እንደ መግቢያ
ጋዜጦች በዓለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በአፍሪካ የብዙኃን መገናኛ መሠረት ሆነው ይነሳሉ:: አመሠራረታቸውም ዓላማ አለው:: ለአብነት በአፍሪካ በግምባር ቀደምትነት የተመሠረቱት ኬፕታውን እና አይዊ ኢሮሂን ጋዜጦች ዋና ዓላማ አድርገው የተነሱት ኢ-ፍትሐዊነትን እና የቅኝ ግዛት አስተዳደርን መታገል እንደ ነበር የአሚኮ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩት መዝሙር ሐዋዝ “የብዙኃን መገናኛ ዕድገት በኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል::
የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ የተጀመረውም በነጋሪት ጉሰማ፣ በድንጋይ ላይ ጽሑፎች እና በጥናታዊ ሥራዎች (ስንክሳር እና ዜና መዋዕል፣ ገድል እና ታአምራት) እንደሆኑ በመጽሐፉ ላይ ተጠቁሟል:: ጥንታዊው የኢትዮጵያ የሥነ ተግባቦት ሂደት (ነጋሪት) የተተካው ደግሞ በሕትመት የጋዜጠኝነት ሥራ ነው ተብሎ ይታመናል::
ትናንት
አማራ ክልልም ራሱን የቻለ የብዙኃን መገናኛ ድርጅትን ለማቋቋም መሠረቱን የጣለው በበኵር ጋዜጣ ነው:: በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚዋ ክልላዊ ጋዜጣ ሆና ታህሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም ተመሠረተች::
ክልሉ በበኵር ጋዜጣ የመገናኛ ብዙኃን ጉዞውን ሲጀምር ዋና ዓላማው ለረጅም ጊዜ የቆየው ትልቅ የመልማት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እንደነበር መዝሙር ሐዋዝ በመጽሐፋቸው ላይ ጽፈዋል:: ጋዜጣዋ መረጃዎችን ማድረስ የጀመረችው ከዜና ገጽ ዉጭ በአምስት አምዶች፣ በስምንት ገጾች፣ በአራት ሺህ ቅጂዎች እንደነበርም ከመጽሐፉ መረዳት ተችሏል::
በበኵር ጋዜጣ ይደርስ የነበረው መረጃ የሕዝቡን ፍላጎት በሚገባ ማሟላት ባለመቻሉ የክልሉ መንግሥት የሬዲዮ ስርጭትን በግንቦት 16 ቀን 1989 ዓ.ም አስጀመረ:: “የአማራ ብሔራዊ ክልል ድምጽ” ደግሞ የስርጭቱ ጅማሮ ማብሰሪያ ነበር::
የመረጃ አማራጮችን ለማስፋት፣ የክልሉን ገጽታም በሚፈለገው ልክ ለማስተዋወቅ ሚያዝያ 1992 ዓ.ም የ30 ደቂቃ የቴሌቪዥን ሥርጭት እንደተጀመረ የአሚኮ ታሪክ ያስረዳል:: ዘገባዎች ተቀናብረው ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና ወደ ሌሎች የብዙኃን መገናኛ ተቋማት በመላክ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ይደረግ ነበር::
መዝሙር ሐዋዝ በመጽሐፋቸው እንደከተቡት ከሆነ ዘገባዎችን የሚያሰራጩ ተቋማት በአየር ሰዓት መጣበብ እና በጋዜጣ ገጽ ውስንነት ምክንያት ዘገባዎችን ተቀብለው ለማስተናገድ አለመቻላቸውን እንደ ትልቅ ፈተና አንስተዋል::
ከአሚኮ መስራቾች መካከል ቀዳሚ የሆነው ጋዜጠኛ ጌታቸው ፈንቴ በበኩሉ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተጠናቀሩ ዘገባዎችን ለማድረስ በሚደረግ የጉዞ ሂደት ውስጥ ዘገባዎች ከሚሰራጩበት የሚዲያ ተቋም ሳይደርሱ በመንገድ ላይ ዘራፊዎች ይቀሩ እና አድራሽ ባለሙያዎችም እንግልት ይደርስባቸው እንደ ነበር ያስታውሳል:: አሚኮን በመመሥረት ሂደት እና ሕዝብን ለማገልገል በሚደረግ ጥረት ያጋጠሙ ውጣ ውረዶች ግን የሙያዊ ፍቅር እና በዓላማ የመጽናት ማሳያ መሆናቸውን አስታውሷል::
ዛሬ
አሚኮ ፈተና በማይበግራቸው እና በጋዜጠኝነት ሙያ በተለከፉ የዛሬው ትውልድ የጽናት ተምሳሌት በሆኑ ሠራተኞች ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አላለም:: በየጊዜው የአየር ሰዓትን ማሳደግ፣ በኋላም በኵር ጋዜጣን፣ ሬዲዮን እና ቴሌቪዥንን በአንድ ሥር ይዞ ተደራሽነቱን እያሰፋ ሄደ::
አሚኮ በአሁኑ ወቅት በአራት ጋዜጦች፣ በሁለት የቴሌቪዥን እና በሰባት የሬዲዮ ጣቢያዎች፣ በዲጅታል ሚዲያ (ድረ ገጽ፣ ፌስቡክ፣ ዩቱዩብ፣ ትዊተር ቲክቶክ፣ ኢንስታግራም) መረጃዎችን እያደረሰ ይገኛል:: በአንድ ቋንቋ ብቻ መረጃውን ሲያስተላልፍ የነበረው አሚኮ በአሁኑ ወቅት ሕብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን መሠረት አድርጎ በ12 ቋንቋዎች ለ24 ሰዓታት እያደረሰ ይገኛል::
ዘገባዎችን እየሠሩ በትራንስፖርት በመላክ ማሰራጨት የጀመረው አሚኮ አሁን ላይ ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ ታግዞ በቀጥታ ዘገባዎችን ከቦታው ላይ ሆኖ እያሰራጨ ይገኛል። የተንቀሳቃሽ ስቱዱዮ (ኦቪቫን) ባለቤትም ለመሆን በቅቷል። በውስን የሰው ኀይል የተቋቋመው አሚኮ በአሁኑ ወቅት ከ850 በላይ ሠራተኞች አሉት።
አሚኮ እና ይዘቶቹ
አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት ስለሕዝብ ማንነት፣ ገጽታ እና እሴት ግንባታ፣ ስለሰላም፣ ስለአብሮነት እና መቻቻል፣ ስለሃይማኖት እና ታሪክ በትኩረት ሠርቷል:: ግብርናው ዘምኖ ምርታማነት እንዲያድግ፣ የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥል፣ ችግር ፈቺ ምሁራን እንዲወጡ፣ ጤናማ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር፣ እንቁ ባህሎቻችን በመጤ ባህሎች እንዳይዋጡ… ለተሠራው ሥራም የመረጃ ባለቤቱ ሕዝብ እማኝነት ያስረዳል::
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነዋሪዉ አቶ በላይ ሙሉ አሚኮ ነጻነቱን ተነፍጎ ለቆየው ሕዝብ ድምጽ በመሆን የሠራው ሥራ ከፍተኛ ነው ብለዋል:: በተለይ አሚኮ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በሕወሓት የደረሰበትን ግፍ እና ጭቆና ለዓለም በማጋለጥ ለሕዝብ ድምፅ የሆነበትን ክስተት በቀዳሚነት አንስተዋል:: “ለወሰን እና ማንነታችን በምናደርገው ትግል ሁሉ ከጎናችን የቆመው አሚኮ ነው!” ሲሉ የአሚኮን ተጽእኖ ፈጣሪነት ተናግረዋል::
አሚኮ ለልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ በዓላት ሽፋን የሰጠ፣ የቤተክርስቲያኗን ትውፊቶች እና መንፈሳዊ ሕይወትን ያስተዋወቀ ተቋም መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደሴ ከተማ ቤተክህነት ሥራ አሥኪያጅ ሊቀ ጠበብት ሲራክ መለሰ ናቸው:: አሁንም በርካታ ያልተዳሰሱ ቅርሶች እና ታሪኮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ጠይቀዋል::
የደሴ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ሰብሳቢ ሼህ እንድሪስ በሽር በበኩላቸው አሚኮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እና እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል:: በቀጣይም የሙስሊሙ ታሪካዊ መገለጫ የሆኑ እና ለሀገርም ትልቅ አበርክቶ ያላቸውን ጥንታዊ እና ታሪካዊ መስጅዶች እንዲዳስስ ጠይቀዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጠዬ በበኩላቸው አሚኮ አሁን የመጣውን የዲጅታል ሚዲያ ጨምሮ በሁሉም አይነት የሚዲያ አማራጮች አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከበኵር ጋዜጣ ተነስቶ መሆኑን ተናግረዋል:: የአሚኮ የ30 ዓመታት ጉዞ አልጋ በአልጋ እንዳልነበረም አስታውሰዋል:: አሚኮን በበኵር ጋዜጣ የመሠረቱ ባለሙያዎች በዘመኑ ምቹ የሆነ የሥራ ቦታን እና የተሟላ ቴክኖሎጂን ቢጠብቁ፣ ውጣ ውረድን እና ፈተናን ቢሸሹ ኖሮ ዛሬ ላይ ለበርካታ ሙያተኞች መሰባሰቢያ እና ለሕዝብ ድምጽ የሚሆን ተቋም ባልተፈጠረ ነበር ይላሉ::
