በግዛቱ ፍትሕን ያሰፈነ፣ የእውነት ምድር የተባለላትን የደጋጎች መኖሪያ የሀበሻን ሀገር የሚያስተዳድር አንድ ደግ ንጉሥ ነበረ:: ሁሉንም በእኩል የማየት ፀጋ የታደለ ኢትዮጵያ ያበቀለችው፣ ቅን ፈራጅ ሩህሩሁ ንጉሥ ነጃሺ:: ሰውንም በሰውነቱ ብቻ እንጂ በዘር በእምነቱ የማይለካ፣ ሀቀኛነቱን ታላላቆች የመሰከሩለት፣ በስልጣኑ የማይታበይ የ7ኛው ክፍለ ዘመን ፈርጥ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የሀበሻ ምድር ንጉሥ ነጃሺ::
በሙስሊሙ ዓለም ታሪኩ የናኘው አል ነጃሽ በእምነቱ ክርስቲያን ሲሆን በሙስሊሞች የታመነ የተወደደ፣ የነብዩ ሙሀመድ የልብ ወዳጅ ነበር:: የዚህ ወዳጅነት መሰረቱ የቆመው ታዲያ በ620 ዓ.ም ማለትም በሄጅራ ስድስተኛው ዓመት ላይ ነብዩ ሙሀመድ ስምንት መልዕክተኞችን ወደ ስምንት ሀገራት መሪዎች በላከበት ወቅት ነበር- ወደ ስድስቱ ልዑላን እና ወደ ሦስት ንጉሠ ነገሥታት:: የየመን፣ ያማማህ፣ ባህሬን፣ እና ወደ አልታሪዝ ልዑሎች፤ እንዲሁም ወደ አሌክሳንድሪያ ገዢ እና የግብፅ ጠቅላይ ገዥ ወደ ነበረው ጆርጅ፣ ወደ ኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት፣ ወደ ፐርሽያው ንጉሠ ነገሥት ኮሶረስ፣ እና ወደ ሮማውያን ንጉሠ ነገሥት ሄራክሊየስ ነበር:: ከልዑላኑ ሁለቱ ብቻ የነብዩን መልእክት በቀናነት ተቀብለው ለእስልምና ወዳጅነታቸውን ገለፁ:: ከነገሥታት ግን በሚደንቅ ሁኔታ ቀና ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ብቻ ነበር::
ከመቀሌ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነጋሽ የተባለችን አንድ አነስተኛ ከተማን እናገኛለን:: በእስልምና ታሪክ ውስጥ በአፍሪካ የመጀመሪያው ሂጅራ የተደረገባት ቦታ ናት:: ከመካ ቀጥላ ሁለተኛዋ ቅዱስ ስፍራ ይሏታል:: እንዲሁም የሀይማኖት ህብር ምልክት ናት:: በምስራቅ አፍሪካ የታሪክ ሀብታም ናት:: በዓለም የመጀመሪያ የሙስሊም ሰፈራ የተካሄደበት ነው::
አስደማሚው የአልነጃሽ መስጅድ በአሁኑ ወቅት በነጃሽ ከተማ ተራራማ አካባቢ ላይ ቆሞ የሚገኝ፣ ወደ አዲግራት መስመር ከውቅሮ 20 ኪሎ ሜትር ላይ ይገኛል:: መስጅዱ በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው::
የነብዩ ሙሃመድ ተከታዮች በክርስቲያኑ የአክሱም ንጉሥ ከተደረገላቸው ያልተለመደ አቀባበል ጀምሮ ነጋሽ በሙስሊሞች እና በክርስቲያኖች መካከል በሰላም አብሮ የመኖር አንድ ምልክት በመሆን ወሳኝ ታሪካዊ እና ሀይማኖታዊ ጠቀሜታ አግኝታለች:: በብዙ ሙስሊሞች ዘንድ በሙስሊሙ ዓለም ከመካ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ቅዱስ ስፍራ ተብላ ትታሰባለች:: በየዓመቱ ከሁሉም የዓለማችን ክፍል በርካታ ሙስሊሞችን የሚስብ ወደ አል ነጃሽ የሚደረግ ሀይማኖታዊ ጉዞ አለ::
ከአዲስ አበባ 790 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል ነጋሽ የተባለች አነስተኛ ከተማ ትገኛለች:: በሀገሪቱ ካሉ ታሪካዊ ስፍራዎች አንዷ ናት:: በዓለም የመጀመሪያዋ የሙስሊም ሰፈራ የተካሄደባት እንደ መሆኗ ከእስልምና ጋር ቅርበትም አላት::
ሁሉም ታሪኩ የሚጀምረው 7ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የነብዩ ሙሃመድ የመጀመሪያ ተከታዮች በእስልምና እምነታቸው የተነሳ በገዛ ሀገራቸው ሰዎች በመካ የከረረ በጎሳዎች በተሰደዱበት እና በተጨቆኑበት ወቅት ነው:: ከዚህ የተነሳ ነብዩ ሙሀመድ ለተከታዮቻቸው አስተማማኝ ቦታ እና አስተማማኝ መሸሸጊያ እና ከለላ ሊሰጣቸው የሚችል ሩህሩህ ሰው ፈልገው ነበር:: ቀደምት በሆነው መዘገብ በኢሻቃ ሲራ እንደተገለፀው፦
“ነብዩ ሙሃመድ ተከታዮቻቸውን ከጥቃት መከላከል እንደማይችሉ በመገንዘባቸው፣ ‘ወደ ሀበሻ ከዱ፣ በዚያ አንድ ክርስቲያን ንጉሥ አለ:: በመንግሥቱ ፍትሕ አለ:: ሀበሻ የእውነት ምድር ናት:: ስለዚህ በአላህ እርዳታ ድል እስክንቀዳጅ በዚያ ከዱ” ብለዋቸው ነበር::
በመሆኑም፣ እርሳቸው ክርስቲያን በነበረው የአክሱም ዘመነ መንግሥት እንግድነት ጠየቁ:: የወቅቱ የአቢሲኒያውያን ንጉሥ ነጃሺ እንግዶቹን ሞቅ ባለ ስሜት ተቀበላቸው እና በዛሬዋ የትግራይ ክልል አካል በሆነችው በጋሽ ከተማ ውስጥ ማረፊያ ሰጣቸውንን::
የመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት የነብዩ ሙሃመድ ተከታዮች የመጀመሪያውን ሒጅራ አደረጉ እና በ607 ዓ.ም ላይ በአክሱማውያን የግዛት ክልል ውስጥ ደረሱ:: እነርሱን ተከትለውም ወደ 101 የሚጠጉ ሰዎችን የያዘ ቡድን በከረን ተከትሏቸው እንደደረሰ ይነገራል::
ቁረሾችም ተከትለዋቸው በመምጣት ንጉሡ እነዚህን ሰዎች አሳልፎ እንዲሰጣቸው እና መልሶ ወደ መካ እንዲልካቸው ለማሳመን ስጦታዎችን እንደ መደለያ ማበርከትን ጨምሮ እያንዳንዱን የተቻለውን መንገድ ሞክረው ነበር:: ነገር ግን ንጉሡ እንዲህ በማለት ተቃወማቸውን፣ “የወርቅ ክምር ብትሰጡኝ እንኳ እኔን የተጠጉትን ሰዎች አልተዋቸውም:: “ይልቁንም ንጉሡ እንዲህ በማለት ነበር ለሙስሊሞቹ ጥበቃ እንደሚያደርግ አስረግጦ የነገራቸው፣ ‘ከዱ እና በሰላም ይኑሩ፣ ማንም የሚያንገላታችሁ ቢኖር፣ ለዚያ ስራው ከባድ ዋጋ ይከፍላል::’
በኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነት በመነሳሳት ነብዩሙሃመድ ራሳቸውን ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን ተከታዮቻቸውን ኢትዮጵያን እንዲያከብሩ እና ከኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ጋር በሰላም እንዲኖሩ አዝዘዋቸው ነበር:: ከእነዚህ ሙስሊሞች አብዛኛዎቹ እስከ ዕለተ ሞታቸው በሀገሪቱ የቆዩ እና በተቀደሰችው የነጋሽ ከተማ ተቀብረዋል::
ስያሜውን ከንጉሥ ነጃሺ ያገኘው አል ነጃሽ መስጅድ (ነጋሽ አሙዲን መስጅድ) አፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያው መስጅድ እንደሆነ እና በዓለም ቀደምት መስጅዶች አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል:: ይህን ስፍራ በተለይ፣ በታሪክ እና በሀይማኖት ዙሪያ ፍላጎት ያለው ማንኛውም ሰው የግድ ሊያያቸው ከሚገቡ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ ነው:: በእስልምና ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ስፍራ የያዘችና ፅኑ የኢትዮጵያ ንጉሥ ለመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች የተሰጣቸውን የሞቀ አቀባበል እንደ ፅኑ ማስታወሻነት ያገለግላል:: እንዲሁም ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እና ከአብዛኞቹ ከብዙሃኑ የመካ ህዝብ እንኳ ጭምሮ ከአብዛኛዎቹ የአረብ ሀገሮች እስልምናን በመቀበል የመጀመሪያ ሀገር ኢትዮጵያ ለመሆኗ አንዱ ምልክት ነው::
በአሁኑ ጊዜ ነጋሽ፣ በጌጥ በተዋቡ በአረቦች ባህል በተሰሩ የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች መቃብር እና በመጀመሪያው መስጅድ ቦታ ላይ እንደተሰራ በሚነገረው በቅርብ በተገነባው መስጅድ ትታወቃለች:: አንድ ጥንታዊ የመቃብር ቦታም በቁፋሮ የተገኘ ሲሆን ኢትዮጵያን የረገጡት የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞችን መቃብሮች እንደተያዙም ይታመናል::
አብሮ የመኖር ትውፊቱ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በአካባቢው ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች አብረው በፍቅር ይኖራሉ:: ጋብቻ የተለመደ ነው:: አብረው ይበላሉ፣ ይሰራሉ፣ ይጫወታሉ፣ ይፀልያሉ:: አብረው ትምህርት ቤት ይሄዳሉ:: ክርስቲያኑ የሙስሊሙን ሙስሊምሙ የክርስቲያኑን ቤተ እምነት የሚገነቡባት ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያን ነጋሽ ውስጥ ያገኟታል::
በአልነጃሺ መስጅድ የተለያዩ የጥንት ሀይማኖታዊ መጸሕፍት፣ ደብዳቤዎች፣ ማኑስክሪፕቶች እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች መቃብሮች ይገኙበታል:: ከሁሉም የዓለም ማዕዘናት ያሉ ሙስሊሞች ለማየት የሚጎርፉለት አል ነጃሽ መስጅድ እኛ ኢትዮጵያውያን በሕይወት ዘመናችን ልናየው የተገባ ውድ ሀብታችን ነው፤ በቅርቡ በሀገራችን በተደረገው ጦርነት ካገኘው ጉዳት እንዲያገግም በመረባረብ ልንጠብቀው ግድ ይላል::
ኘሮፌሰር ሰርግው ሀብለ ሥላሴ አንሸንት ኤንድ ሜዲቫል ሂስትሪ
የኢትዮጵያ ታሪክ አባ ጋስቢኒ
መሪ ራስ አማን በላይ
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም