ንግግር የችግር ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ነው!

0
124

የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

ክልሉ ውስጥ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በየቦታው የሚካሄዱ ህዝባዊ ውይይቶች ፍሬ እንዲያፈሩ የሁሉም ምኞት ነው፡፡ ግጭትና ብጥብጥን በማስወገድ፤ በሰላም ወጥቶ መግባት ጤነኛ የሆነ ሰው ሁሉ ፍላጎት ነው፡፡

ምክንያቱም ሁልጊዜም ቢሆን ጦርነት ካለ ሞት፣ ጦርነት ካለ መፈናቀል፣ ጦርነት ካለ ስደት፣ ጦርነት ካለ ረሃብ አለ። ከቁሳዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ባሻገር ጊዜያዊ እና  ቋሚ የሆነ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳትን አስከትሎ ማለፉ የምንጊዜም ሀቅ ነው።

ዓለም ለጦርነት የሚታትረውን እና ቤንዚል እያቀበለ የማን  ደም ፈሰሰ በሚል የሚያራግበውን ያህል፤ ለሰላም መስፈንና ለውይይት የሚከፍለው ዋጋ ማነስ ትውልድን በየዘመኑ እየተፈራረቀ ዋጋ ሲያስከፍለው ኖፘል።

አብዛኛዎቹ አስከፊ ጦርነቶች በውይይት ነው የተቋጩት፡፡ ነገር ግን ጦርነት ትቶት ከሚሄደው ዳፋ አንዱ ከአንዱ ትምህርት ባለመውሰዱ ሁሉም በዙር ዋጋ እየከፈለ ይኖራል፡፡ በየዘመኑ ትውልድ ካለፈው ቁርሾ እያጣቀሰ እንደመልካም ነገር የየራሱን የጥፋት አሻራ ለማስቀመጥ ሲሽቀዳደም ማየት የዓለማችን ሌላኛው መልክ እየሆነ ቀጥሏል።

ከሁሉም ጦርነቶች ማግስት የምንሰማው ጸጸት እና ባልነበር የሚል ቁጭትን ነው፡፡ ከጦርነት ተርፎን የምናወራው ታሪክ የብዙዎች ልብ የተሰበረበትና የደማበት፣ ወደፊት የሄድነውን ያህል በእጥፍ ወደኋላ የምንመለስበት፣ ቤትና ቤተሰብ የሚፈርስበት፤ ሰው መሆን የሚፈተንበት ከባዱ የህይወት ፈተና ነው።

ነገር ግን ሁሉም  የንግግርና የሰላምን ዋጋ የሚረዳው እንደ ህጻን ልጅ ሳቱ እጁን  ሲያቃጥለው ብቻ መሆኑ ዛሬም ድረስ የሚያሳዝን ነው፡፡  የሰላምን ዋጋ በማቅለል  ለጦርነት ከምናወጣው ሃይል፣ በጀትና አቅም ትንሹን መደማመጥ ለሰላም፤ ለጦርነት  የምንሄደውን ሩቅ መንገድ ያህል አጭሩን ለሰላም ለማዋል  ምን ዓይነት አዚም ነው የተጫነን?

ሰላምን እስካመጣ ድረስ ከግማሽ በላይ መንገድ እንኳ ቢሆን ሄደን ችግርን በስክነት፣ ከእልህ በዘለለና መፍትሔ ባለው መልኩ በመነጋገር  ትውልድን የማዳን ኃላፊነትም መወጣት ለምን አቃተን?

ለሰላም ያጠረ ለጸብ የረዘመ እጅ ማንንም አይጥቅምም። ለሰላም ምንጊዜም በሚዛናዊነት ሁሉንም ሊያዳምጥ የሚችል ክፍት ጆሮ፣ የማይዝል እጅ፣ የተገራ አንደበትና ቀና ልብ  ያስፈልጋል።

መነጋገርና መወያየትን ቅድሚያ በመስጠት፤ አትራፊውን መንገድ መከተል መሸነፍ ሳይሆን ለሰላም ዋጋ መስጠትና ለህዝብ ህልውና ቅድሚያ መስጠት ስለሆነ ከህዝባዊ ውይይቶች የሚገኙ ግብዓቶች ሀገርን ያተርፋሉ፡፡ ከመነጋገር አልፎ መደማመጥ፤ ያደመጡትን ደግሞ ወደሚጠቅም ተግባር በመቀየር ህዝባዊ ውይይቶችን ለሰላም መስፈን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here