አሚኮ በሚዲያ አማራጮች ቀዳሚ መሆኑ ተገለጸ

0
120

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ የሚዲያ ስቱዲዮ (ኦቢቫን) ባለቤት በመሆን ወደ ሥራ ገብቷል፤ ይህን ተከትሎ በነበረው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ንግግር ያደረጉት የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ  አሚኮ በዲጂታል ሚዲያው ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩ ዘገባዎችን በመስራት፣  ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀድሞ የጀመረ ስለመሆኑና  አብሮነትን እንደ ሀገር እየሰበከ የሚገኝ የሕዝብ ሚዲያ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ሙሉቀን እንደተናገሩት የክልሉን ሕዝብ  የሚዲያ ፍላጎት በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ብቻ መመለስ የማይቻል በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡ ስለሆነም በአሚኮ ኅብር ጣቢያው  ገዥ ትርክትን ለማስረጽ፣ ለኅብረ ብሔራዊነት እና ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር ከክልሉ ውጭ ለሚገኙ ኢትየጵያዊያንን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት  አሚኮ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ስምሪት በመስጠት ብቻ ሳይሆን በዜናዎች የቀጥታ ሽፋን መስጠት የቻለ፣ አብሮነት የሚል መስኮት በመክፈት አብሮነትን እየሰበከ ያለ የሕዝብ ሚዲያ ነው፡፡ ለውጥ እንዲመጣ እና የሕዝብ ጥያቄ እንዲመለስ የሕዝብ ድምጽ የሆነ የሚዲያ ተቋም እንደ ሆነም አብራርተዋል።

ንግግርን እና ውይይትን በማበረታታት የሰለጠነ የፖለቲካ ባሕል እንዲጎለብት የሃሳብ ብዝኀነትን የሚያስተናግድ የሕዝብ ሚዲያ የማድረግ ሥራን በእቅድ እየሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ  በበኩላቸው በሀገሪቱ ይህ ቴክኖሎጂ ያላቸው የሚዲያ ተቋማት ሁለት ብቻ እንደነበሩ ጠቁመው አሁን አሚኮ በሦስተኛነት መቀላቀሉ  ለሕብረተሰቡ የተሟላ መረጃ ከማድረስ ባሻገር ቴክኖሎጂው የውስጥ ገቢውን ለማሳደግ ያስችለዋል ብለዋል፡፡

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር) አሚኮ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች ሳይበግሩት  ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን  ማከናወኑን ነው የገለጹት። ወደ ሥራ ያስገባው ተንቀሳቃሽ ቴክኖሎጂም ለኮርፖሬሽኑ ይገባዋል ነው ያሉት።

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የርእሰ መስተዳድሩ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ እና የአሚኮ የቦርድ ሰብሳቢ ይርጋ ሲሳይ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ብዝኃ ልሳን፣ ታማኝ እና ተቀባይነት ያለው፣ ለሀገር ዕድገት እና ሰላም አበክሮ የሚሠራ መሆኑን በማንሳት ኮርፖሬሽኑን ለማጠናከር የምንሰስተው ነገር አይኖርም ብለዋል።

ከ30 ዓመት በፊት በአማርኛ ቋንቋ መታተም በጀመረው የበኩር ጋዜጣ ሥራውን የጀመረው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በአሁኑ ጊዜ የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች ተደራሽ መሆን ችሏል፡፡

ለኢትዮጵያ ራዲዮ ዜና ሠርቶ በመላክ የጀመረውን የራዲዮ ዘገባ በማሳደግ በአሁኑ ወቅት በባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደሴ  እና በአዲስ አበባ  ተደራሽነቱን  አስፍቷል፡፡ ተጨማሪ ራዲዮ ጣቢያዎች እንዲኖሩትም እየሠራ ይገኛል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደተነገረው ሀገራዊ ጉዳዮችን በጎረቤት ሀገራት ጭምር በራዲዮ እንዲደርሱ ለማድረግ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ለዚሁ ማሳያ የሚሆነውም አጭር በሚባል ጊዜ ገንዳ ውኃ ላይ ተጨማሪ ራዲዮ ጣቢያ ለመክፈት እተደረገ የሚገኘው ጥረት ነው፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here