የኢትዮጵያን ክብር ከወራሪ ሲጠብቁ በየጦር አውዱ የተሰውላት ቆራጥ የጀግና ዳሮች እንዳሏት ሁሉ፣ የሀይለኞችን መንደር የሚያሸብር፣ የአምባገነኖችን መሰረት የሚያናውጥ፣ የክፉዎችን የክፋት ጫካ መንጣሪ፣ የጭቁኖችን እምባ አባሽ ሃያል ብእር ያላቸው ጉምቱ የብእር አርበኞችንም አፍርታለች። ከእነርሱም ውስጥ አቤ፣ ለመፃፍ የተወለደ፣ ለመፃፍ የኖረ፣ በመፃፍም ዋጋ የከፈለ፣ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጉምቱ ደራሲያን አንዱ ነው። ስሙን ከመቃብር በላይ የሚያስጠሩ ብዙ ሥራዎችን ሠርቶ ያለፈ፣ ምንጊዜም ኢትዮጵያ የማትረሳው ጀግናዋ ነው።
አቤ የተከበረ የአገሪቱ ጋዜጠኛና ደራሲ ነበር። እንደ ጋዜጠኛ ወደ አሜሪካ የመጓዝ እድል ያገኘ፤ እንዲሁም እንደ ደራሲ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን ያበረከተ የታወቀ ፀሃፊ ነበር። እስኪ አቤን ከልጅነት እስካለፈበት የጉልምስና ዘመኑ ድረስ የሕይወት ጉዞውን በወፍ በረር እንቃኘው!
የአቤ ጣቶች ከብእርና ወረቀት ጋር የተዋወቁት ገና በልጅነቱ መሆኑን ወላጅ አባቱ በአንድ ወቅት የተናገሩትን ሬዱልፍ ሞልቫየር ‘ብላክ ላዮንስ’ በተሰኘ መፅሃፉ ላይ አውስቷል። አቤ በቀድሞው የጎጃም ክፍለ ሀገር፣ በባህር ዳር አውራጃ፣ አቸፈር ወረዳ ውስጥ በምትገኝ ቆረንጭ በተባለች አንድ ትንሽየ የገጠር መንደር ውስጥ፣ ሰኔ 25 ቀን 1926 ዓ.ም ተወለደ። ወላጆቹም አቶ ጉበኛ አምባየ እና ወይዘሮ ይርገዱ በላይ ይባላሉ።
የስድስት ዓመት ልጅ ሳለ ፊደል ትምህርት ቤት እንደገባ እና ማንበብ እንደቻለ ይነገራል። በተወለደበት ቀየ ባህላዊ ትምህርቱን ሲከታተል የአእምሮውን ብሩህነት የተረዱት መሪጌታ ገሰሰ የተባሉ አስተማሪው በእጅጉ ይወዱት እና ይገረሙበት እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል። በዚያ የሚሰጡ ባህላዊ የትምህርት አይነቶች፦ የቤተክርስቲያን ዝማሬ፣ ወረብና ግጥም የተማረ ሲሆን፣ በተለይ ግጥም ላይ ይጠበብበት ስለነበር እንደ ሊቅ አስቆጥሮት ነበር። አቤ በትምህርቱ በጣም ብርቱና ጎበዝ ተማሪ ነበር። በባህላዊ ትምህርቱ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት፣ ወደ ጎንደር በመሄድ በተለያዩ የአብነት ትምህርት ቤቶች እንደተማረና ግእዝ፣ ቅኔና ዝማሬ በሚገባ ተምሮ አጠናቋል። በአጠቃላይ ለሶስት አመታት ያህል ተምሯል። ከዚያም ወደ ትውልድ ቀየው ተመልሶ በመሪጌታነት አገልግሏል።
ይህ በእንዲህ እያለ፣ አቤ ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ይወስናል። በመሆኑም በአቅራቢያው ወደምትገኘው የጎጃም ክፍለ አገር አንዷ አካል ወደ ሆነችው የዳንግላ ከተማ በመሄድ ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ ትምህርት ቤት መደበኛ ትምህርት አሀዱ ብሎ ጀመረ። ከአንደኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ዳንግላ ተምሯል። ጥሩ ውጤት ነበረው:: የአቤ ፅኑ የትምህርት ፍላጎት በዚህ አልተገደበም። ትምህርቱን ለመቀጠል ግን መንገዱ አልጋ በአልጋ አልነበረም። በዘመኑ በመላ ሀገሪቱ እንደሆነው ከአዲስ አበባ ውጭ በአቅራቢያው መለስተኛም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የለም። ስለዚህ አንድም ማረፊያ የሚሆን እና ሊያስጠጋው የሚችል ዘመድ ወደ ሌለበት አዲስ አበባ ሥራ ለመፈለግ ድንገት ተነስቶ ሄደ። መልካም አጋጣሚ ሆኖ ወዲያው በጤና ሚንስቴር ውስጥ ስራ አገኘ። በኋላም በመረጃ ሚንስቴር በመቀጠር በጋዜጠኛነት ሰራ። በአጠቃላይ በመንግሥት ሰራተኛነት ለሰባት አመታት ማገልገሉን መረጃዎች ዋቢ ናቸው። ከመንግሥት ስራው ጎን ለጎንም ወደ አዲስ አበባ የሄደለትን የመማር አላማውን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ወይዘሮ ጥሩ ብርሃን የተባሉ የታላቅ እህቱ ልጅ፣ በአቤ ስራዎች ዙሪያ ለሚያጠና አንድ ተመራማሪ እንደ ተናገረችው፣ አቤ ትምህርቱን ስለ መቀጠሉ እርግጠኛ ባትሆንም ቅሉ፣ አስራ ሁለተኛ ክፍል ማጠናቀቁን የሚገልፅ የምስክር ወረቀት በቅርበት ማየት መቻሏን አረጋግጣለች። ከአስራ ሁለተኛ በኋላ ግን የከፍተኛ ተቋም ትምህርቱን ስለመቀጠሉ መረጃ ባይኖርም ራሱን በራሱ በማስተማር ራሱን ለመለወጥ የታተረ ብርቱ አንባቢ እንደነበር ወይዘሮ ሙሉ ነግረውኛል። አንባቢነቱም ለታላላቅ ስራዎቹ ከፍተኛ አቅም የሆነለትን ሰፊ እውቀት መገንባት ያስቻለ እድል እንደፈጠረለት ታስታውሳለች፤ ወይዘሮ ጥሩ።
አቤ የስነፅሁፍ ስራውን የጀመረው በ1942 ዓ.ም በጤና ሚንስቴር እየሰራ ባለበት ተውኔቶችን በመፃፍ ነበር። በማከታተልም፣ አቤ ካበረከታቸው ስራዎቹ፦ ከመቅሰፍት ስራዊት ይጠንቀቅ ሰውነት፣ የሮም አወዳደቅ (1953)፣ የፓትሪክ ሉሙምባ አሳዛኝ አሟሟት (1954)፣ የአመፅ ኑዛዜ፣ አልወለድም፣ the savage girl፣ የፍጡራን ኑሮ፣ የራኄል እምባ (1956)፣ የደካሞች ወጥመድ (1965)፣ ፖለቲካና ፖለቲከኞች (1969)፣ ቂመኛው ባህታዊ፣ መልክአ ሰይፈነበልባል፣ defiance.፣ የረገፉ አበቦች፣ ጎብላንድ አጭበርባሪው ጦጣ፣ አንድ ለእናቱ፣ እድል ነው በደል እና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው። ቂመኛው ባህታዊ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴያትር ለሕዝብ ያሳየው የመጀመሪያ ተውኔቱ ሲሆን አልታተመም። ነገር ግን ለህትመት ከበቁት ተውኔቶቹ ውስጥ፣ የደካሞች ወጥመድ፣ እንዲሁም ፖለቲካና ፖለቲከኞች የተሰኙት ሁለቱ ብቻ ናቸው መድረክ ላይ የታዩት። የራኄል እምባ የተሰኘው ሶስተኛ ተውኔቱ በመፅሐፍ ቅዱሳዊ ጭብጥ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ለመድረክ እይታ እንዳይበቃ ተደርጓል:: ዋነኛ ምክኒያቱም አሰቃቂው የራሄል የባርነት ታሪክ ለባለስልጣናቱ ሊዋጥላቸው ባለመቻሉ ነው። ለዚህም ይመስላል በመግቢያው ላይ እንዲህ የፃፈው፣
ይህ ቲያትር ከተፃፈ ጥቂት አመታት አልፈዋል። በመድረክ ለመታየትም ተመድቦ ነበር፣ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ለተንቀሳቃሽ የሆሊውድ ፊልምና ወይም ለዚያ ቦታ አግባብ ላለው ካልሆነ በቀር ለእኔ ቲያትር ጊዜ ባለመገኘቱ ሳይታይ ቀርቷል፤ ግድ የለኝም፣ ካሳተምኩት ይበቃኛል።
በ1956 አ.ም ‘ዘ ሳቬጅ ገርል’ የተሰኘ አጭር ልብ ወለድ የእንግሊዝኛ መፅሃፍ አበርክቷል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከዚህ በፊት “ከልታማዋ እህቴ” በሚል በአማርኛ የደረሰውን የራሱን የልቦለድ ስራ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሞታል። እንዲሁም በ1967 ‘ዲፊያንስ’ የተሰኘ ታሪካዊ አጭር ልብ ወለድ በቀጥታ በእንግሊዝኛ በመፃፍ በኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያዊ የተበረከተ የመጀመሪያ ስራ ተብሎለታል። ዲፊያንስ መቼቱን በ1928ቱ የጣሊያን ወረራ ላይ በማድረግ በወቅቱ ኢትዮጵያዊያን በጨቋኙ የፋሽስት አገዛዝ የደረሰባቸውን መከራና አስቸጋሪ ወቅት የሚያስታውስ ስራ ነው። አቤ ዲፊያንስ የተባለውን የእንግሊዝኛ ስራው በጥሩ ብቃት ስለመፃፉ በአንድ ጥናቱ ላይ የገለፀው ዴቪድ ቢር(David Beer) የተባለ ተመራማሪ፣ በዚህ ውጤታማ ስራው በፋሽስቶች የተፈፀሙ ወንጀሎችንና የተራራውን ፍልሚያ በግልፅ አሳይቶበታል። እንዲሁም በጥቅሉ በባንዳዎቹና በአማፂያኑ መካከል በነበረው የህዝቡ መከፋፈልና በተደረገው የነፃነት ትግል ላይ ያተኮረ ስራ መሆኑን በጥናቱ አስረድቷል። ?
በእንግሊዝኛ ካበረከታቸው ስራዎቹ ታሪኩን ጀመርነው እንጂ፣ አቤ ከዚያ በፊት በአማርኛ ቋንቋ ባበረከታቸው ተፅእኖ ፈጣሪ ስራዎቹ ነበር ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው። አቤ ብዙ ከፃፉ ጉምቱ ኢትዮጵያውያን ፀሃፊዎች አንዱ ሲሆን ከ20 በላይ መጻሕፍት በአማርኛና ሁለት በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደፃፈ ይነገራል። ከእነዚህ ውስጥም በአዲስ አበባ ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ ቲያትር ቤት ለእይታ የበቁ ሁለት ተውኔቶች ይገኙበታል። በአጠቃላይ በመንግሥት ሰራተኛነት ለሰባት ዓመታት ከሰራ በኋላ ስራውን ለቅቆ ቀጣይ አስራ አምስት ዓመታትን የሙሉ ጊዜ ፀሀፊ በመሆን የህይወት መስመሩን ቀየረ። ህይወቱን በፅሁፎቹ ላይ መሰረተ ማለት ነው። በወቅቱ በኢትዮጵያ በፅሁፍ ብቻ ህይወቱን መምራት የቻለ አንድም ሰው አልነበረም። በስነ ፅሁፍ ብቻ ኑሮን መመስረት በተለይ በዚያ ወቅት ከባድ ፍልሚያ ያለበት የህይወት መስመር ነበር። ምክንያቱም የመጻሕፍት ገበያው አነስተኛ መሆኑና የመጻሕፍት ዋጋም ዝቅተኛ በመሆኑ ሌላ አማራጭ እስካልታከለበት በዚያ መስመር ብቻ ህይወትን መምራት አያስችልም። አቤ ግን ተሳክቶለታል፣ ብዙ ገንዘብም ማካበት ችሎ ነበር። የሽያጭ ሪከርዱንም በበላይነት መምራት የቻለ ታሪክ ሰሪ ነው።
በ1962 ዓ.ም ወደ ባህርዳር በመምጣት የባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ ምርት አከፋፋይ መኪል ሆኖ እንደሰራም ይነገርለታል። መንግሥትን በመጎሻሸም እስከሞት ዋጋ የመክፈል ፅናት የነበረው አቤ፣ በፅሑፎቹ የተነሳ ለብዙ ጊዜያት ተግሳጽ የደረሰው ሰው ነበር፤ በቁጥጥር ስር ውሎም፣ ኢሉባቦር ውስጥ በጎሬና በሞቻ ወህኒዎች ተወርውሮ ከሶስት አመታት በላይ ታስሯል።
በሁሉም የአማርኛ ስነ ፅሑፍ ሃያሲያን ዘንድ እንደተመሰከረለት አቤ፣ ከፍሬያማዎቹና ለማህበረሰባዊ እድገት ከተጉ የዘመኑ ቱባ ፀሃፍት ውስጥ የሚመደብ ታላቅ ደራሲ ነው። ጆአና- ማንቴል ኒኮ እንደከተበችው፦
አቤ ጉበኛ፣ በተራማጅ ምሁራን አዙሪት ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ስራዎችን ፈጣሪ ሲሆን፣ ርእሰ ጉዳያቸውም፣ ምንም እንኳ ታሪካዊ ቢሆኑም፣ በስፋት መነጋገሪያ የሆኑ የወቅቱን የሀገሪቱን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የማጋለጥ ሚና ያላቸው ነበሩ።
በሌላ በኩል መንግሥቱ ለማ እንደተናገሩት፣ “አቤ በዘመናዊ የአማርኛ ስነ ፅሑፍ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የሽያጭ ደረጃ የያዙ ስራዎቹን በመፃፍ ወደር ያልተገኘለት ታታሪ ሰው ነው።” ለምሳሌ፣ አልወለድምና መልከአ ሰይፈነበልባል በተሰኙ ሁለት የልብ ወለድ ስራዎቹ አቤ በሀገሪቱ ያለውን ማህበራዊ ኢፍትሃዊነት በቆራጥነት በመተቸትና የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲኖር አቀንቅኗል። የጊዜውን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በቻለው መጠን በሀቀኝነት በማጋለጥ ከጊዜው የቀደመ ይሉለታልም። የካህናትን፣ የሚዲያውንና የዘመኑን ያረጀ አገዛዝ ያለምንም ርህራሄ ክፉኛ ይነቅፍ ነበር። ስራዎቹ በጥቅሉ፣ አንባቢውን ራሱን ዞር ብሎ በደስታ እንዲመለከትና ራሱን እንዲመረምር ያስቻሉ ናቸው፣ ምክኒያቱም፣ ኤድዊን ቢ እንዳስቀመጠው፣ “ልቦለድ በማንበብ ውሰጥ አንዱ የደስታ ምንጭ በማህበረሰብ ውስጥ እንዳለን የጋራ እንቅስቃሴ ስለራሳችን የበለጠ ለማወቅ ያለንን ፍላጎት ማርካቱ ነው። የደራሲ ተቀዳሚ አላማው የሚኖርበትን ማህበረሰብ መለወጥ እንጂ እጁን አጣጥፎ መቀበል አይደለም። ህዝቡ በአገዛዙ የተሰላቸ ቢሆንም ልክ እንደ አቤ በቆራጥነት ለመተቸት ጥቂቶች ደፍረዋል። ለዚህም ነው አቤ ሙሁራንን ጨምሮ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ አይን ዝነኛ ፀሃፊ ሆኖ የሚታየው።
አቤ ሀሳባዊ ሰው ሆኖ ተገለጠ፤ ለድሆች ርህራሄ በማሳየትና ጭቆናን፣ ብዝበዛንና ሙስናን- በአጭሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉንም ህመሞች በመዋጋት ብቅ አለ። የአቤ ጥንካሬ የወቅቱን አስተዳደራዊ ህፀፆች፣ ማህበራዊ ኢፍትሃዊነትንና ሙስናን እየነቀሰ በመተቸትና ለውጥን በማቀንቀን ይታወቃል። ከእንደዚህ ዘርፈ ብዙ መጻሑፍቱ ውስጥ በአንዱ-በአልወለድም- መፅሃፉ የተነሳ ለሦስት አመታት ታስሮ ነበር።
አቤ ወደ መጨረሻዎቹ ጊዜያት የዘውድ አገዛዙን በተካው ማርክሲስታዊ ርእዮትን በሚያቀነቅነው አዲሱ የደርግ አገዛዝ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋ እየቆረጠ መጣ። በመሆኑም የደርግን መንግሥት በመቃወም በግልጽ ይናገር እንደነበር ታሪኩን የፃፉ ሙሁራን ይናገራሉ። በ1972 ዓ.ም ጥር ወር ውስጥ፣ ስራዎቹን ለማሳተም ከባህርዳር ወደ አዲስ አበባ በሄደበት ወቅት አንድ ሆቴል ውስጥ ተገድሎ ተገኘ። አሟሟቱ እጅግ በረቀቀ መንገድ የተፈፀመና ልክ እንደ በዓሉ ግርማ የአቤ የአሟሟት ምክኒያት እስካሁን ሚስጢር እንደሆነ ተዳፍኖ ቀርቷል። ገና ስራ በሚጀምርበት ትኩስ እድሜው በ47 ዓመቱ ከዚህ ዓለም ድካም አርፏል። አንድ ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆች አፍርቶም ነበር። ይህ የህዝብ ልጅ በአካል ቢያልፍም በስራዎቹ ህያው ሆኖ የሚዘልቅ ጀግና የኢትዮጵያ ልጅ ነው።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም