የአፍሪካ አንደበት
ከሰባቱ የጥበብ ዘርፎች አንዱ የሆነው ፊልም የሀገራት ጉልበት እና አቅም ማሳያ ነው። ሀገራት ይህንን የፊልም ጉልበት ተጠቅመው ዓለም አቀፍ ገጽታቸውን ለማስተዋወቅ ተጠቅመውበታል። ፊልም የፓለቲካዊ ዲፕሎማሲ መሳሪያም ነው። አሜሪካ እና ሕንድ እንደ ሀገራቸው መከላከያ ሠራዊት ታላቅ ጉልበታም መሳሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል።
ለአሜሪካ ሆሊውድ፣ ለሕንድ ቦሊውድ፣ ለናይጀሪያ ደግሞ ኖሊውድ አላት። አፍሪካዊቷ ናይጀሪያ እንደ አሜሪካ እና ሕንድ ሁሉ የፊልም ኢንዱስትሪ ከፍታለች። ኢንዱስትሪውንም ከሌሎች ሀገራት ስም አወጣጥ እና ልምድ በመከተል ኖሊውድ ብላዋለች። የናይጀሪያው ኖሊውድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ፊልሞችን በመስራት የአሜሪካውን ሆሊውድን በልጦ ከሕንዱ ቦሊውድ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ፊልም በማምረት ኖሊውድ ሁለተኛ ደረጃ ተጠቃሽ ኢንዱስትሪ ነው። በማምረት ሁለተኛ ይሁን እንጅ በጥራት እና በገቢ በኩል ከሆሊውድ እና ቦሊውድ ያንሳል። የናይጀሪያ ፊልም ኢንዱስትሪ ኖሊውድ 590 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በዓመት ያስገኛል። ኢንዱስትሪው በየጊዜው ከዘመኑ ጋር ራሱን እያሳደገ ተጒዟል።
እ.ኤ.አ በ2010 1,074 ፊልሞችን የሰራው ቦሊውድ በ2023 በዓመት እስከ 2,500 ፊልሞችን ለተመልካች እንዳደረሰም ይነገርለታል። ለሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል እንደፈጠረም ጭምር ይነሳል። በኖሊውድ ኢንዱስትሪ ውስጥ ተዋናዮች አንድ ፊልም ላይ ሲሰሩ በአማካይ ከአንድ እስከ ሦስት ሺህ ዶላር ይከፈላቸዋል። የሀገሪቱን ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት አምስት በመቶ ድርሻም ይዟል። እንደ አሮፓዊያን አቆጣጠር በ2015 ኖሊውድ የሰራቸው ፊልሞች 59 በመቶ ለዓለም ሕዝብ መድረስ የቻሉ ነበሩ። በፊልም አሰራር በኩልም ዘርፉ በማደግ ላይ ነው። ቀደም ሲል ኮሜዲ እና ድራማ በመስራት ይታወቅ የነበረው ኖሊውድ አሁን አስፈሪ የሆረር፣ ታሪካዊ ድራማ፣ ሙዚቃዊ እና አኒሜሽን ፊልሞችን እየሰራ ነው። ኦኬ አፍሪካ ድረገጽ ኖሊውድ በአሁኑ ጊዜ ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ገንዝብ የሚንቀሳቀስበት ኢንዱስትሪ ነው ሲል ይገልጸዋል።
የናይጀሪያ ፊልም ጉዞ መነሻው ቴያትር ነው። ጊዜው ደግሞ እ.አ.አ 1920ዎቹ ነው። የናይጀሪያ ቅኝ ገዢ የነበረችው እንግሊዝ የፊልም ኩባንያዎችን ከፍታ ትሰራ ነበር። በወቅቱም እንግሊዝ ለናይጀሪያዊያን ፍጆታ የሚሆኑ ፊልሞችን ትሰራ ነበር። በ1926 ፓላቬር፣ በ1935 ሳንደርስ ኦፍ ዘሪቨር የተሰኙ ፊልሞችን በመስራት ራሳቸው ናይጀሪያዊያንም ጭምር በተዋናይነት እንዲሰሩ ታደርግ ነበር።
እነዚህንም ፊልሞች በትልልቅ አዳራሾች እና ሰው በብዛት በሚገኝባቸው ቦታዎች ታሳይ ነበር። በዚህ ጊዜ የሃይማኖት ሰባኪዎች ፊልምን እንደ መሳሪያ ይጠቀሙበት ስለነበር ሃይማኖት ትልቅ ጉልበት ነበር። ሲኒማ በናይጀሪያዋ ከተማ ሌጎስ የማህበራዊ ሕይወት መስተጋብር መግለጫም ሆኖ ነበር። ይህን ተከትሎ ትልልቅ የንግድ ሲኒማ ቤቶች በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተቋቋሙ። ተጓዥ የቴያትር ቡድኖችም በስፋት ስራ ጀመሩ። ጭውውቶች ለሕዝብ በብዛት ይሰሩ ነበር። ቤተክርስቲያናት፣ ፍርድ ቤቶች እና ተመልካቾችም በገንዘብ መደገፍ እና ማስተዋወቅ ጀመሩ።
የፊልም መቅጃ መሳሪያዎች መተዋወቅ ሲኒማን ለብዙዎች ማድረስ አስቻለ። ናይጀሪያ በ1960 እ.አ.አ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ስትወጣ የፊልም ስራዎች ማደግ፣ መስፋፋት የጀመሩበት ጊዜ ሆነ። ሲኒማ እና ቴያትር ቤቶች ከነጻነት ማግስት በሀገሪቱ በስፋት ተከፈቱ። ይሁን እንጂ የሕንድ፣ አሜሪካ እና ቻይና ፊልሞችም በስፋት በናይጀሪያ የሚታዩበት ጊዜ ነበር። በ1970ዎቹ የውጪ ሀገር ተዋንያን በዝናቸው የገዘፉበት ጊዜ ቢሆንም፤ ለናይጀሪያ ደግሞ የሲኒማን ባህል ያስተዋወቀ ጊዜ መጣ። በ1972 የሀገሪቱ መንግሥት የውጪ ሀገር ፊልሞችን ወረራ ለመከላከል ድንጋጌ አወጣ። በዚህም የውጪ ሀገራት ዜጎች የመሰረቷቸውን 300 ሲኒማ ቤቶች የሀገሪቱ መንግሥት እንዲያስተዳድር ፈቀደ። ይህንን ተከትሎም ናይጀሪያዊያን በስፋት በፊልም ስራዎች መሳተፍ ጀመሩ። ተወዳጅ ታሪኮች እና መጽሐፍት እንዲሁም ድርሰቶች ወደ ፊልም መቀየር ጀመሩ። ፊልም ማየት በዚህ ጊዜ የወቅቱ ፋሽን ነበር። ብዙ ሰዎች ፊልሞችን ለመመልከት ትኬት ቆርጠው የሚሰለፉበት ጊዜ ሆነ። የሲኒማው ዘርፍ ለብዙዎች እንጀራም መዝናኛም ሆኖ ቀጠለ።
ብዙ ናይጀሪያዊያን ቴሌቪዥን በመግዛታቸው የፊልም ማየት ፍላጎትም አብሮ አደገ። የሲኒማ እና ቴያትር አዘጋጆች የሀገር ውስጥ ፊልሞችን እና ቴያትሮችን በመስራት በቴሌቪዥን ማሰራጨታቸውን ገፉበት። የሀገሪቱ መንግሥት በ1972 ያወጣው ድንጋጌም የውጪ ፊልሞችን ማሳየትን አያበረታታም። ዝቅተኛ መጠን ያላቸው የውጪ ሀገራት ፊልሞች ብቻ ነበሩ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚተላለፉት። አብዛኛውን ድርሻ የሀገር ውስጥ የፊልም እና ቴያትር ስራዎች ይተላለፉበት ያዙ። ይህ ግን ብዙም አልቆየም ቴክኖሎጂ እና ዘመን የፊልሙን ዘርፍ መፈተን ጀመረ።
ሕገወጥ የቪዲዮ ንግድ ቤቶችም ማቆጥቆጥ ጀመሩ። ስራዎችን ማባዛት፣ መሸጥ ፣ መሸቀጥ እና ዝርፊያዎች ተጀመሩ። እ.አ.አ 1990ዎቹ ለናይጀሪያ ፊልም ዘርፍ የፈተና ጊዜ ነበር። ከውጪ ፊልሞች ወረራ ነጻ የወጣው የሀገሪቱ ፊልም ዘርፍ በሕገወጥ ፊልም አከራዮች እና ቸርቻሪዎች እጅ ወደቀ። የተከፈቱ ቴያትር እና ሲኒማ ቤቶች ወደ ቤተክርስቲያንነት ተቀየሩ ሲል ኦኬ አፍሪካ ጽፏል። ቀሪዎቹ ደግሞ ተዘግተው ተቀመጡ። 1999 የናይጀሪያ ፊልም ከመነቃቃቱ ከፍታ ወርዶ ወደቀ። የተቀረጹ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን አባዝቶ መሸጥ መንገድ ላይ የሚታይ ትዕይንት ነበር። በየጎዳናው ፊልሞች እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ተባዝተው ይሸጡ ነበር። ቪዲዮ ማከራያ ቤቶች እንደ አሸን የፈሉበት ወቅት ነበር። በዝቅተኛ ዋጋ ፊልሞችን ቤት ውስጥ ማየት ሲቻል ማን ሲኒማ ድረስ ይሄዳል? ሲኒማ ቤቶች የተዘጉት ለዚህ ነበር። ቀደም ሲል በድንጋጌ የተከለከሉት የውጪ ሀገራት ፊልሞች እንደገና ተመልሰው በየቤቱ በቪኤች ኤስ እና ሲዲ አማካይነት በየቤቱ ገቡ። ገበያውን ተቆጣጠሩት። የሀገር ውስጥ ፊልሞች ደግሞ መሰራት አቆሙ። ተመልካችም እየቀነሰ መጣ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ የናይጀሪያ ፊልም ዘርፍ ስራዎችን አላቆመም። ከችግር ጋር እየተጋፋ ተጉዟል። በ2008 እ.ኤ.አ በዓመት ውስጥ 200 ፊልሞች ተሰርተዋል። ይህም ዘመን ችግሮች ያልተለዩት ሆነ። ዝርፊያ፣ የስርጭት ችግር፣ ከመንግሥት ድጋፍ ማጣት እንዲዳከም አድገውታል። የአሁኑን ኖሊውድ የፈጠሩት ወጣት እና ጠንካራ የፊልም ሰዎች ብቅ ያሉት በ2000 ዎች ውስጥ ነው። እ.ኤ.አ በ2002 የኒዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ ኖርሚስቱ ኦኒሽ ናይጀሪያ ሌጎስ በተገኘበት ጊዜ የሀገሪቱ ዜጎች ፊልም ለመስራት ያላቸውን ጥረት እና አቅም ተመለከተ። ናይጀሪያ ያላትን የታሪክ እና ብዝኀ ባህል የተመለከተው ጋዜጠኛው “ኖሊውድ” ሲል የሀገሪቱን የፊልም ኢንዱስትሪ ስም አወጣለት። ስም ሆኖ ቀረ።
ኪንግ ኦፍ ቦይስ፣ ላይን ኸርት፣ ሳይቴሽን፣ ፋር ፍሮም ሆም፣ ብለድ ሲስተርስ፣ ኦሎቱር፣ ዘ ብላክ ቡክ፣ ሊቪንግ ኢን ቦንዴጅ፣ ዘዊዲንግ ፓርቲ፣ ቺፍ ዳዲ፣ ኦሞ ጊቴ፣ ኦክቶበር ፈርስት፣ እና ሌሎችም ተወዳጅ ፊልሞች ኖሊውድን ያስታውሱታል።
ካኑሪ፣ ዮሩባ፣ ሀውሳ፣ ኢግቦ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን በመጠቀም የኖሊውድ ፊልሞች ይሰራሉ። እንግሊዘኛ እና ሀውሳ ቋንቋዎች ብዙ ተመልካቾችን እንዲያገኙ ምክንያቶች ሆነዋል። ብዙ ተመልካቾችን ማግኘታቸው ደግሞ ብዙ ፊልሞች እና ታሪኮች ወደ ፊልምነት እንዲመጡ አግዟል። የኖሊውድ ፊልሞች በኔትፍሊክስ ዓለም አቀፍ የፊልም ማሰራጫ መተላለፋቸው ሌላው የኖሊውድ እድገት ምክንያት ነው። ይህንን ተከትሎም ፊልሞችን በጥራት ለመስራት ፉክክር እና እድገት ተመዝግቧል። አማዞን እና ዩቱዩብ አሁንም ሌሎች የፊልም ማሰራጫ መንገዶች ናቸው። በዚህም ምክንያት የናይጀሪያ ፊልሞችን መላው ዓለም ለማየት ዕድል አግኝቷል።
በማምረት በዓለም ሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው ቦሊውድ ስጋትም ተስፋም አለበት። ስጋቱ አሁንም የገንዘብ ችግሮች አሉበት። አሁንም የጥራት ቁጥጥር መመሪያ የለውም። ተዋናዮች ተጠቃሚ አይደሉም። የቅጂ መብት አሁንም አይከበርም። የናይጀሪያ ፊልም ኢንዱስትሪ በአንጻሩ መልካም አጋጣሚዎችም አሉት። አሜሪካ በፊልሞቿ የምታዝናና ብቻ የሚመስለው ሰው ካለ ተሸውዷል። ፊልም ከማዝናናት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ማንነትን ማሳያ ነው። ኖሊውድ የአፍሪካን ታሪክ ለመላው ዓለም፤ በዓለም ቋንቋ የመንገር አቅም ፈጥሯል። ኖሊውድ ከናይጀሪያ ባሻገር ድንበር ተሻግሮ አፍሪካ እና ዓለምን የመድረስ እድል አለው። የአፍሪካን ታሪክ በአዲስ ገጽታ የማሳየት ወርቃማ እድልም አለው። አፍሪካዊያን ታሪካቸው ገና ድንግል ነው። ይህንን ድንግል ታሪክ ለመላው ዓለም ለማሳየት ኖሊውድ ይችላል።
ናይጀሪያ 232 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ አላት። የሀገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ እንግሊዘኛ ይሁን እንጂ ከ500 በላይ ቋንቋዎች ይነገሩባታል። ከ200 በላይ ብሔሮች አሏት። ይህ ለሀገሪቱ የፊልም እድገት እንደ እድል የሚቆጠር ነው።
ማን ነበር የኢትዮጵያ ሲኒማ ቤቶች ጭራሽ አነቃቂ ንግግር ማድረጊያ ሆኑ ያለው?
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም