አመስጋኝነታችን ለምን እየደበዘዘ መጣ?

0
196

በጥር 5/2017 ዓ.ም ዕትም እዚሁ አምድ ላይ “ቦረቦር ዘዳር አገር” የተባሉ ፀሐፊ “ወርቃማዉ ቃል” በሚል ርዕስ እጅግ በጣም አስተማሪ የሆነ የትዝብት ፅሑፍ አስነብበውናል። በኔ ግምገማ ፀሐፊው ካነሱት የትዝብት ጭብጥ አስተማሪነት ባሻገር የአፃፃፍ/አቀራረብ/ ዘዴው የፀሐፊውን ችሎታ በእጅጉ እዳደንቅ አስገድዶኛል።

ቦረቦር ዘዳር አገር እንዳሉት በታክሲ ላይ የተሳፈረ ወጣት በእድሜ የገፉ አዛውንትን አክብሮ ወንበር ሲለቅ ምስጋና ሊቸረው ይገባ ነበር። ግን ሳይሆን ቀረ። እንግዲህ በእድሜ የገፉ አባት መልካም ተግባር ለፈፀመ ወጣት ምስጋናን ከነፈጉ በምን ሁኔታ የቀደመው መልካም የመከባበር ልምዳችን ከትውልድ ትውልድ መሸጋገር ይችላል። በእድሜ ከፍ ያለው ወጣቱን ማመስገን ካልቻለ ይህ እየደበዘዘ የመጣው የመከባበር ልምድ ተረስቶ  አለመከባበርን ማንገሡ አይቀሬ ይሆናል። በትዝብት ፅሑፍዎ ላይ ያነሷቸው ነጥቦች በአጠቃላይ እውነታ ላይ የተመሠረቱ እና አስተማሪ ናቸው። እርስዎ ይህን ካሉ እኔም የተወሰኑ ጉዳዮችን ለማንሳት እሞክራለሁ።

ለሰዎች ምስጋና መስጠት ፋይዳው ዘርፈብዙ መሆኑን የዘርፉ አጥኝዎች ያስገነዝባሉ። በመሆኑም ምስጋናን በመግለፅ የአንድን ሰው ጥረት፣ ደግነት ወይም ድጋፍ እውቅና ያሰጣል። ምስጋናን ማሳየት እምነትን ይገነባል፣ አዎንታዊ ስሜቶችን ያዳብራል፣ ግንኙነቶችን ያጠናክራል። አንድን ሰው ማመስገን መልካም ተግባራቱን ያጠነክራል፤ አጋዥ ወይም ተቀባይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርግ ያበረታታል። በስነምግባር ላይ የተገነባ አመስጋኝነት ሰዎች ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጣቸው እና እንዲከበሩ ያደርጋቸዋል፣ በራስ የመተማመን ስሜታቸውን እና ተነሳሽነታቸውን ይጨምራል። ምስጋና የደግነት ባህልን ያጎለብታል፤ ይህም በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ መደጋገፍ እና ተስማሚ ሁኔታን ለመፍጠር ይረዳናል። ምስጋና ተቀባዩን ብቻ የሚጠቅም ሳይሆን የምስጋና ሰጭውን የደስታ ስሜት እና ስሜታዊ እርካታ ይጨምራል።

የምስጋና ፋይዳ በዘርፉ ባለሙያዎች እንዲህ ከተገለጸ በሃገራችን ኢትዮጵያ ስልጣኔ እንዲህ ባልተስፋፋበት ወቅት መከባበር ከፍተኛ ቦታ ይሰጠው ነበር። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ ጨርሶ ያልጠፋውን አብነት ልጥቀስ፤ አንድ በእድሜ የገፋ አልያም ከአንድ በላይ ሆነው ከሌላ አቅጣጫ የሚመጡ መንገደኞችን አክብሮ ማሳለፍ የተለመደ ተግባር ነበር። ለዚህም ሲባል ገና ከርቀት እያሉ ቆም ብሎ የአክብሮት ሰላምታ ይሰጣል። አክብሮት የተቸረውም መንገደኛ አክባሪውን ዝም ብሎ አያልፍም። “እለፍ፣ ኧረ እለፍ” በማለት ያከብራል። “ይለፉ” የሚል ምላሽ ይሰጣል። ይሄኔ ቆሞ ላከበረው መንገደኛ “አመሠግናለሁ! ፈጣሪ ያክብርህ” የሚል ምስጋና ይሰጣል። ይህ መልካም ተግባር አሁን አሁን እንኳንስ በከተማ ገጠር ላይም ተሟልቶ ሲተገበር አይስተዋልም። ይህ አለመከባበራችን የመመሰጋገን መልካም ልምዳችንን እያደበዘዘ ለመሆኑ አንደኛው መገለጫ ነው።

አንድ የአካባቢያችን ነዋሪ ሌላ ሃገር ሰንብቶም ይሁን ገበያ ቆይቶ ሲመለስ የተሸከመውን ጓዝ ተቀብሎ እቤቱ ማድረስ እና ምስጋና መቸርም እድሜያችን 40ዎቹን ለዘለለ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ዛሬ ይህ ሲሆን አይታይም። አክብሮቱም፤ ምስጋናውም ተያይዘው ጠፍተዋል። በእኔ እይታ ለዚህ ተጠያቂው ወላጅ አልያም አሳዳጊ ነው እላለሁ። ምክንያቱም እኛ ያለፍንበት መከባበር ከፍተኛ ፋይዳን በምስጋና እንደሚያጎናፅፍ ለልጆቻችን በአግባቡ አላስተላለፍንም። በዚህም የተነሳ የመከባበር እና መመሰጋገን በጎ ልምዳችን ሙሉ በመሉ ጠፍቷል ባይባልም እየደበዘዘ ለመምጣቱ ግን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን የምናስተውለው ሃቅ ሆኗል።

በዋናነት የነበሩንን አበይት የቀደሙ መልካም መስተጋብር መገለጫዎች ለመጥቀስ ሞከርሁ እንጂ አንደየእምነቱ ምስጋና ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመንበታል። ሳይንስም በምርምር ውጤቶቹ ምስጋና ለጤነኛ ህይወት እና መልካም መስተጋብር ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን ያስገነዝባል። በመሆኑም ምስጋና ለሚገባው ሁሉ ሊሰጥ ይገባል እላለሁ።

“ምን አገባኝ” እሚሉት ጊዜ አመጣሽ መልካም መስተጋብርን የሚያኮስስ ድርጊትም ምስጋናን ጥላ ካጠሉበት ሳንካዎች መካከል አንዱ እየሆነ መጥቷል። በቅርቡ የገጠመኝን ሁኔታም በአስረጅነት ልጥቀስ። ከሰፈራችን እየተቆረጠ የነበረ ዛፍ የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ወደቀ። ገመዱም ተበጠሰ። በዚህ ጊዜ ታዲያ የወደቀው ገመድ አደጋ አንዳያደርስ በማሰብ ስልክ ደውዬ ለሚመለከተው አሳወቅሁ። ጥያቄዬ የተቆረጠው መስመር ይቀጠል የሚል ሆኖ ሳለ ባለሙያዎች ግን መጥተው መስመሩን በመጠገን ፋንታ በማቋረጣቸው ለሶስት ተከታታይ ቀናት ጨለማ ውጦን ሰነበተ።

ከቀናት በኋላም የዉሃ መስመር ፈንድቶ ውሃው ሲፈስ ተመልክቼ እንዲጠገን ደውዬ ለሚመለከተው አሳወቅሁ። እነሱም ልክ እንደመብራቱ መስመሩን አቋርጠው ያለ ውሃ ሰነበትን። ከዚያን ጊዜ ወዲህ እኔም ተገድጄ እምጠላውን “ምን አገባኝ” ተቀላቀልኩ። ግን ውሳኔዬ ስህተት መሆኑን አሌ ለማለት አልደፍርም። ምክንያቱም ስህተትን በስህተት ማረም አይቻልምና። እንዲያው አንዳንዴ መልካም መስራት እንኳንስ ምስጋና ማሰጠት ቀርቶ ጉዳትንም እያስከተለ መጥቷል የሚለውን ለመጠቆም ፈልጌ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል እላለሁ።

“አመሰግናለሁ” በማለት ምስጋናን መግለፅ ያጠነክራል። መልካም መስተጋብርን እና በጎ ፈቃድን ይገነባል። የሌሎችን ጥረት እውቅና ይሰጣል። ግንኙነቶችን ሊያጠናክር ይችላል፤ ይህም ሰዎች አድናቆት እና ዋጋ እንዳላቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል። ምስጋና በግልም ሆነ በሙያዊ መቸቶች የበለጠ አዎንታዊ አካባቢን ያመጣል ሲል “ኮውራ ዶትኮም” ላይ የሰፈረ ፅሁፍ ያስረዳል።

“ብሊቭኢንማይንድ” ድረ ገፅ በበኩሉ “አመሰግናለሁ የማለት አስፈላጊነት” በሚል ርዕስ ባስነበበው ፅሑፍ “አመሰግናለሁ” ማለት ለአንድ ሰው ጥረት ወይም ደግነት ምስጋናን፣ አድናቆትን እና እውቅናን የመግለጽ መንገድ ነው። አመሰግናለሁ! ማለት ግንኙነቶችን ያጠነክራል፣ በጎ ስሜትን ያሳድጋል፣ አዎንታዊ ሁኔታን ይፈጥራል። እንዲሁም ምስጋና የህይወት እርካታ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ የራስዎን ደህንነት ያሻሽላል ሲል ይገልፃል። በመሆኑም “ደግነት ለራስ ነው” እንዲሉ ደግ መስራት እና ለተሰራው ደግ ስራም የምስጋና ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው እያልሁ፤ የዛሬውን በዚሁ ቋጨሁ። እናንተስ ምን ትላላችሁ?።

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here