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዉ ማብራሪያ በየጊዜው ራሱን እያሳደገ የመጣው አሚኮ ዛሬ ላይ 30ኛ ዓመቱን እያከበረ ይገኛል:: በፕሮግራሙ ኮርፖሬሽኑ ዛሬ ካለበት ደረጃ እንዲደርስ የታተሩ እና በፈተና ውስጥ ሆነው ለሕዝብ የሚጠቅመውን እየሠሩ ያሉ ሠራተኞች ይመሰገናሉ:: ከኮርፖሬሽኑ ጎን ተሰልፈው የነበሩ ግለሰቦች እና ተቋማትም እውቅና ይሰጣቸዋል:: አሚኮ የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ የሚከበረው በዓሉ የሠራተኛውን መስተጋብር እና ውስጣዊ አንድነት የበለጠ ለማጠናከር፣ ኮርፖሬሽኑን ለማስተዋወቅ እና ለቀጣይ ሥራዎች ስንቅ የሚሆኑ ምክክሮችን ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል::
በአጠቃላይ በፈተናዎች ውስጥ አልፎ ከትናንት ዛሬን ያሳመረው አሚኮ ዛሬም ከነገ የተሻለ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል::
ነገ
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በይዘት ተመራጭ፣ በተደራሽነትም አድማሱ ከዛሬው በላይ የሰፋ፣ በቴክኖሎጂም ተወዳዳሪ ማድረግ የመጪው ዘመን ዕቅድ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዉ ያብራራሉ:: ለዚህም ኮርፖሬሽኑን ወደ ሌላ የከፍታ ዓመታት የሚያሻግረውን መሠረት የሚጥል የአምስት ዓመታት ስትራቴጅክ ዕቅድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል:: ለግቡ ስምረትም ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች ዘርዝረዋል::
ጥራት ያለው የሚዲያ አገልግሎት መስጠት የአምስት ዓመቱ ስትራቴጅክ ዕቅድ ቀዳሚ ግብ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዉ አንስተዋል:: ለዚህም በሰው ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ የሚያሳርፉ፣ ታታሪነትን የሚያሳድጉ፣ የምጣኔ ሐብት ልማትን ከፍ የሚያደርጉ፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክሩ እና ወደ አንድነት የሚወስዱ ይዘቶች ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል:: ራስን በቴክኖሎጂ ማዘመን፣ የባለሙያዎችንም ዕውቀት ማሳደግ፣ ብቁ አመራርን መፍጠር ለግቡ ስኬት መሠረት መሆናቸውን አንስተዋል::
አጋርነትን ማጠናከር ለአሚኮ የነገ ከፍታው ሌላው በትኩረት የሚሠራበት ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል:: አሚኮ 30 ዓመታትን ሲያልፍ ብቻውን አልነበረም ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዉ የግለሰቦች እና የተቋማት እገዛ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል::
ተቋሙ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ተቋማት ስልጠና እና ድጋፍ ማግኘቱንም ጠቁመዋል:: አሁንም ጠንካራ አሚኮን ለመገንባት ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ሌሎች ሚዲያዎች ጋር ያለውን መስተጋብር አጠናክሮ ያስቀጥላል ነው ያሉት:: በዕውቀት፣ በሥልጠና፣ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሊያግዙ ከሚችሉ ሌሎች ተቋማት እና ግለሰቦች ጋርም አጋርነቱን አጠናክሮ ይሠራል ብለዋል::
አሚኮን በቴክኖሎጂ ለማጠናከር፣ በይዘት ተመራጭ ለማድረግ እና ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋት ገቢ ልማትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ብለዋል:: ለዚህም ዘገባዎች የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ሆነው ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል::
ስትራቴጅክ ዕቅዱ የኮርፖሬሽኑን የቀጣይ ዘመን ከፍታ በእጅጉ የሚወስን በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሳስበዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም