“አሚኮ የሕዝባችን ልዩ ምልክት ሆኖ እየቀጠለ ነው”

0
21

የዛሬው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መነሻዉ ታህሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም የተመሠረተችው በኵር ጋዜጣ ናት፡፡ በስድስት አምዶች፣ በስምንት ገጽ፣ በአራት ሺህ ቅጂ ለሕዝብ መረጃ ይደርስባት የነበረችው በኵር ጋዜጣ በጊዜ ሂደት ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና ዲጅታል ሚዲያን በማዋለድ ፈር ቀዳጅ የሚዲያ አውታር ናት፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በየጊዜው የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የሚመጥን የስያሜ ለውጥ እያደረገ 30 ዓመታትን ተጉዟል፡፡ በበኵር ጋዜጣ የተጀመረው የጋዜጣ ሥራ ዛሬ ላይ በአገውኛ፣ በኽምጣና እና ኦሮሚኛ ቋንቋዎች የሚታተሙ አራት ዲጅታል ጋዜጦች ደርሰዋል፡፡ አሚኮ ሁለት የቴሌቪዥን እና ሰባት የሬዲዮ ጣቢያዎችን ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር ራሱን ያስተዋወቀበት የዲጅታል ሚዲያ ባለቤት ሆኖ የተመሠረተበትን 30ኛ ዓመት አክብሯል፡፡

 

አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የ30 ዓመታት ጉዞው ምን እንደሚመስል ከምስረታው ጀምሮ የነበሩ ሂደቶችን፣ ውጣ ውረዶችን፣ ዛሬ ላይ የደረሰበትን እና የነገ መዳረሻውን በኤግዚቢሽን አሳይቷል፤ ዐውደ ጥናትም አካሂዷል፡፡ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ በዝግጅቱ ላይ እንዳሉት የአሚኮን የ30 ዓመታት ምሥረታ የምናስበው ትናንት የሠራነውን ለመዘከር፣ ለነገም መሠረትን ለመጣል ነው። ከዚህ በተጨማሪም የሠራተኛውን ቤተሰባዊነት እና አንድነት ለማጠናከር ነዉ ብለዋል::አሚኮ ዛሬ ላይ በ12 ቋንቋዎች ብዝኀ ልሳን ሆኗል ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዉ፡፡ አሚኮ ዋጋ እየከፈለም ቢሆን ለሕዝብ የሚበጀውን እየመረጠ የሚሠራ፤ በችግርም ውስጥ ሆኖ በችግሮች ሳይበገር እና ራሱን እያሳደገ የተጓዘ የሚዲያ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አሚኮ ሀገር ችግር ውስጥ በገባች ጊዜ ከፊት ተሰላፊ ሆኖ እየተጓዘ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ አሚኮ ጥራት እና ፍጥነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ሁሉ አቀፍ የለውጥ ሥራ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ራሱን በቴክኖሎጂ እያዳበረ፣ ተደራሽነቱን እያሰፋ እንደሚሄድም ገልጸዋል።

 

የአማራ ክልል የ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ እንዲሳካ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዲከበር፣ አብሮነት እንዲጠናከር ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ አስታውቀዋል::በአሚኮ የ30 ዓመታት ጉዞ ዝግጅት ላይ  በነበረው ዐውደ ጥናት ላይ “በቀውስ ወቅት የሚዲያ ሚና” በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን መምህር እና ተመራማሪ ጀማል ሙሀመድ (ዶ/ር) ቀውስ (ግጭት) ድንገት የሚፈጠር “የብራ መብረቅ አይደለም” ብለዋል፡፡ ይህም ሚዲያዎች አዝማሚያውን ተመልክተው ቅድመ መከላከል ላይ እንዲሠሩ ዕድል የሚሰጥ ነው ይላሉ፡፡ ሚዲያን በትክክል የሚጠቀም እና ማኅበራዊ ኃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ ቀውስ በተፈጠረ ጊዜ ቀውሱ ተባብሶ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ ቀድሞ በውይይት እንዲፈታ መውጫ መንገዶችን ማመቻቸት ላይ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ የሁሉም ነገር መፍቻው ውይይት ነው ያሉት መምህር እና ተመራማሪዉ፤ “ለግጭት ያበቃን ባለመወያየታችን ነው” ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሚዲያዎች ውይይት ባህል ሆኖ በግጭት ሰው እንዳይሞት በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ለሰላም ልዩ ትርጉም ሰጥተው ከመሥራት በተጨማሪ የእያንዳንዱን ዘገባ የቋንቋ አጠቃቀም መፈተሸ የሚዲያዎች ሌላው ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል::ዘመኑ የፈጠረው የቴክኖሎጂ ዕድል ግን ለከፍተኛ ሐሰተኛ መረጃ መሠራጨት በር በመክፈት ፈተና ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ጊዜ የሚዲያዎች ዋና መውጫ መንገድ ሊሆን የሚችለው መረጃን ሳያዘገዩ እና ሳይደብቁ በፍጥነት ትክክለኛ መረጃን ለሕዝብ ማድረስ ነው ብለዋል፡፡

 

የኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው የሚዲያዎችን ተጽእኖ ፈጣሪነት ያስረዱት “ሚዲያ በሁለቱም በኩል የተሳለ ሰይፍ ነው” በማለት ነው፡፡ ሚዲያ ቀውስ ሊፈጥርም ሊያመክንም እንደሚችል አብነቶችን በማንሳት ያስረዳሉ፡፡ በሩዋንዳ የእርስ በእርስ መጨፋጨፍ እና በጀርመን ብሄርተኝነት መግነን ውስጥ የሚዲያዎች አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰወል፡፡ ሚዲያዎች ብሄራዊ ጥቅምን ታሳቢ ያደረጉ እና ሕዝባዊ መስተጋብርን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ዘገባዎችን መሥራት እንደሚኖርባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል::አሚኮ የሕዝብ መስተጋብር እንዲጠናከር፣ ግጭቶች እንዲረግቡ፣ ሀገራዊ ገዥ ትርክቶችን በማስረጽ ረገድ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁንም ሕዝቡ በዕለት ከዕለት ሕይወቱ ውስጥ የሚያጋጥሙት ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያግዙ አካባቢያዊ መረጃዎችን በቅርበት እንዲያገኝ ተደራሽነት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ላለው ሥራ ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡

ሀገር እንደ ሀገር ጠንካራ ሆና ልትቀጥል የምትችለው ብሄራዊ ጥቅሞቿን አውቃ፣ ቆጥራ እና አስከብራ መጓዝ የቻለች እንደሆነ ሲሉ የተናገሩት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ሀገራዊ ህልውና እና ደኅንነት፣ ምጣኔ ሐብታዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ፣ ፖለቲካዊ አቅም እና ተጽእኖ ፈጣሪነት፣ የባህል ነጻነት እና ተጽእኖ ፈጣሪነት፣ የሕዝቦች ማኅበራዊ ልማት የሀገራችን ብሄራዊ ጥቅሞች ዋና ዋና ግቦች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

 

የብሄራዊ ጥቅም ግቦችን ለማሳካት አንደኛው መሳሪያ ሚዲያ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚዲያዎች የትኛውም ይዘት እና ዘገባ ብሄራዊ ጥቅምን ታሳቢ አድርጎ ሊነሳ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ትልልቅ አጀንዳዎችን ቀርጾ በመሥራት ልዕለ ኃያል የሆነች ሀገር መገንባት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ሰላሟ የተረጋገጠ፣ በምጣኔ ሐብታዊ ልዕልና ከድህነት የወጣች፣ ሕዝቦቿ የተግባቡበት እና አንድነት ያስከበሩባት፣ ሉዓላዊነቷን እና ነጻነቷን የምታስከብር፣ ተከብራ የምትኖር ሀገርን ለመፍጠር የሁሉም ሚዲያዎች አጀንዳ  ሆኖ ሊሠራበት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ ብቃት ያለው አደረጃጀት፣ ተደራሽነት እና አሠራር የሚዲያዎች ትኩረት ሊሆን እንደሚገባም አስታውቀዋል::አሚኮ አደረጃጀቱን እያሳደገ፣ ተደራሽነቱን እያሰፋ፣ በቴክኖሎጂ ራሱን እያሻሻለ ባለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ውስጥ የራሱን አሻራ ስለማኖሩ ገልጸዋል፡፡ አሁናዊ አጀንዳው የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅሞች ቆጥሮ የማረጋገጥ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም የሚሆን አደረጃጀት፣ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ፣ ብቃት ያለው ባለሙያ፣ ፋይናንስ፣ አሠራር እና ተቋማዊ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በበኩላቸው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባለፉት 30 ዓመታት ጥራት ያለው መረጃን ለዜጎች በማድረስ፣ ሕዝብን በማስተማር፣ የመንግሥትን አቅጣጫዎች ለሕዝብ በማሳወቅ፣ ከሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችም በመንግሥት በኩል ምላሽ እንዲያገኙ በትኩረት መሥራቱን አረጋግጠዋል፡፡ በሕዝብ መስተጋብር ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጫፍ ረገጥ አስተሳሰቦችን በመዋጋት ረገድም አይተኬ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡

 

አሚኮ ሰላም በታጣ ጊዜ ውይይት እንዲደረግ፣ የሰላም ዋናው አትራፊ መንገድ መነጋገር እና መደራደር መሆኑን በሚገባ ማሳየቱንም አስታውቀዋል፡፡ ሰላምን በሰላማዊ መንገድ የመመለስ ሂደት የእያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል ባህል እንዲሆን እና እንዲጎለብት የሠራውን ሥራም አድንቀዋል::አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት እምነት የሚጣልበት ተቋም ሆኖ ማገልገሉንም ጠቁመዋል፡፡ በችግር ወቅት ሁሉም የትኛውን መረጃ ልመን ብሎ ግራ በተጋባበት ጊዜ ትክክለኛ መረጃን ከቦታ በማድረስ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡

 

ያም ሆኖ አሚኮ በሐሰተኛ መረጃ አሰራጮች የሚፈተን የሚዲያ ተቋም መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ሐሰተኛ መረጃን ጨምሮ በስነ ልቦና እና በአካል የሚደርስን ጥቃት ተቋቁሞ ለሕዝብ የሚጠቅመውን ትክክለኛ መረጃ ሲያደርስ 30 ዓመታትን ደርሷል ብለዋል::በአንዳንድ ሀገራት ሚዲያዎች የመረጃ ማሠራጫ ብቻ ሳይሆኑ የሀገራት መገለጫ ምልክትም ናቸው ያሉት አቶ አረጋ፤  “አሚኮ የሕዝባችን ልዩ ምልክት ሆኖ እየቀጠለ ነው” ብለዋል፡፡ ለዚህም ምልክትነቱን አጉልቶ በሚያሳይ መንገድ ማደራጀት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ወደ ፊት እንድትሆን ለምንፈልጋት ሀገራችን አንድነት፣ ለሕዝብ መብት እና ጥቅም መረጋገጥ ሕዝብን ማስተሳሰር እና ማንቃት ላይ በትኩረት እንዲሠራ ጉልበት የሚሆኑ የሚዲያ ፍላጎቶችን ማሟላት ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡ በሙያዊ መርህ የተካነ ብቁ የሰው ኅይል ማፍራት እና በከፍተኛ የሚዲያ ቴክኖሎጂ ማስታጠቅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here