የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ቀደም ሲል “አላጣሽ” እየተባለ ይጠራ ነበር። ፓርኩ የሚገኘው በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ነው። ከ1930ዎቹ ጀምሮ ጥብቅ ደን በመሆን በህብረተሰቡ ሲጠበቅ ቆይቷል። ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ “አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ” በሚል ህጋዊ እውቅና አግኝቷል።
በሰሜን ምዕራብ አካባቢ የሚገኘውን የሃገሪቱን ወካይ ቆላማ ስርዓተ ምህዳር እና በውስጡ የያዘውን ብዝሃ ህይወት ለመጠበቅ ታስቦ የተከለለ ብሔራዊ ፓርክ ነው።
አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ስፋቱ 266 ሺህ 570 ሄክታር ነው። ከባህር ወለል በላይ ከ500 እስከ 900 ሜትር ከፍታ አለው። ከ13 ነጥብ አንድ ዝቅተኛ እስከ 41 ነጥብ አንድ ከፍተኛ ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሙቀት መጠን ይፈራረቅበታል።
ብሔራዊ ፓርኩን በሰሜን እና ምስራቅ የቋራ ወረዳ ሰባት ቀበሌዎች፤ በደቡብ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል /ብጃሚስ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ / ወይም አይማ ወንዝ እና በምዕራብ ሱዳን /ዲንደር ፓርክ/ ያዋስኑታል።
አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በብዝሃ ህይወት ሃብቱ በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ከእፅዋት ዝርያዎች 14 የቁጥቋጦ አይነቶች፤ 57 ታላላቅ እፅዋት /የዛፍ አይነቶች/፣ ከ10 በላይ የሳር ዝርያዎች፣ 32 አጥቢ እንስሳት /በአፍሪካ ብቻ የሚገኝ የተባለለት እና በመጥፋት ላይ ያለ ባለ ጥቁር ጋማ የአንበሳ ዝርያን እንዲሁም ዝሆንን ጨምሮ/፤ ስምንት አይነት ተሳቢ እና የተራማጅ እንስሳት ዝርያ፣ 16 የአይጥ ዝርያዎች፣ ሰጎንን ጨምሮ 240 የአእዋፍ ዝርያዎች እና 16 የአሳ ዝርያዎች ይገኙበታል።
የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ቆላማው አካባቢ በአረንጓዴ የደን ሽፋን ምክንያት የሰሃራ በረሃማነት መስፋፋትን ከሚከላከል ስነምህዳር አካል ዋነኛ በመሆኑ አረንጓዴው ሙቀት /Green belt/ ወይም አረንጓዴው ዘብ /Green Guard/ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ የካርበን ልቀትን ከመከላከል አንፃር ኢትዮጵያ ካሏት ጥብቅ ቦታዎች እና ፓርኮች ሁሉ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።
የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል አንፃር ብሔራዊ ፓርኩን ለየት ከሚያደርጉት ጉዳዮች የአፍሪካ ታላቁ አረንጓዴ ግድግዳ /Great Green Wall of Africa/ የተፈጥሮ አካል መሆኑ ነው።
ምንጭ፦ Gondarpress.org
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም