ንጹሐንን ዋጋ እያስከፈለ ያለዉ ጦርነት

0
158

በመካከለኛው ምሥራቅ ፍልስጤም ለሁለት ተከፍላ የአረብ እና የአይሁዳውያን ሀገራት እንዲመሠረቱ ከተወሰነ በኋላ ፍጥጫ እና ጦርነት በተለያየ መጠን ሞቅ፣ ቀዝቀዝ እያለ ሲካሄድ ዘመናት ተቆጥረዋል። በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጥቃት እና ጦርነት እየተደጋገመ የቀጠለ ቢሆንም፣ በቅርቡ የተከሰተው ግን ከሌሎች ጊዜያት የተለየ በመሆኑ አሳሳቢ ሆኗል።

የፍልስጤሙ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ሐማስ የፈጸመው ድንገተኛ፣ የተቀናጀ እና መጠነ ሰፊ ጥቃት እስራኤላውያንን አስደንግጦ ቁጣን ቀስቅሷል። ሐማስ በእስራኤል ይዞታዎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ከማዝነብ ባሻገር ከሌላው ጊዜ በተለየ ታጣቂዎቹን ወደ እስራኤል አስርጎ በማስገባት ከባድ ጉዳትን አድርሷል።

እስራኤልም በአጸፋው በጋዛ ሰርጥ ላይ ተከታታይ የአየር ጥቃት በማካሄድ በርካታ ፍልስጤማውያንን ከመግደሏ ባሻገር ከባድ ውድመትን አድርሳለች። ይህ የሐማስ ጥቃት እና የእስራኤል የበቀል እርምጃ እስከ ምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ባይታወቅም፣ በአጭሩ የሚገታ አይመስልም። ለመሆኑ ለዚህ የፍልስጤም – እስራኤል ፍጥጫ እና ጦርነት መነሻው ምንድን ነው? ሊያስማሟቸው ያልቻሉት ጉዳዮችስ የትኞቹ ናቸው።

ግጭቱ እንዴት እና መቼ ጀመረ?

በዮርዳኖስ ወንዝ እና በሜዲትራኒያን ባሕር መካከል ያለው እና በኦቶማን ቱርኮች ቁጥጥር ስር የነበረው የፍልስጤም አካባቢ በሙስሊሞች፣ በአይሁዶች እና በክርስቲያኖች ዘንድ እንደ ቅዱስ ቦታ የሚታይ ነው። አካባቢውም በአብዛኛው በአረቦች እና በሌሎች ሙስሊም ማኅበራሰቦች የተያዘ ሲሆን፣ አይሁዶችም ነበሩበት። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነትን ተከትሎ የኦቶማን ቱርኮች ግዛተ መንግሥት ሲፈራርስ፣ በወቅቱ የነበረው የዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ብሪታኒያ (እንግሊዝ) የፍልስጤምን ግዛት እንድታስተዳድር ውክልና ሰጠ። በተለያዩ ጊዜያት ብሪታኒያ በአካባቢው ላሉ አረቦች እና አይሁዳውያን የሚፈልጉትን እንደምታደርግ ቃል ብትገባላቸውም አንዱንም ባለመፈጸሟ ቅሬታ እና ውጥረት ተፈጥሯል።

አረቦች እና አይሁዳውያኑ በየበኩላቸው ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት ጥረት ሲያደርጉ በአረብ ብሔርተኞች እና በአይሁድ ጽዮናውያን መካከል ያለው ፍጥጫ ተባብሶ በሁለቱም ወገኖች በኩል ባሉ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች ተከሰቱ። በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር 1920ዎቹ እና 1940ዎቹ አውሮፓ ውስጥ ከሚደርስባቸው ጭቆና በመሸሽ እንዲሁም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአይሁዳውያን ላይ ከተፈጸመው የጅምላ እልቂት በኋላ መጠለያ ሀገር ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚገቡት አይሁዶች ቁጥር ጨመረ። በዚያ ወቅትም በአይሁዳውያን እና በአረቦች መካከል ግጭቶች እየጨመሩ ሲመጡ በብሪታኒያ አስተዳደር ላይም ተቃውሞው ተጠናከረ።

በርካታ ፍልስጤማውያን የአይሁዶችን እርምጃ በመቃወማቸው በአካባቢው ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ የአጎራባች አረብ ሀገራት ወታደሮችም ፍልስጤማውያንን በመደገፍ በጦርነቱ ተሳታፊ ሆኑ። በዚህም ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ቀያቸውን ጥለው ሸሹ ወይም ለቀው እንዲሄዱ ተገደዱ። ይህንንም ክስተት ፍልስማውጤያን “አል ናቅባ” ወይም “መቅሰፍት” ሲሉ ይጠሩታል።

በ1967 እ.አ.አ በተካሄደው የአረብ – አስራኤል ጦርነት እስራኤል ከፍልስጤም ግዛቶች ባሻገር የጎረቤት አረብ ሀገራትን ይዞታዎች በወረራ ለመያዝ ችላለች። ለስድስት ቀናት በተካሄደ ጦርነት እስራኤል በዮርዳኖስ እጅ የነበረውን ምሥራቃዊ የኢየሩሳሌም ክፍል፣ ግብፆች ያያዙትን የጋዛ ሰርጥን፣ የሶሪያን አብዛኞቹን የጎላን ተራሮችን እና የግብፅን ሲናይ ባሕረ ገብ መሬትን በእጇ አስገባች።

የእስራኤል ምሥረታ

በአይሁድ ትውፊት መሠረት አሁን እስራኤል የምትገኝበት ቦታ እግዚአብሔር ለአብርሃም እና ለዘሩ ቃል የገባው ምድር እንደሆነ ይታመናል። አካባቢው በጥንታዊው ዘመን በተለያዩ ኃይሎች ተወርሮ የቆየ ሲሆን፣ ስፍራውን ፍልስጤም ብለው የሰየሙት ሮማውያን እንደሆኑ ይነገራል። ከዚያም በኋላ በተካሄዱ ወረራዎች እና ማስገበሮች በአካባቢው በርካታ ለውጦች ተካሂደዋል። እስራኤል እና ፍልስጤም ያሉበትን የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢን ይቆጣጠሩ የነበሩት ኦቶማን ቱርኮች በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሲሸነፉ አካባቢው በብሪታኒያ ቁጥጥር ስር ገባ። መሬቱም ብዙኃን አረቦች እና አናሳ አይሁዳውያን የሚኖሩበት ነበር።

በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል አሁን ድረስ የዘለቀው ፍጥጫ የተባባሰው ብሪታኒያ በፍልስጤም ውስጥ የአይሁድ ሕዝቦች ሀገር መመሥረት የሚለውን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ እርምጃዎችን መውሰድ ስትጀምር ነው። አይሁዶች አካባቢው የአያቶቻቸው ርስት መሆኑን ሲያምኑ፣ የፍልስጤም አረቦች ደግሞ ግዛቱ የራሳቸው መሆኑን በመግለጽ ሐሳቡን ተቃወሙት።

ፍልስጤምን በሚመለከት የተዋቀረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮሚቴ በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር መስከረም 03 1947 በጠቅላላ ጉባኤው ባቀረበው ሪፖርቱ ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ የአይሁዳውያን ሀገር የመመሥረት ጥያቄ “መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ታሪካዊ” ምንጮችን መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሶ ነበር። በተጨማሪም የብሪታኒያ መንግሥት በፍልስጤም ውስጥ የአይሁዶች “ሀገር” መመሥረትን እንደሚደግፍ በ1917 እ.አ.አ በአወጣው የባልፎር ድንጋጌ ላይ አሳውቆ ነበር።

