የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት፣ አንቀጽ 36 (1) ሁሉም ሕፃናት በሕይወት የመኖር፣ ወላጆቻችውን ወይም በሕግ የማሳደግ መብት ያላቸውን ሰዎች የማወቅ እና የእርሱንም እንክብካቤ የማግኘት፣ ጉልበታቸውን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣ በትምህርት፣ በጤናቸው እና በደኅንነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች እንዲሠሩ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ እንዲሁም በትምህርት ቤቶች ወይም በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ በአካላቸው ከሚፈጸም ወይም ከጭካኔና ኢ-ሰብአዊ ከሆነ ቅጣት ነጻ የመሆን መብቶች እንዳሏቸው ተመላክቷል::
የሀገሪቱ ሕገመንግሥት ለሕጻናት ያጎናጸፋቸው መብቶች ግን በተግባር ሲጓደሉ ይስተዋላል:: ለአብነት ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ሁሉ የመማር፣ ደኅንነቱ የመጠበቅ… መብት እንዳለው አጽድቋል:: ይሁን እንጅ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሕጻናት ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው ከቤት እንዲውሉ ተገደዋል::
ዘርፉ ከፍተኛ ተጽእኖ ከደረሰበት አካባቢዎች አማራ ክልል አንዱ ነው:: በክልሉ ከሁለት ዓመት በላይ ባስቆጠረው ግጭት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ ሆነዋል:: ችግሩ በ2018 የትምህርት ዘመን እንዳይደገም የነበሩ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት፣ አሁን ላይ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ምን ላይ እንዳለ… የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2018 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈጻጸምን ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል::
የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ነጋልኝ ተገኘ እንደሚሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት በዞኑ የመማር ማስተማር ሂደቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተቋርጦ ከርሟል:: ተማሪዎች ዘንድሮም ለሦስተኛ ዓመት ከትምህርት ውጭ እንዳይሆኑ በክረምት ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል:: ይህን መነሻ በማድረግም ለሁለት ዓመታት ከትምህርት ውጭ ሆነው የቆዩትን እና በእነዚህ ዓመታት ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 595 ሺህ 864 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ ነበር:: እስከ ጥቅምት መጀመሪያ ሳምንት በብዙ ጥረት 127 ሺህ 500 ተማሪዎች /25 በመቶ/ ብቻ ተመዝግበዋል::
ከተመዘገቡት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት በመማር ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል:: እነዚህን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት ለኅብረተሰቡ ትምህርት ዋና ጉዳይ መሆኑን ማስገንዘብ ላይ በትኩረት መሠራቱን ጠቁመዋል:: ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት እና ያቋረጡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልክም መግባባት ላይ እስኪደረስ ውይይት መደረጉን አስረድተዋል:: ሀሳቡን የተቀበሉ ነዋሪዎችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ልከዋል:: እስካሁን ያልመጡ ተማሪዎችን ደግሞ ተማሪ በተማሪ እንዲቀሰቀስ፣ ተሰሚነት ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ ወጣቶችን… በመጠቀም ለማምጣት እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል::
ባለፈው ዓመት አልፎ አልፎ የመጡ ጥቂት ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል:: በዚህም 6ኛ ክፍል 99 በመቶ እና 8ኛ ክፍል 91 በመቶ ማሳለፍ መቻሉን ኃላፊው ጠቁመዋል:: 12ኛ ክፍል ከነበረው ችግር አኳያ ለፈተና የተቀመጡ ተማሪዎች ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች የሉም:: በማሳለፍ ምጣኔም ከሪሚዲያል ውጭ 18 በመቶው ቀጥታ መግባታቸውን ኃላፊው ተናግረዋል::
በተያዘው የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ትምርታቸውን ሳያቆራርጡ እንዲቀጥሉ በዞኑ ለ152 ሺህ ተማሪዎች የምገባ መርሀ ግብር ለመጀመር ቅድመ ሁኔታዎች መጠናቀቃቸውንም ጠቁመዋል::
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በ2018 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ 141 ሺህ 132 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ዕቅድ ተይዟል:: እስካሁንም 143 ሺህ ተማሪዎችን መመዝገብ መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ/ር) ለአሚኮ ተናግረዋል::
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ባለፉት ሁለት ዓመታት 10 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ዝግ ነበሩ:: ያለፉት ዓመታት ችግሮች ዘንድሮ እንዳይደገሙ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ተጽኖ ፈጣሪ ወጣቶችን፣ የእድር አባላትን… ለምንድን ነው ትምህርት ቤቶች ለሁለት ዓመት የተዘጉ? በማለት አወያይተዋል:: ለአብነት መሸንቲ፣ አጫድር እና ወርቀምላ አካባቢ የሚኖረውን ሕዝብ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ወስደው በማሳየት እንዲጠግኑ እና ሙሉ በሙሉ የፈራረሰውን በአዲስ እንዲሠሩ በማድረግ ተማሪዎቻቸው ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ማድረግ ተችሏል::
እንደ ኃላፊው ገለጻ በፈተና ውስጥ ሆነውም ከተማ አስተዳደሩ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በ2017 ዓ.ም 45 በመቶ ተማሪዎችን ማሳለፍ ተችሏል:: ዘንድሮ በርካታ ተማሪዎችን ለማሳለፍ የአምና ችግሮች ምን ነበሩ? በማለት ተለይተው ወደ ትምህርት ቤቶች መውረዳቸውን አስታውቀዋል::እንደ መፍትሔም የቅዳሜ እና እሁድ ትምህርት እንዲኖር፣ ቤተ መጻሕፍት በሁሉም ቀናት አገልግሎት እንዲሰጡም እየተደረገ ነው ብለዋል::
የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ደስታ አሥራቴ በበኩላቸው በተያዘው የትምህርት ዘመን 811 ሺህ 221 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ እስከ ጥቅምት ወር አጋማሽ 435 ሺህ /53 በመቶ/ ተማሪዎችን መመዝገብ ተችሏል:: ከነዚህ ውስጥ ወደ ትምህርት ቤት መጥተው በመማር ላይ ያሉት 81 በመቶ ናቸው:: ከእነዚህም ውስጥ በወጥነት ወደ ትምህርት ቤት የማይመጡ ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል::
ማህበረሰቡ ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎች እንዲመጡ ከዞን እስከ ቀበሌ ግንዝቤ እየተፈጠረ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል:: ይህ በመደረጉ ዘንድሮ መሻሻል ቢኖርም አጥጋቢ እንዳልሆነ ግን አስገንዝበዋል::
ኃላፊው እንደሚሉት የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ውጤት አጥጋቢ አለመሆኑን አስታውሰዋል:: ለዚህም ችግሮቻችን በዞን ደረጃ ተለይተዋል:: ዋናው ችግርም ተማሪዎች እንደ ጀመሩ የማብቃት እና የማዘጋጀት ሥራ አልተሠራም:: የተጀመረው የካቲት ወር አካባቢ ነው:: ዘንድሮ ግን መማር ማስተማር ከተጀመረበት እለት አንስቶ ተማሪዎችን በችሎታቸው ለይቶ የማገዝ ሥራ ተጀምሯል::
ሌላው ለመማር ማስተማር ሥራው አጋዥ የሆኑ የቤተ መጻሕፍት እና ላብራቶሪ አገልግሎት በሁሉም ቀናት እንዲያገኙ እንዲሁም የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሳያቆራርጡ እንዲከታተሉ የምገባ ኘሮግራም መጀመሩን ጠቁመዋል::
እንደ ኃላፊው ገለፃ እስካሁን ያለው አፈጻጸም ካለፈው ዓመት የተሻለው ነው:: ይህም በየደረጃው ያለው ማህብረሰብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወላጆች እና ምሁራን በሠሩት ሥራ የመጣ ውጤት ነው:: ነገር ግን አሁንም ወደ ትምህርት ቤት የመጡ ሕፃናት ከሚጠበቀው 53 በመቶ ብቻ ናቸው የተመዘገቡት:: የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አፈፃፀም 28 በመቶ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል:: 129 ሺህ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እስካሁን 38 ሺህ ተማሪዎች ብቻ ናቸው የተመዘገቡት:: አሁንም የማህበረሰቡ እገዛ ከፍተኛ ሊሆን ይገባል፤ ጊዜው ገና ነው በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል::
ኃላፊው እንደጠቆሙት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ላለመምጣት እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል አንዳንድ ተማሪዎች በተፈጠረው የሠላም እጦት በሥነ ልቦና ተጐድተው ሥራ ፍለጋ አካባቢውን ለቀው በመሄዳቸው፤ በተለይ ሴቶች ትዳር መመሥረታቸው፤ ግጭቱ አሁንም ድረስ በአንዳንድ አካባቢወች በመቀጠሉ ትምህርት አይቀጥልም ብለው ተስፋ መቁረጥ…ዋና ዋናዎቹ ናቸው::
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው በ2018 የትምህርት ዘመን በክልሉ መዝግቦ ለማስተማር የታቀደው ሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን ተማሪዎችን ነበር:: እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ያለው አፈፃፀም ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን /52 ነጥብ 5 በመቶ/ ብቻ ነው::
በትምህርት ዘመኑ እስካሁን ባለው ምዝገባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 32 በመቶ ሲሆን ይህም ዝቅተኛው አፈጻጸም እንደሆነ ገልጸዋል:: የተሻለ አፈፃፀም ያለው ደግሞ ቅድመ መደበኛ ሲሆን ይህም 73 በመቶ ነው:: በአዲሱ የትምህርት ደረጃ /እርከን/ ከአንደኛ እና መካከለኛ/ ከአንድ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለው 52 ነጥብ 5 በመቶ ነው::
እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ አሁንም ያለው አፈፃፀም ከእቅዱ አንፃር ብዙ መሥራትን ይጠይቃል:: አሁንም ምዝገባው ቀጥሏል:: ለውጤታማነቱ ህብረተሰቡ ልጆቹ ከማንኛውም ጫና ነጻ ሆነው እንዲማሩ ጥረት ማድረግ አለበት:: ይህ ካልሆነ ወላጆች ልጆቻቸው ካልተማሩ ከእነሱ የባሰ ኑሮ ለመግፋት ይገደዳሉ ነው ያሉት::
ትውልዱ ካልተማረ ከየትኛውም ዓለም የተነጠለ ሕይዎት ይገጥመዋል፣ የትውልድ ቅብብሎሽ ክፍተት ይፈጠራል፣ ከዚህ ባለፈ ነገ እና ከነገ ወዲያ ከክልል አልፎ ሀገርን አንገት የሚያስደፋ ውጤት ሊመዘገብ ስለሚችል ልጆች ባልፈለጉት አጀንዳ፣ ባልፈለጉት መንገድ እንዳይጠለፉ መረባረብ እንደሚገባ ኃላፊዋ አስገንዝበዋል::
በተለይ ሰላም በሆነባቸው አካባቢም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ቢሮ ኃላፊዋ ጠቁመዋል:: በተለይ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በእውቀትም ሆነ በዕድሜ ገና በመሆናቸው የትም መድረስ ስለማይችሉ ወላጆች መክረው መመለስ አለባቸው:: በተለይ ሴቶች ያለ እድሜያቸው እያገቡ በመሆኑ አጽንኦት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል::
መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትም ለሕፃናት መብት ቆመው የዓለም አቀፍ ተሞክሮውን በማሳየት እንዲያግዙ፣ ሌላው አካልም ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ከማምጣት ጐን ለጐን ከሁለት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ከነቁሳቁሳቸው በመውደማቸው እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ ኃላፊዋ ጠይቀዋል:: ከሀገር ውጭ ያለው ወገንም ከሀብት እስከ ሀሳብ ሊያግዝ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል::
ባለፈው ዓመት 12ኛ ክፍል የተፈተኑ ተማሪዎች ቁጥር ጥቂት ቢሆንም ሲተነተን ካለፉት ጊዜያት በተሻለ 12 ነጥብ 99 በመቶ ማሳለፍ ተችሏል:: ይህን ውጤት ለማሻሻል ዘንድሮ ቅዳሜ እና እሁድ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እንዲሰጡ፣ ቅዳሜን ሙሉ ቀን የትምህርት ቀን ማድረግ፣ 10 ሺህ መምህራንን ከነበሩበት የሥነ ልቦና ጫና እንደወጡ እና አቅማቸውን የሚያሳድግ ስልጠና መስጠት፣ ዘግይተው ለሚመጡ ተማሪዎች ማካካሻ መስጠት፣ ተማሪ እንዳይኮርጅ የአፈታተን ሥርዓት መዘርጋት እየተከናወኑ ያሉተግባራት ናቸው:: ሌላው ተማሪው ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርቶ ለራሱም ሆኖ ለሌላው ተማሪ ተሥፋ በመጫር ተተኪ ትውልድ ለመገንባት የሚሰጡ ትምህርቶች ገበያው የሚፈልጋቸው መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል::
ግዕእዝ በአማርኛ
ዮም – ዛሬ
ትማልም – ትላንት
ጌሰም – ነገ
ናሁ – አሁን
(ሙሉ ዓብይ)
በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


