አማራጭ የሙግት መፍቻዎች

0
233

ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ማለት በፍትሐብሄራዊ ጉዳይ የተፈጠረን  አለመግባበት  ለፍርድ ቤት አቅርቦ  ከመከራከር  ባለፈ መፍትሄ የሚገኝበት  አማራጭ መንገድ ነው:: አማራጩ በግለሰብ፣ በማሕበር አሊያም አንደ ማሕበረሰብ የተፈጠረን አለመግባባት በሕጋዊ መንገድ ለመጨረስ የሚያስችል የሙግት መፍቻ ዘዴ እንደሆነ የገለፁልን በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ  የፍትሐብሔር ጉዳዮች የክልል አቃቢ ሕግ ባለሙያ አቶ ቢራራ ወርቁ ናቸው::

አቶ ቢራራ እንደሚሉት አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች  በብዙ ሀገራት ልምድ እንደ ሚታየው በተለይም አሁን በፍትሕ ተቋማት ካለው የክርክር ብዛት እና ውስብስብነት እንዲሁም በነፃ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ከመገኘት አንፃር ሰላማዊ የንግድ ልውውጥን ለማምጣት ጠቀሜታቸው የጎላ ነው:: በተለይም አሁን ከተስፋፋው ዓለም አቀፍ ንግድ እንቅስቃሴ ጋር የሚሄድ እና ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገራችን ለመሳብ መንግሥት በውል እና ከውል ውጭ የሚያገለግሉ ከፍርድ ቤት ውጭ ያሉ አማራጮችን አስቀምጧል:: ይህን መሰረት በማድረግም መንግሥት በ2013 ዓ.ም  ችግሮች ሲከሰቱ በእርቅ እና በግልግል ዳኝነት እንዲፈቱ የሚያስችል ሕግ በአዋጅ ቁጥር 1237/2013 አውጇል::

ከእነዚህ አማራጭ  የሙግት መፍቻ ዘዴዎች አንዱ ድርድር  እንደሆነ ባለሙያው አንስተዋል::  ድርድር  ማለት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ሰዎች፣ ድርጅቶች ወይም ተቋማት በሥራ ሂደት  ባለመስማማት ወደ አልተፈለገ  ጭቅጨቅ እና ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ:: በዚህ ወቅት ያልተግባቡ አካላት ያልተስማሙበትን ጉዳይ ለጋራ ጥቅም እና ደኅንነት ሲባል ቁጭ ብለው ሌላ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ሳይገባ በስምምነት የችግሩ መነሻ በሆነው ጉዳይ ላይ መፍትሔ የሚያስቀምጡበት ዘዴ ነው::

ድርድር በሁለት መንገድ ይካሄዳል፤ የመጀመሪያው የሚያከራክራቸውን ጉዳይ በፍርድ  ቤት ክስ ከመሰረቱ በኋላ  በክርክር ሂደት ላይ እያሉ ወደ ድርድር ለመግባት ፍርድ ቤቱን አሳውቀው ወደ ድርድር ይገባሉ፣ ሁለተኛው ደግሞ ከክርክር (ክስ) በፊት  መደራደር ነው::

በድርድር ወቅት ያልተግባቡ አካላት የራሳቸውን እንጂ ሌላ  ሦስተኛ ወገን የማይነኩ፣ አንዱ በአንዱ ተፅእኖ የማያሳድር እና ከሕግ ተቃራኒ ሊሆኑ እንደማይገባቸው በሕግ ተደንግጎ ተቀምጧል:: ሁለቱ ተገላጋይ ወገኖች እያወቁ ለገቡበት ጉዳይ ኃላፊነትም ይወስዳሉ::

በድርድር በተቻለ መጠን በስምምነት ከተፈጸመ  ረዥም ጊዜ የሚቆይ፣ ሰላምን ይዞ የሚመጣ እና ለስምምነቱ መሰረት የሆነውን ጉዳይም ወደ ኋላ የመመለስ ዕድሉ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ አቶ ቢራራ ጠቁመዋል::

ሌላኛው የሙግት መፍቻ ዘዴ  እርቅ ነው::  እርቅ ተዋዋይ ወገኖች በስምምነት በጋራ በሚመርጡት  ሦስተኛ  ወገን አጋዥነት ከውል ወይም ከውል ውጪ በሚመነጭ ሕጋዊ ውጤት ባለው ጉዳይ ላይ በክርክር ሂደት ወይም ወደ ፊት ሊከሰት የሚችል አለመግባባትን ለመፍታት የሚከናወን ሂደት ነው::

እርቅ ሲፈፀም  ባለጉዳዮች እርቁን ለማፋጠን በመረጡት ሦስተኛ ወገን  ፊት ለፊት ቀርበው ያስረዳሉ::  ሦስተኛ  ወገን ጭብጦቹን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ  እና የውሳኔ ሀሳብ መጠቆም፣ ያልተግባቡት ወገኖች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ነገሩን ከመከላከል እና ከመጠቃቃት ይልቅ በሚያስሟሟቸው ነጥቦች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ይመከራሉ:: ሦስተኛ ወገን ባለጉዳዮችን የሚያስማሙ አማራጭ ሀሳቦችን እንዲያቀርቡም ግፊት በማድረግ የግራ ቀኙን ጉዳይ በተለይም ለቅራኔ መንስኤ የተባሉትን ምክንያቶች ያደርቃል:: ይህ ሲሆን ሦስተኛ ወገን ምንም ዓይነት ጫና አያደርግም::

በዚህ የሙግት መፍቻ ተሟጋቾች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ከሚታየው ቀን ባጠረ ውሳኔ ስለሚሰጥ  ወጫቸውን ይቆጥባሉ፤  በጥቂት ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር የፍርድ ቤት ሂደቶች ለሕዝብ ክፍት በመሆናቸው ሳቢያ የተሟጋቾችን ጉዳይ እና ክርክር በችሎቱ ወቅት የተገኘው ሁሉ ያዳምጠው ነበር:: ውዝግቡ በእርቅ ከተፈታ  ግን ጉዳያቸውን የሚያውቀው አንድ ሰው ብቻ በመሆኑ የተደራዳሪ ወገኖች ምስጢር  ይጠበቃል::  በዚህም የተነሳ ማን ከሰሰ፣ ለምን ተከሰሰ ፣ በምን ተከሰሰ ፣ ምን ብሎ ተከራከረ እና ምን ተወሰነ የሚለው በሕዝብ ሊታወቅ አይችልም::

በእርቅ  ዳኝነት  ሁሉም ነገር ምስጢራዊ ከመሆኑ የተነሳ ክስ ስለመኖሩም ከተከራካሪ ወገኖች ውጪ ሌላ ሰው ላያውቅ ይችላል:: በተለይ የንግድ ማህበረሰቡ የንግድ ምስጢሩ ወደ አደባባይ እንዲወጣ ስለማይፈልግ የእርቅ ዳኝነትን ተመራጭ ያደርገዋል:: ሆኖም ግን እነዚህ ወገኖች መስማማት ካልቻሉ አስታራቂ የነበረው ግለሰብ ለሁለቱም ወገን ምስክር፣ የሕግ ጠበቃ እና ወኪል ሆኖ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ አይችልም::

ሦስተኛው ደግሞ የግልግል  ዳኝነት የሚባለው የሽምግልና ዘዴ ነው:: የግልግል  ዳኝነት ግራ ቀኙ ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸውን ለሦስተኛ ወገን አቅርበው የግልግል ዳኛው የሚሰጠውን ውሳኔ የሚቀበሉበት መንገድ ነው:: በግልግል ዳኝነት እና የእርቅ አሠራር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 ከአንቀጽ 6 እስከ 53 የተመለከቱት ድንጋጌዎችም ስለ ግልግል አደራረግ እና አፈፃፀም የሚገልፁ ናቸው::

ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ በሕጉ አግባብ የተደረጉ የግልግል ስምምነቶች ሊፈጸሙ የሚችሉ ስለመሆኑ ነው::

በዚህ አሠራር መሰረት ግልግል ውል ነው:: ምክንያቱም በሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች የሚፈፀሙ የውል ግዴታዎች የሚያቋቁሙበት፣ የነበሩት (ያልተስማሙበት) የሚለወጡበት ወይም ቀሪ የሚሆኑበት ስምምነት በመሆኑ ውል ስለመኖሩ መሟላት የሚገባቸው ነገሮች በግልግል ስምምነትም ተሟልተው ሊገኙ ይገባል::

በመሆኑም የግራ እና ቀኙ ተሸማጋይ ወገኖች የሚችሉትን ነገር ለመፈፀም የግልግል ጉዳይ  የሚፈልጉ ከሆነ ከሁሉም ወገን መጠይቆች  ተሟልተው መገኘት የግልግል ስምምነት መኖሩን የሚረጋገጥባቸው መንገዶች ናቸው:: ስለሆነም በግልግል ሽምግልና ዘዴ ቀዳሚው ርምጃ ግራ ቀኙ ወገኖች በሕጉ የሚፀና የግልግል ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ ሆነው ገብተው  መገኘት  ሲሆን በግልግል ዳኛው የሚሰጣቸው ውሳኔ የመጨረሻ ነው::

እነዚህ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች  ባህሪያት እና ጠቀሜታ ከባህሪ አኳያ ሲታዩ ዘመናዊ የፍትሕ ስርዓት ከተመረኮዙበት እውነትን ወይም ትክክለኝነትን እና ስህተትን ከመወሰን ይልቅ የባለጉዳዮቹን የወደፊት ግንኙነት ታሳቢ ያደረጉ ወጪንና ጊዜን የሚቆጥቡ ፣ መደበኛ ያልሆነ የአቤቱታ ፣ የጉዳይ አመራርና የማስረጃ ሂደት የሚከተሉ ናቸው:: በአብዛኛው ችግራቸውን በሕግ በተቀመጠ ሥነ ሥርዓት እና ሕግ መሰረት ሳይሆን በግጭቱ ባለቤቶች ወይም በሦስተኛ ወገኖች ሚዛናዊነትን መሰረት አድርጎ የሚፈቱ ናቸው።

የአማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓትን መከተል ተመራጭ ከሚያደርጉት አሠራሮች አንዱ ውጣ ውረድ የሌለበት መሆኑ ነው:: የአሠራር ስርዓቱ ያልተንዛዛ መሆን  እና የቀጠሮዎች አለመብዛት ሰዎች የአማራጭ የሙግት መፍቻን እንዲመርጡ ያደርጋቸዋል::

በሌላ በኩል ደግሞ ባለጉዳዮቹ በሂደቱ ላይ የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እድል ይሰጣል::   ፈቃድን መሰረት ያደረጉ ውሳኔዎችም በስምምነት የሚፈፀሙ በመሆናቸው በአብዛኛው ባለጉዳዮች የወደፊት ግንኙነታቸው ሰላማዊ እንዲሆን የሚያስችል ጥቅምና ውጤት አሏቸው::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here