በአውሮፓ ውስጥ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ጊዜ እና ከዚያም በፊት በናዚዎች አማካይነት በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ አይሁዶች ላይ በተፈጸመው የጅምላ እልቂቶች ምክንያት ሀገረ እስራኤል እንድትመሠረት እና ዕውቅና እንዲሰጣት ግፊት ሲደረግ ነበር። በአረብ ብሔረተኞች እና በጽዮናዊነት እንቅስቃሴ አራማጆች መካከል ያለውን መካረር ለማርገብ ያልቻለችው ብሪታኒያ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወሰደችው። የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤም በኅዳር 29 ቀን 1947 እ.አ.አ ፍልስጤም ለሁለት ተከፍላ ነጻ የአረብ እና የአይሁድ ሀገራት እንዲመሠረቱ የቀረበው ሐሳብ ጸደቀ። ይህን ተከትሎ ብሪታኒያ በፍልጤስም ላይ የነበራት ውክልና ከመጠናቀቁ አንድ ቀን በፊት ግንቦት 14 ቀን 1948 እ.አ.አ አይሁዳውያን የእስራኤልን ነጻ ሀገርነትን አወጁ። በቀጣዩ ቀንም እስራኤላውያን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርበው ከአንድ ዓመት በኋላ ተቀባይነትን አገኙ።

የፍልስጤም  የተነጣጠሉ ግዛቶች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ላይ የፍልስጤማውያኑ አረብ ግዛት የትኞቹን አካባቢዎች እንደሚያካትት በዝርዝር ቢያመለክትም፣ የመጀመሪያው የአረብ – እስራኤል ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ ነበር ግዛታቸውው በግልጽ የለየው። በዚህም በመካከላቸው የእስራኤል ግዛት የሚለያቸው ግራ እና ቀኝ በ45 ኪሎ ሜትሮች የተነጠሉ ሁለት የፍልስጤማውያን ግዛቶች ተፈጠሩ። አንደኛው ምሥራቃዊ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ዌስት ባንክ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የጋዛ ሰርጥ ሆነ። ለረጅም ጊዜ በእስራኤል አገዛዝ ስር የቆየው እና አሁንም የአየር እና የባሕር እንቅስቃሴዎቹን እስራኤል የምትቆጣጠረው የጋዛ ሰርጥን ደቡባዊ ድንበር በእጇ አስቀርታ ለፍልስጤማውያን የመለሰችው በአውሮፓውያኑ 2005 ነበር።

በአሁኑ ወቅት የጋዛ ሰርጥ በፍልስጤም አንጃዎች እና በእስራኤል መካከል የተፈረሙ ስምምነቶችን በማይቀበለው በእስላማዊው ቡድን ሐማስ አስተዳደር ስር ነው የሚገኘው። በሌላ በኩል ደግሞ ዌስት ባንክን የሚያስተዳድረው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው እና ዋነኛው ፓርቲ ፋታህ ሲሆን ይህም የፍልስጤም መንግሥት ተብሎ ነው የሚጠራው።

በመንግሥታቱ ድርጅት አማካይነት ፍልስጤም ለሁለት ተከፍላ የአረብ እና የአይሁድ ሀገራት እንዲመሠረቱ ከወሰነ በኋላ እስራኤል የራሷን መንግሥት መሥርታ በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት አንዷ ለመሆን ችላለች። ፍልስጤም ግን እስካሁን ሙሉ ለሙሉ ለዚህ አልታደለችም። እስራኤል በተመሠረተች በዓመት ውስጥ እንደ አንድ ሀገር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ስትሆን፣ ፍልስጤም ግን “አባል ያልሆነች ታዛቢ ሀገር” በመሆን የድርጅቱ ሙሉ የአባልነት ቦታን አላገኘችም። እንደ ሀገር የመንግሥታቱ ድርጅት ሙሉ አባል ለመሆን ጥያቄ ብታቀርብም ከፀጥታው ምክር ቤት አባላት በቂ ድጋፍ ባለማግኘቷ ጉዳይዋ ተንጠልጥሎ ቀርቷል። ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አባል ከሆኑት 193 ሀገራት መካከል 138ቱ ወይም ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የፍልስጤምን ሀገርነት በይፋ ዕውቅና ሰጥተዋል።

