የሙዚቃ ሕይወቱን ገና በለጋ እድሜው በ1966 ዓ.ም ጀምሯል:: ከቤተክርስቲያን መዘምራን እስከ ባንድ ድረስ በሙዚቃ ተጉዟል:: አረጋኸኝ ወራሽን፣ ፍቅር አዲስ ነቃ ጥበብን፣ እንዳለ አድምቄን እና ሌሎች ሙዚቀኞችን በሙዚቃ መሣሪያ አጅቧል፤ የባሕር ኃይል አባልም ነበር:: አሁን ደግሞ በወሎ የኒቨርሲቲ የስነ ጥበብ ትምህርት ክፍል የሙዚቃ መምህር ነው፡- የሙዚቃ መምህር እና ባለሙያው ሰመረ ከበደ:: ከሙዚቃ ባለሙያው ሰመረ ከበደ ጋር ያደረግነውን ቆይጣ የመጀመሪያ ክፍል እነሆ::
ሙዚቃ እንዴት ጀመርክ?
የተወለድኩት በጅማ ከተማ ነው፤ በአዲስ አበባም አድጌያለሁ:: ከዛ በኋላ ነው ወደ ደሴ የመጣነው:: አባቴ ወታደር ነበር፤ ወታደር ደግሞ አንድ ቦታ አይቀመጥም:: ከቦታ ቦታ ስትንቀሳቀስ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ታያለህ፣ ትሰማለህ፤ ትማራለህ:: በወታደር ቤት ደግሞ ማርሽ ባንዶች እና ልዩ ልዩ ሙዚቃዎችን የሚጫወቱ አይጠፉም:: ስለዚህ እኔ የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎችን እያየሁ፣ እየሰማሁ እና እየሞከርኩ ነው ያደኩት:: ለሙዚቃ ያለኝ ጥልቅ ስሜት ከእዛ የመነጨ ነው የሚመስለኝ::
ወደ ደሴ ከመጣን በኋላ ታላቅ ወንድሜ በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ገባ:: ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ማርሽ ባንድ ሳይቀር የነበረው ትልቅ ተቋም ነበር:: ከ60 እስከ 70 የሚሆኑ አባለት የነበሩት ማርሽ ባንድ ነበረው:: ታላቅ ወንድሜ የሳክስፎን ተጫዋች ሆኖ የማርሽ ባንዱ አባል ሆነ:: የማርሽ ባንዱን መለዬ ለብሱ ሳክስፎኑን እየተጫወተ ሳይ ደግሞ የበለጠ ለሙዚቃ ያለኝ ፍላጎት በጣም ከፍ አለ::
እያደኩ ስመጣ በመንደራችን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ነበረች:: እዛ ቤተክርስትያን ውስጥ አባ ሮቤርቶ የሚባሉ ቄስ ፒያኖ ሲመቱ አየሁ እና እጅግ ወደድኩት:: እኔም እንደ እነሱ መጫወት ብችል ብየ ተመኘሁ:: በቤተክርስቲያኑ ወጣቶች ተሰብስበው መዝሙር ይዘምራሉ:: ጠጋ ብየ እንዴት ነው መግባት የሚቻለው ብየ ጠየኩ:: መዝሙር ከቻልክ ትገባለህ አሉኝ:: የሰጡኝን መዝሙር አጠናሁ እና ገባሁ:: የመዝሙሩን ሂደት የሚመሩት ቄስ አዲስ መሆኔን አይተው “ምንድን ነው? ምን እያደረክ ነው?” ብለው ጠየቁኝ:: እኔ መዘመር እችላለሁ አልኳቸው:: “በል እስኪ?” አሉኝ:: ያጠናሁትን መዝሙር አልኩላቸው፤ እሳቸውም ወደውት በዛው ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዘማሪ ሆንኩኝ:: በዚህም የሙዚቃ ጉዞዬን በ1966 ዓ.ም ሀ ብየ ጀመርኩኝ ማለት ነው::
ከዚያስ?
በቤተክርስቲያኑ ያሉ ዘማሪዎች ፒያኖውን መንካት አይፈቀድልንም ነበር:: አባ ሮቤርቶ ነበር የሚጫወቱት:: አንድ ቀን ማታ መዝሙር ልምምዱ አልቆ ወደ ቤታችሁ ሂዱ ሲባል አዳራሹ ውስጥ ወንበር ስር ተደብቄ ተኛሁ:: የልጅ ነገር ሆነ እና ቄሱ ከአዳራሹ ወጥተው ብዙ ሳይርቁ ፒያኖውን ስደበድብ ሰምተው ተመልሰው መጡ:: እንዳገኙኝ ገረፉኝ፤ ከእኔ ቤት ነው የምታድረው ብለው ይዘውኝ ሄዱ:: እሳቸው ቤት አደርኩ፤ ጠዋት “ይሄውልህ ትላንት የገረፍኩህ ያደረከው የተከለከለ ነገርን ስለሆነ ተናድጄ ነው፤ ይሄን ያክል ፍቅር ካለህ እኔ አስተምርሀለሁ” አሉኝ:: የመጀመሪያውን የፒያኖ ትምህርቴን በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተማርኩ:: በዚህ አጋጣሚ የመጀመሪያው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የፒያኖ ተማሪ እኔ ነኝ:: ከፒያኖ በኋላ ሳክስፎን መጫወት አጠናሁ::
የቤተሰብ ድጋፍስ ምን ይመስላል?
ቤተሰቤ ወደ ሙዚቃው እንዳልገባ ጫና አያደርግብኝም ነበር:: አባቴ ሰው በተፈጥሮ ስጦታው ይኑር የሚል ፍልስፍና ነበረው:: እናቴ ወደ ሙዚቃው እንዳልገባ ፍላጎት ነበራት፤ ቢሆንም አባቴ አቋም ስለነበረው እየመረራት ነው የምትውጠው:: ልጅሽ ሃይማኖቱን ቀየረ ብሎ የሰፈር ሰው ስለነገራት እንዳልሄድ ከለከለችኝ:: ፀቧ ከሙዚቃው ጋር አልነበረም ማለት ነው::
ከቤተክርስቲያኑ ወጥቼ ሙዚቃ ያለበትን ቦታ ሳጠያይቅ የሰፈር ኪነት ያለበትን ቦታ ተቆሙኝ:: ከእዚያም ደግሞ ዘፋኝ ነኝ፣ እችላለሁ ብየ ገባሁ:: “ክብር ላንቺ ለሰማይ እመቤት…” ሲል የነበረው ሰመረ በአንድ ጊዜ ተገልብጦ “ጀግና ባለ ድሉ…” እያለ መዝፈን ጀመረ:: መዝሙር የምዘምረው ቀረ እና ዘፋኝ ሆንኩ፤ እናቴም ተቃውሞዋን ትታ ትደግፈኝ ጀመር:: የቀበሌ የኪነት ቡድን አባል ስሆን 15 ዓመት አካባቢ ይሆነኝ ነበር::
የአማተር የሙዚቃ ጉዞህ እንዴት ቀጠለ?
ከፍተኛ ኪነት ሊቋቋም ነው ተባለ እና ከየቀበሌው አባል ሲመረጥ እኔም ተካተትኩ:: ከፍተኛ ሦስት የተባለ ኪነት ቡድን ውስጥ ገባሁ:: በኋላ በከተማ ደረጃ ኪነት መቋቋም አለበት የሚል ውሳኔ ተወሰነ፤ በዚህም ከተማ አቀፍ የተባለ ኪነት ተቋቋመ፤ ከዚያም ደግሞ ተመርጬ ገባሁ:: ከዚህ በፊት በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ማርሽ ባንድ ውስጥ ሳክስፎን እጫወት ነበር:: የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ የከተማ አቀፍ ኪነት ውስጥም በዘመናዊ ባንድ ሳክስፎን ነበር የምጫወተው::
በወቅቱ ኪነት ለአብዬት የተባለበት ጊዜ ነበር:: ሁሉም ቀበሌዎች ኪነት ነበራቸው:: ቀበሌ ስብሰባ ሲኖር ቅዳሜ ቅዳሜ ልማት ሥራዎች ሲኖሩ የልማት እና ሀገር ነክ ዘፈኖችን እንዘፍናለን:: በቀበሌ ደረጃ ብዙ ሙዚቃ መሣሪያዎች አልነበሩም:: በብዛት በቃል፣ በውዝዋዜ እና በጭብጨባ ነበር ዘፈኖቹን ለታዳሚው የምናቀርበው:: ትልቁ መሣሪያ ከበሮ ነበር:: የተደራጀ መሣሪያ ማግኘት ብርቅ ነው የነበረው:: የሙዚቃ ስሜታችንን ግን እንወጣ ነበር:: የሚዘፍነው ይዘፍናል፤ መወዛወዝ የሚፈልገው ከበሮ ይመታለታል፤ ይጨበጨብለታል:: የሙዚቃ መሣሪያዎቻችን ጭብጨባ እና ከበሮ ነበሩ::
ወደ ከፍተኛ ኪነት ስንሄድ ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ተገዙ:: ድራም (ዘመናዊ ከበሮ)፣ ሳክስፎን እና ቤዝ ጊታር እንዲሁም ሌሎች መጡልን:: በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የናዝሬቱ ዐፄ ገላውዲዎስ፣ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ እና ደሴ ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ነበሩ ትልቅ ባንድ የነበራቸው:: ለደሴ ጥሩ እድል ነበር:: የባለሙያ እጥረት አልነበረብንም:: ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የተመረቁ ባለሙያዎች ነበሩ:: እነሱ በየቀበሌው ሁሉ እየዞሩ ስልጠና ይሰጡ ነበር:: ስለዚህ ኖታ ማንበብ እና መጻፍ ይነግሩን ስለነበር ጥሩ እድል ነበር::
ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስትወጣ የፒያኖ ፍቅርህ አልተገደበብህም?
ፒያኖ እጅግ በጣም እወድ ስለነበረው፤ ያንን ማጣት ለእኔ ቀላል አልነበረም:: ነገር ግን የት ልሂድ? ምን ላድርግ? ስለዚህ ከዛ ስሜት ጋር የሚጠጋጋ ነገር መፈለግ ስለነበረብኝ ወደ ኪነቱ ገብቻለሁ:: ሁለቱ ግን የሚገናኙ አልነበሩም:: በቤተክርስትያኑ የሙዚቃ ትምህርት እንማራለን፤ በአራት ተከፍለን በተለያዩ ቴክኒኮች በፒያኖ ታጅበን እንዘምራለን፤ በኋላ በቀበሌ ኪነት በጭብጨባ መዝፈኑ ከበፊቱ ጋር በጭራሽ ሊወዳደር የሚችል አልነበረም::
ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ የዘፈንኩት፡-
ፀሐይ ሳይል ሀሩር በረሃ ይኖራል
ጀግናው ወታደር ነው ሀገር ያስከብራል…
የሚል እንደ መዝሙር ያለ ዘፈን ነበር:: ያኔ በአዳራሹ የነበረው ሰው በሙሉ አድናቆቱን አቀለጠው:: አምስት ሳንቲም ብዙ ቁም ነገር በሚሠራበት ዘመን አንድ ብር ተሸልሜያለሁ:: ይሄ በጣም ትልቅ ነገር ነበር:: ቤተሰብም ሰውም ድጋፍ ያደርግ ነበር::
በአማተር የሙዚቃ ጉዞህ የማትረሳው ነገር ምንድን ነው?
እደገጠመኝ ከሆነ የማነሳው ሙዚቃ ሳልችል ፍላጎት ስላለኝ ብቻ ሙዚቀኛ ነኝ ብየ በተለያዩ ቦታዎች የምመዘገበው ነገር፣ ክራር ሳልችል እችላለሁ ብየ የምቀርበው ነገር እንዲሁም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እነሱን ነገሮች በደንብ ችዬ መገኘቴ የሚገርም ገጠመኝ ነው::
የአማተር ሙዚቀኛነትህ እንዴት ተጠናቀቀ?
በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት የሙዚቃ መሣሪያዎችን እጫወት እንደነበር ተናግሬያለሁ:: መምህሮቼም ሙዚቃ ፍቅሬን ያውቃሉ፤ በግልጽም እናወራ ነበር፤ በወቅቱ ወደ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የምትገባው 11ኛ ክፍልን ስታልፍ ነው:: አስተማሪዎቼም ይህን ቃል ገብተውልኛል:: ወደ 11ኛ ክፍል ሳልፍ አስተማሪዎቼን ጠየኩ ፈቀዱልኝ:: በእናቴ ጥያቄ አዲስ አበባ ያለች አክስቴ ተቀብላ ያሬድ ሙዚቃ ቤት አስመዘገበችኝ:: አብዛኛው ነገር ደሴ እያለሁ የተማርኩት ስለነበር አልከበደኝም:: በዚህ ሁኔታ የአማተርነት ጉዞዬ ተጠናቀቀ::
ከዚያም የባሕር ኃይል ስልጠና ተቀላቀልኩ:: የመርከበኛነት ትምህርቶችን ተከታተልኩ:: በባሕር ኃይል ማሰልጠኛው ውስጥ ከሙዚቃ ጋር የተገናኘ ክፍል አገኘሁ፤ በዛን ጊዜ ባሕር ኃይል ባንድ ይኑረው አይኑረው አላውቅም ነበር፤ ዳግም ከመጣህማ ብየ ተቀላቀልኩ:: እጅግ የተደራጀ ሙዚቃ ባንድ እና ትምህርት ነበር ያገኘሁት:: የምፈልጋቸውን መሣሪያዎች እንደልብ አገኘሁ:: አሁን ያለው ማንነቴ የተሠራው ባሕር ኃይል ውስጥ ነው::
ትልልቅ ሥራዎችን ስንሠራ ቆይተን በምጽዋ ጦርነት ጊዜ ብዙ ሰው አለቀ፣ ተጎዳ:: በኋላ እንደገና ይቋቋም የሚሉ ሀሳቦች ተነሱ:: ሁኔታው አሳሳቢ ነበር፤ በሕይወት የነበርነው ጥቂት ሰዎች ነን:: ስለዚህ ወደ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተመልሼ ተላኩ::
ይቀጥላል
(ቢኒያም መስፍ)
በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም