የአማራ ክልል የ2015 እስከ 2016 ዓ.ም ከነሐሴ እስከ ነሐሴ የአንድ ዓመት ጉዞ ዋነኛ መገለጫው የሰላም መታጣት፣ የደኅንነት መታወክ፣ ነጻነት አልባ እንቅስቃሴ ስለመሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች የየዕለት መወያያ ዋና ጉዳይ ነው:: ይህ የግጭት አዙሪት አንዴ ሞቅ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ እያለ አሁንም ድረስ ቀጥሏል:: በጥቅሉ አሁንም ድረስ በቀጠለው ግጭት በርካታ ሰብዓዊ ጉዳት ደርሷል:: ይህንን ችግር ለመፍታትም የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥታት እየደረሰ ካለው ሰብዓዊ ኪሳራ ሕዝቡን ለመታደግ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን በማስተጋባት ላይ ናቸው:: ዋነኛ ትኩረታቸውን ሰብዓዊ መብት ላይ አድርገው የሚሠሩ አካላትም መፍትሄ የራቀው ግጭት በርካታ ንጹሀንን ለሞት እና ለተለያዩ ጉዳቶች እየዳረገ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት አረጋግጠዋል::
የጠብመንጃ ጩኸት ባልተለየው በዚህ ዓመት የደረሰው ምጣኔ ሐብታዊ እና ማኅበራዊ ምስቅልቅልም ከፍተኛ ነው:: በተለይ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት የክልሉን የመልማት አቅም በእጅጉ በሚያሳድገው የመንገድ ዘርፍ ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ ሆኖ ይነሳል:: ከአዴት ከተማ – ሰከላ – ፈረስ ቤት የሚያገናኘው 62 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ መቆሙን የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ አሰፋ በቅርቡ ለአሚኮ ገልጸዋል:: ከዱር ቤቴ – ሻውራ – ደለጎ መተማ ዮሐንስን የሚያገናኘው 260 ኪሎ ሜትር መንገድም በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ግንባታው ቆሟል::
በመንገድ ግንባታዎቹ ላይ የደረሰው ጉዳት በግንባታ ሥራ ላይ የነበሩ ሠራተኞች እና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ወገኖች ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል::
በግጭቱ አምስት ከተማን ከከተማ የሚያገናኙ ድልድዮች ጉዳት እንደደረሰባቸው የክልሉ ገጠር መንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) ከአሚኮ ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ ማስታወቃቸውም አይዘነጋም:: ይህም በአንድም ይሁን በሌላ የምርት ዝውውር እንዲስተጓጎል በማድረግ ለኑሮ ውድነት መባባስ መንስሄ ሆኗል:: ከአንድ ጤና ተቋም ወደ ሌላ ለተሻለ ሕክምና የሚደረገው እንቅስቃሴም እንዲስተጓጎል ምክንያት ሆኗል::
በጥቅሉ ግጭቱ እያደረሰ ያለው ጉዳት ምጣኔ ሐብታዊ ጥገኝነት እንዲጨምር፣ የክልሉ የመልማት አቅም እንዲዳከም እና የክልሉ ሁለንተናዊ ሀገራዊ አበርክቶ በእጅጉ እንዲቀንስ አስተዋጾው ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን በንግግር ለመፍታት ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የክልሉ አመራሮች ነዋሪዎችን ሲያወያዩ በተደጋጋሚ የሚሰጥ አስተያየት ነው::
በዓመቱ ያጋጠመው የሰላም እና ደኅንነት ችግር መንገዶች በተደጋጋሚ እንዲዘጉ ምክንያት መሆኑን ነዋሪዎች እና የዘርፉ አስፈጻሚ አካላት ተናግረዋል:: ይህም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዲሻክር በማድረግ ሀገራዊ አንድነት ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም:: ችግሩ በክልሉ ውስጥ እንኳ ዘመድ ወገኑን እንደፈለገ በነጻነት ተመላልሶ እንዳይጠየቅ አድርጎታል፤ የሕልፈት መርዶ በስልክ ከማሰማት ባለፈ በቦታው ተገኝቶ መቅበርም ያልተቻለበት ዓመት ነበር:: የተዘጉ መንገዶች ተከፍተው እንቅስቃሴ ሲጀመርም ዝርፊያ እና እገታ የሕዝብ ዋነኛ የዓመቱ ስጋቶች ነበሩ::
የትምህርት ዘርፉ ክልሉ ባጋጠመው የሰላም መደፍረስ በከፍተኛ ደረጃ መስተጓጎል አጋጥሞታል:: የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በዓመቱ ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ ከሚገኙ 10 ሺህ 874 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 4 ሺህ 286 ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ውጭ ሆነው ከርመዋል:: ይህም 2 ሚሊዮን 586 ሺህ 702 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዳደረጋቸው የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት አስታውቋል::
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የጤና ግብዓት በአግባቡ እንዳይቀርብ፣ የጤና መሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲስተጓጎሉ አድርጎ ስለመቆየቱ የክልሉ ጤና ቢሮ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው የዓመታዊ ሥራዎች ግምገማ ወቅት አስታውቋል:: የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አየለ አልማው በመድረኩ ተገኝተው ነበር:: በወቅቱ የጸጥታ ችግሩ የጤና ግብዓት ለማቅረብ እና ለማሰራጨት ከፍተኛ እክል እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል:: እንደ ኦክስጅን፣ ደም እና መድኃኒት ያሉ ወሳኝ የጤና ግብዓትን ለጤና ተቋማት በማሠራጨት ተገልጋዩ ተገቢውን አገልግሎት አግኝቶ እንዲመለስ ለማስቻል በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንቅፋት መሆኑንም አስታውቀዋል:: በተጨማሪም የጤና ተቋማትን እና ባለሙያዎችን ለመደገፍ፣ የጤና መድኅን እና የጤና መሠረተ ልማት ግንባታዎችን በሚፈለገው መንገድ ለማከናወን እንዳይቻል ማድረጉም ተጠቁሟል::
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የሰላም እና የጸጥታ ችግሩ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በጸጥታው ምክንያት እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ በማድረጉ ምክንያት የጤና ኤክስቴንሽን ሥራው በእጅጉ መጎዳቱን ገልጸዋል:: መድኃኒቶችን ጨምሮ ሌሎች የጤና ግብዓት ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ የጸጥታ ችግሩ ፈተና ሆኖ መቆየቱን እና አልፎ አልፎም እነዚህ ግብዓት መንገድ ላይ ይወሰዱ እንደነበር አንስተዋል። ጤና የማኅበረሰብ የሕይዎት ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም በጋራ መቆም እንዳለበት እና የጤና ተቋማትንም መጠበቅ እንደሚገባ ጠይቀዋል::
የሰላም እና ደኅንነት ችግሩ በቀጣዩ ዓመትም ቀጥሎ ክልሉን ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ እንዳያሸጋግረው ከወዲሁ መፍትሄ አመላካች ሁሉም ለሰላም በባለቤት እንዲቆም ኃላፊነትን የሚሰጡ ትኩረታቸውን ሰላም ላይ ያደረጉ ውይይቶች አሁንም እየተደረጉ ነው:: ከእነዚህ የሰላም ውይይቶች መካከል የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በክላስተር ከሚጎዳኛቸው የዞን እና የክልል የመልካም አሥተዳደር ተቋማት ጋር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ያደረገው ውይይት ይጠቀሳል::
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አቶ ጌትነት አናጋው በውይይቱ እንዳሉት ከተማዋን ካጋጠማት የጸጥታ ቀውስ ለማውጣት የሰላም እና ጸጥታ አባላትን በማደራጀት ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል:: ከተማ አስተዳደሩ በቀጣዩ ዓመት ያቀደውን የልማት ሥራ በውጤታማነት ለማከናወን ሰላምን ማስከበር ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል::
ክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ይፈጸም የነበረው የስርቆት እና እገታ ችግሮች መቀነሳቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል:: ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥም የሰላም ካውንስሉን ዓላማ በመደገፍ ይሠራልም ተብሏል::
የምሥራቅ ጎጃም ዞን የሰላም ሁኔታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን በውይይቱ የተገኙት የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አበባው በለጠ አስታውቀዋል:: የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም አስቀጥሎ ለመጓዝም የጸጥታ ኀይሉ በከተሞች ላይ ተደራጅቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል::
በቀጣይ የእርስ በርስ ግድያን ማስቀረት ዋነኛ አጀንዳ መሆኑን አስታውቀዋል:: ለዚህም ተፋላሚ ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ማስቻል እንደሚገባ ተናግረዋል:: ከዚህ ባለፈ ግን የተጀመረውን ሕግ የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል::
በክልሉ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም በመገንባት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ፣ የምጣኔ ሃብት ውድመትን መቀነስ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መፍታት የቀጣይ ዓመት ትኩረቶች መሆናቸውን ያስታወቁት ደግሞ የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) ናቸው:: በመጭው ዓመት መንግሥት ሁሉንም አካባቢዎች በመቆጣጠር እና ሰላምን በማስከበር ሕዝብ የሚፈልገውን መንግሥታዊ አገልግሎት በአግባቡ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል:: በተጨማሪም ይቆራረጥ የነበረውን የመጓጓዣ/የትራንስፖርት/ አገልግሎት በተሟላ ደረጃ ማስቀጠል፣ የጸጥታ መዋቅሩን ጉድለቶች በማረም ኅብረተሰቡን መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶች እንዲሰጡ ማስቻል ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል::
የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በበኩላቸው በማክሮ ኢኮኖሚው ዙሪያ በየደረጃው ካሉ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ ተቋማት ጋር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም መክረዋል:: በወቅቱ በየደረጃው ያለው አመራር በክልሉ ለሚፈጠር ችግር ባለቤት ከመፈለግ እና በድህረ ችግር ትንታኔ ከመጠመድ ወጥቶ በኃላፊነት ሊሠራ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል::
በአጠቃላይ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ግጭት እና ጦርነት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሰላማዊ የትግል አማራጮችን ተጠቅሞ መቋጨት ይገባል:: ለዚህም የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ለክልሉ ሰላም እና ለሕዝቡ ደኅንነት ሲባል በትግል ላይ የሚገኙ ሁሉም ወገኖች ወደ ውይይት እና ድርድር እንዲመጡ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በቀናነት መቀበል ከጉዳቱ ጥቅሙ እጅጉን ያመዘነ ይሆናል::
በሌላም በኩል ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጎቿ በፈለጉት አካባቢ በነጻነት ተንቀሳቅሰው በመሥራት እና ሐብት አፍርተው እንዲኖሩ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የጀመረውን የሰላም ማስፈን ሂደት መደገፍ ይገባል:: ልዩነትን በጠብመንጃ ለመፍታትም ሆነ ለመቀልበስ የሚደረግ አካሄድ ሀገርን ወደ ኋላ ከመጎተት እና ሕዝብን ደኅንነት ከማሳጣት ያለፈ ትርጉም ስለማይኖረው ሁሉም አካል ልዩነቱን በንግግር እና በድርድር መፍታትን ሊያስቀድም ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም