ከግጭት እና ከጦርነት ጋር ውሎ ማደርን ያህል አሰቃቂ እና አሳዛኝ ክስተት የለም። ዓመት የተሻገረው የአማራ ክልል ግጭት አሁንም አስከፊ ድባብን አዝሎ ቀጥሏል። እንኳንስ በሀገር አቋራጭ መንገዶች ይቅርና ወረዳን ከወረዳ፣ ከተማን ከከተማ በሚያገናኙ መስመሮች ሳይቀር ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሆኗል። የመሳሪያ ድምፅ ሳይሰሙ ውሎ ማደር ብርቅ ነው። መንገዶች በተደጋጋሚ በመዘጋታቸው ሻጭ እና ገዢ መገናኘት አልቻሉም። ታማሚ ወደ ህክምና፣ ተማሪ ወደ ትምህርት ቤት፣ አማኝ ወደ ቤተእምነት ለመሄድ ችግር ሆኗል።
ይሄ ሁሉ ሰቆቃ እያለ እና እየቀጠለ ለሰላም ቁርጠኛ ሆኖ ገፍቶ የሄደ አካል ብዙ የለም። በአንደበት ደረጃ የሰላም ጥሪዎች ቢሰሙም፣ ከጥሪ ያለፈ ወደ ሌላኛው ያደገ ምዕራፍ የተሻገረ ተግባር የለም። ተፋላሚ ሀይሎችም እስካሁን ግልፅ እና ቁርጥ ያለ የሰላም ንግግር እና የድርድር ሐሳብ ሲያቀርቡ አይሰሙም። በብዛት የዳመነ ሐሳብ ተይዟል። ግልፅ፣ የጠራ፣ አሰራር ያለው የንግግር እና የድርድር ሐሳቦች ሲነሱ አለመሰማታቸው የቀጣዩን ጊዜነት የሰላም ብቸኛ አማራጭ አጠራጣሪ ያደርገዋል። የሕዝቡ ሰቆቃ እንዳይቀጥል ብዙዎች እየሰጉ ነው፡፡ ነገን ማየት እና ማለምም ከባድ እየሆነ ነው፡፡ ውሎ ማደር፣ አድሮም መዋል አጠራጣሪ የሆነበት የማህበረ ፖለቲካ ድባብ አለ፡፡ ይህ ሁኔታ ሊስተካከል የሚችለው በንግግር እና ድርድር ነው፡፡ ማንም ንግግር እና ድርድርም ሊሸሸው አይገባም፡፡ ምንም ሆነ ምን የአማራ ክልሉ ቀውስ ካለንግግር መፍትሄ ሊሰጠው ስለማይችል ድርድርን መቅረብ ያስፈልጋል፡፡
ለወገን ሲባል ማንም በምንም ሁኔታ ለሕዝብ፣ ለሀገር እና ለወገን ሲባል የመሳሪያ ድምፆች እንዲዘጉ ለንግግር እና ድርድር ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል። መናናቅ፣ መፈራረጅ፣ ጥበብ የራቀው ትንታኔ፣ ከእውነት እና ነባራዊ ሁኔታው ያፈነገጠ እይታ ወደ ሰላም ደጅ ለመቅረብ አስቸጋሪ ያደርገዋል። በትክክል መሬት ላይ ያለውን እውነት ተገንዝቦ ለድርድር መዘጋጀት ተገቢ ነው። ቀውሱ ከቀጠለ ሰባዊ እና ቁሳዊ ውድመቱ ጨምሮ ሀገር ቁልቁል እየተጓዘች የፈሰሰውን ለማፈስ ሳይቻል ይቀራል። በስንት ዘመን የተገነባ ሐብት በውስን ደቂቃ ሲወድም፣ አይተኬው የሰው ልጅ ሕይዎት ሲቀጠፍ፣ ወገን ከወገኑ ጋር ሲተኳኮስ ማየት ልብ ሰባሪ ነው።
ሕዝባችን ወደ ሰላም መንገድ ይመጣ ዘንድ ንግግር እና ድርድር ከልብ እና ከእውነት ሊተገበር ይገባል። የአማራ ክልል ግጭት ሁነኛ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው በንግግር እና በሀቀኛ ድርድር መሆኑ ግልፅ ነው። ማንም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ለድርድር እና ንግግር ዝግጁ መሆን ይገባዋል። ለዚህም በሙሉ ልብ እና በሀቅ መሰናዳት ይገባል፡፡ ተመን የለሽ የሆነው የሰላም ውል ተፈርሞ ሕዝባችን ይድን ዘንድ ሁላችንም አወንታዊ ሚናችንን እንወጣ፡፡ ከማጋጋል ርቆ ለንግግር ዝግጅነት እንዲኖርም ሁሉን አቀፍ ትብብር በእጅጉ ተገቢ ነው፡፡
በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም