን” ብለው ሰቅዘው ያዙዋቸው። ንግሥተ ንግሥትም ነገሩ ስለገባቸው የነበራቸው አማራጭ መስማማት ብቻ ነበርና ተስማሙ። ስለሆነም ራስ ተፈሪ ንጉሥ ተፈሪ ተብለው መስከረም 27 ቀን 1921 ዓ.ም ዘውድ ደፉ።

ከዚህ ሹመት በኋላ ግብር በሁለት ቦታ እየተበላ፤ ሰው እየተከፈለ፤ በንግሥቲቱና በአዲሱ ንጉሥ መካከል ውስጥ ውስጡን አለመግባባት እየፈጠሩ ሄዱ። ቅሬታ አሳይተው የነበሩትን የንግሥቲቱን የበፊት ባልና የጎንደሩን ገዢ ራስ ጉግሣ ወሌንም ማስወገድ አስፈላጊ ሆነ። ራስ ጉግሣ ወሌም ወደ አዲስ አበባ ሲጠሩ አኩርፈው ለመምጣት ባለመቻላቸው በነደጃች ሙሉጌታ የሚመራ ጦር ዘመተባቸው። በዚሁም ውጊያ አንቺም ላይ ተገደሉ። ንግሥት ዘውዲቱም ከራስ ጉግሳ ወሌ ሞት በኋላ በሁለተኛው ቀን መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።  ንግሥተ  ንግሥት  ልጅ  ስላልነበራቸው  መሬታቸውንና  ንብረታቸውን  ልዕልት  ተናኘ  ወርቅ  እንዲወርሱ  ተደረገ ።

ምንጭ : –

የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ፣ በጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ

የኢትዮጵያ ረጅም የህዝብና የመንግስት ታሪክ ፣ በዶክተር ላጵሶ ጌታሁን ድሌቦ።

(መሠት ቸኮል)

በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here