የማያስማሟቸው ነገሮች

ለዘመናት በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ስምምነት እንዳይደረስ ምክንያት የሆኑ በርካታ ምክንያቶች አሁንም በመካከላቸው እንቅፋት ሆነው አፋጠዋቸው ይገኛሉ። ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ፍልስጤማውያን ስደተኞች በተለያዩ ሀገራት ውስጥ ተበትነው የሚገኙት ስደተኞች ጉዳይ አንዱ ነው። ዋነኛው ፍልስጤማውያን ፖለቲካ ፓርቲ ፒ ኤል ኦ 10 ነጠብ ስድስት ሚሊዮን ዜጎቹ በስደት እንዳሉ ይጠቅሳል። ከእስራኤል ጋር ለመስማማት አሁን እስራኤል ወደሚባለው ግዛት መመለስ አለባቸውም ይላል። አስራኤል ደግሞ ይህ የአይሁድ ማንነቷን አደጋ ላይ ይጥላል በማለት አትቀበለውም።

ሁለተኛው የእስራኤላውያን ሰፈራዎች ናቸው፡፡ እስራኤል ከ1967 እ.አ.አ ጦርነት በኋላ በወረራ በያዘቻቸው ፍልስጤማውያን ግዛቶች በሚባሉት በምሥራቅ ኢየሩሳሌም እና በዌስት ባንክ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አይሁዳውያንን አስፍራለች። በእስራኤል መንግሥት የተገነቡት እነዚህ የሰፈራ አካባቢዎች በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገ ወጥ ተብለው ተነቅፈዋል። ፍልስጤማውያን አይሁድ ሰፋሪዎች ከግዛታቸው እንዲወጡ ቢጠይቁም እስራኤል ሳትቀበለው ቆይታለች።

ሦስተኟው የድንበር ጉዳይ ነው፡፡ ፍልስጤማውያን የተባበሩት መንግሥታት ሁለቱ ሀገራት እንዲመሠረቱ ሲወስን ያስቀመጣቸው ግዛቶች እንዲከበሩ፣ ለዚህም እስራኤል ከ1967ቱ የአረብ – እስራኤል ጦርነት በፊት ወደነበረ ይዞታዋ እንድትመለስ ይፈልጋሉ። እስራኤል ግን ይህንን አትቀበለውም። አራተኛው የማይስማሙበት ምክንያት የኢየሩሳሌም ባለቤትነት ጉዳይ ነው፡፡ እስራኤል ከተማዋ ሉዓላዊ ግዛቷ እንደሆነች እና በ1967ቱ ጦርነት ምሥራቃዊውን ኢየሩሳሌም ከተቆጣጠረች በኋላ ኢየሩሳሌም ዋና ከተማዋ መሆኗን በይፋ ብትገልጽም ዓለም አቀፍ ዕውቅና አላገኘችም። ፍልስጤማውያን ደግሞ ምሥራቅ ኢየሩሳሌም መዲናቸው እንድትሆን ይፈልጋሉ።

በጥቅምት 2020 እ.አ.አ የእስራኤል ፍርድ ቤት ውሳኔ ለምሥራቅ እየሩሳሌም ቅርብ በሆነችው ሼክ ጃራህ ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ፍልስጤማውያን ተገደው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ በ2021 ቦታው ለአይሁድ ቤተሰቦች ተላልፏል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል። ፍልስጤማውያኑ ጉዳዩን ለፍርድ ቤት ይግባኝ ቢሉም ምንም ምላሽ ሳያገኙ ቀሩ። በአረቦቹም ሆነ በምዕራባውያንም በኩል ፍትሕ ያጡት ፍልስጤማውያን እንደዚህ እየተንገላቱ ባሉበት ጊዜ ጥቅምት 7 ቀን 2023 ሐማስ በርካታ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል በማስወንጨፍ ከባድ ጉዳት አደረሰ፤  ይህም እንደገና ፍልስጤማውያንን ሌላ እልቂት ውስጥ አስገባቸው።

በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ለሞት ተዳረጉ። ይህ ጉዳት እየጨመረ በመሄዱ ለበርካቶች ህይወት መጥፋት መንስኤ ሆኗል። ከጥቃቱ በኋላም ሁልጊዜም ከእዝራኤል ጎን የማትጠፋው አሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሐማስን በማውገዝ ለእስራኤል ጠንካራ የድጋፍ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ ለእስራኤል አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የጦር ኃይልም ወደ አካባቢው ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሌላኛው (በተቃራኒ)ጎራ ደግሞ የኢራኑ ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት የሆኑት አያቶላ ኾሚኒ ጥቃቱን ተከትሎ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ (x) ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “ግቡ ጽዮናውያንን ከምድረ ገጽ ማጥፋት ነው” ማለታቸው ጉዳዩ በሁለት ጎራ ተከፍሎ የኃያላኑ ጉልበት መለካኪያ መሆኑን ያመላክታል።

በእስራኤል እና የፍልስጤም ቡድኖች መካከል ለሚከሰቱት ግጭቶች ምዕራባውያን የያዙት አቋም እና አረቦች እና ሌላው ዓለም ወጥ አቋም አለመያዝ የሰላማዊ ፍልስጤማውያን ሞት በየጊዜው እያሻቀበ እንዲሄድ አድርጎታል። በቅርቡ የምዕራባውያንን አቋም የተቹት ጋዜጠኞች፣ የፖቲካ ተንታኞች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ምዕራባውያን በአንድ ዓለም ውስጥ ሁለት የተለያዩ አቋሞችን መያዛቸው ኢ-ፍትሐዊነታቸውን እንደሚያሳብቅ ገልጸዋል። አሜሪካ መሩ የምዕራብ ዓለም በሩሲያ ተወራለች ላሏት ዩክሬን የሚሰጡትን ድጋፍ ያክል እንኳን ባይሆን ለፍልስጤም ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ ዳተኛ መሆናቸው ማንነታቸውን ያጋለጠ ሆኗል ነው የሚሉት።

እንደ ተመድ ያሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት ጉዳዩን ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉት፣ አሜሪካ ተቀናቃኞቿን ለመክሰስ የምትጠቀምበት፣ አረቦች ከነዳጅ ዶላራቸው ጥቂት እንኳን ለስደተኞች የማያካፍሉበት እና ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የእስራኤል ከሳሽ ሆነው የሚወጡበት፣ እስራኤል ባሻት ጊዜ ሕዝቡን የምታፈናቅልበት፣ የፍልስጤማውያን ፖለቲካኞች እንኳን ወጥ አቋም ያልያዙበት የእስራኤል – ፍልስጤም ጦርነት አነሆ አሁንም ንፁሃንን ጭዳ እያደረገ ዛሬ ላይ ደርሷል። በተለይም በሀገራቸው ሀገር አልባ የሆኑ ምስኪን ፍልስጤማውያን ታጣቂዎቻቸው ነጻ ያወጡናል ብለው ተስፋ በማድረግ መሥዋዕትነት እየከፈሉ ቀጥለዋል።

በዩክሬን ሰበብ ከምዕራባዉያን መንግሥታት ጋር ተዘዋዋሪ ጦርነት የገጠመችዉ ሩሲያ የፍልስጤምን እና የእስራኤልን  የዘመናት ጠብ፣ ግጭት እና ጦርነት ለማስቆም መሠረቱ የሁለት መንግሥታት ድርድር መቀጠል ነዉ ትላለች። የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እንዳሉት ያሁኑ ግጭት ከቆመ በኋላ ድርድሩ መቀጠል አለበት። ሩሲያ ባንድ ወቅት ፍልስጤምና እስራኤልን ለማደራደር ተሰይሞ የነበረዉ «አራትዮሽ» የተባለዉ ቡድን አባል ነበረች። የፈየደችው ግን የለም። የቱርክ ፕሬዝደንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ግን መካከለኛዉ ምሥራቅን እስካሁን፣ አሁንም ሆነ ምናልባት ወደፊት የሚያወድመዉ ጦርነት እና ግጭት የሚቆመዉ የእስራኤል – ፍልስጤም ጠብ ሲፈታ ነዉ ባይ ናቸዉ።

ይህ በእንዲህ እያለ የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ተከታታይ የሰው አልባ አውሮፕላን እና የሮኬት ጥቃቶችን መፈፀሙን ገልጿል፡፡ እስራኤል በቅርቡ የቡድኑን ከፍተኛ አዛዥ መግደሏን ተከትሎ እየተጠበቀ ያለው የበቀል እርምጃ ገና ይቀጥላል ሲልም አስጠንቅቋል።

ሂዝቦላህ በሰሜን እስራኤል በአክሬ አቅራቢያ የሚገኙ ሁለት የጦር ሰፈሮችን በሰው አልባ አውሮፕላኖች ማጥቃት መጀመሩን እና በሌላ ቦታ በእስራኤል ወታደራዊ ተሸከርካሪ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተናግሯል። የእስራኤል ጦር በበኩሉ ከሊባኖስ የተወነጨፉ በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መለየታቸውን እና አንደኛው መክሸፉን አስታውቋል።

የሕክምና ባለስልጣናትም ጉዳት የደረሰባቸው ሰባት ሰዎች ከአካባቢው ለቀው በደቡባዊ ድንበር ከተማ ናሃሪያ ወደ ሚገኝ ሆስፒታል መወሰዳቸውን፤ አንዱም አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የእስራኤል ጦር እንደገለጸው በርካታ ንጹሃንን ያቆሰለው አደጋ የደረሰው ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለመምታት የተወነጨፈ ተተኳሽ ዒላማውን ስቶ መሬት በመውደቁ ነው፡፡ ይሁንና ክስተቱ አሁንም በምርመራ ላይ እንደሚገኝ አመላክቷል፡፡

የእስራኤል ጦር በሰጠው መግለጫ በአክሬ አካባቢ የማንቂያ ደወል ድምፅ እንደተሰማ እና ነገር ግን ያ የውሸት ማንቂያ ሆኖ መገኘቱን ገልጿል፡፡ የአየር ኃይሉ በደቡብ ሊባኖስ ሁለት የሂዝቦላህ ተቋማትን መምታቱንም ተናግሯል። የሂዝቦላህ አዛዥ ፉአድ ሹክር እና  በቅርቡ በቴህራን ለተገደለው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሐማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒዬህ አጸፋ  እንደሚመልሱ ሂዝቦላህ እና ኢራን ዛቻ መሰንዘራቸውን ተከትሎ መካከለኛው ምሥራቅ ወደ ሙሉ ጦርነት ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት እየጨመረ መጥቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በወሰደችው የሚሳኤል ጥቃት ንጹሐን እና የተጠለሉ ተፈናቃዮች ሰለባ ሆነዋል ሲል አልጄዚራ ዘግቧል፡፡ ጥቃት የደረሰበት ስፍራም በደቡባዊ ጋዛ የሚገኘው ካን ዩኒስ የተሰኘው ነው፡፡ ከጥቃቱ ባሻገር የእስራኤል ባለስልጣናት ረሀብን እንደ መሣሪያ ስለመጠቀም የሚከተሉትን መንገድ እንዲያቆሙ ኢራን አሳስባለች፡፡ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዳቪድ ላሚ የእስራኤሉ ፋይናንስ ሚኒስትር  ቤዛሌል ስሞትሪች “የጋዛን ሕዝብ በሙሉ በርሃ እንቀጣዋለን” ማለታቸውን ኮንነዋል፡፡ ይህም በዓለም ዓቀፍ ሕግ የጦር ወንጀል መሆኑን ገልጸዋል፡፡  የሐማስ መሪ መገደሉን ተከትሎ በአስፈላጊው ሰዓት ኢራን ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቃለች፡፡

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here