“አማራ ክልል ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ያወጣ ነው”

0
117

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ የረዥም ዓመት የማሰልጠን ልምድ አለው:: ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ  እና ጥቁር አባይ የእግር ኳስ ክለቦችን ወደ ከፍተኛ ሊግ ማስገባት ችሏል:: ደሴ ከተማ፣ ወልድያ ስፖርት ክለብ እና የኢትዮጵያ መድህን እሱ ካሰለጠናቸው ክለቦች የሚጠቀሱ ናቸው:: አሰልጣኝ አረጋይ ወንድሙ (ቸንቶ) ይባላል:: አረጋይ ወንድሙ በውትድርና ሀገሩንም አገልግሏል፤ በዚህም የምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ አግኝቷል:: በአሰልጣኝነት ዘመኑ ለኢትዮጵያ ሴት እና ወንድ ብሔራዊ ቡድኖች ተጫዋቾችን አሰልጥኖ ማስመረጥ ችሏል:: ያለፈባቸውን መንገዶች፣ ቀጣይ እቅዶቹን በተመለከተ ቆይታ አድርገናል:: ስለኢትዮጵያ እግርኳስ ሁኔታም እናነሳለን::

መልካም ንባብ!

ለመግቢያ ያክል፣ ቸንቶ  በሚል ቅጽል ስም ትጠራለህ:: ይህ ስም እንዴት ወጣ? ትርጉሙስ ምንድን ነው?

ቸንቶ በጣሊያንኛ መቶ ማለት ነው:: እኔ ደግሞ በኢትዮጵያ የጦር ኃይል ውስጥ በደረጃ ተመርቄያለሁ:: በተመረኩበት ቀን ከሥዩመ ብሔር (ፕሬዝደንት) ሽልማት ወስጄያለሁ:: የምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግም ነበረኝ:: ወታደራዊ ስልጠናዎችንም እሰጥ ነበር:: ስለዚህ ቸንቶ የሚለው ስያሜ መቶ አለቅነቴን የሚገልጽ እና ከእዛ የመነጬ ነው::

የልጅነት ጊዜ እና የእግር ኳስ ጅማሮህ ምን ይመስል ነበር?

አባቴ የሐረር ጦር አካዳሚ ወታደር ነበር:: ሐረር አካባቢ ሜኢሶ የምትባል በረሀማ ከተማ ውስጥ ነው የተወለድኩት:: በልጅነቴ ከጓደኞቼ ጋር ኳስ እየተጫወትን ነበር የምናልፈው:: ወደተለያዩ አካባቢዎች እየሄድንም ግጥሚያዎችን እናደርግ ነበር:: እስከ 11 ኪሎ ሜትር ድረስ ሄደን እንጫወታለን:: በባቡር መመለሻ ገንዘብ እያጣን በእግራችን ነበር ወደ ሐረር የምንመለሰው::

እግር ኳስ መጫወት መቻሌን ያወቅኩት በሐረር ከተማ ነው:: ከልጅነቴ ጀምሮ እግር ኳስ መጫወት እወዳለሁ፤ እየተጫወትኩም ነው ያደኩት:: ሐረር ከተማ ውስጥ በ1970 እና 71 ዓ.ም በከተማ ደረጃ የአግር ኳስ ውድድሮች ይካሄዱ ነበር:: እኔም ቀበሌ 11ን ወክዬ በሲ ሊግ ደረጃ መጫወት ጀመርኩ:: በ1972 ዓ.ም ደግሞ ለትምህርት ቤት ተመረጥኩ:: ከበረኛ እስከ አጥቂ ድረስ በሁሉም ቦታዎች ተጫውቻለሁ::

ከዚያ በኋላ ግን ወደ ውትድርና ነው የገባሁት:: ለሰባት ዓመታት ያክል በኤርትራ ነው የቆየሁት:: የመጨረሻ የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ነው የነበርኩት፤ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፌያለሁ:: ቀጥሎ ወደ ሐረር ጦር ትምህርት መጣሁ:: በዚያም የብርጌዶች የስፖርት ውድድሮች ነበሩ::

እኔ ስፖርቱን ትቼ ጦረኛ ሆኛለሁ፤ የተዋጊነት እና የአዋጊነት መንፈስ ነበር በውስጤ  የዳበረው:: ሰባት ዓመታት አልፈዋል፤ ቀላል ጊዜ አይደለም:: በአጋጣሚ በእግር ኳስ ብርጌዴን ወክዬ ተሰለፍኩ:: እንዴት እንደሆነ አላውቅም የቀድሞው ችሎታየ ተመልሶ መጣ:: ዘጠኝ ግብ አግብቼ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኜ ተመረጥኩ:: የእኛ ብርጌድም ዋንጫውን አነሳ:: የእግር ኳስ ችሎታው እና ፍቅሩ ውስጤ ስለነበር መልሶ ለማምጣት አልተቸገርኩም የሚል ስሜት ነው የሚሰማኝ:: ከዚያም በሐረር የጦር ትምህርት ቤት መምህር ሆኜ ተመደብኩ::

በውትድርና ቤት መቆየትህ አሁን ላለህበት ሕይወት የጠቀመህ ነገር አለ?

ውትድርና ማለት የሰው ልጅ የሚፈተንበት ነው:: የሰዎች ስብዕና የሚቀረጽበት ነው:: ውትድርና የሳይንሶች ሁሉ አናት (የበላይ)  እንደሆነ ነው የማስበው:: በውትድርና ውስጥ የሰው ልጅ መነሻ የሆኑት ፍልስፍና እና ምርምር አሉ:: የሰው ልጅ በተፈጥሮው ራሱን መከላከል ነው የመጀመሪያው ደመ ነፍሳዊ እንቅስቃሴው:: በሕብረት መኖር ከጀመረ በኋላ ደግሞ ቤተሰቦቹን፣ ማኅበረሰቡን እና ሀገሩን መጠበቅ ጀምሯል:: በዚህ ውስጥ የሚጠቀማቸው ቴክኒኮች (ስልቶች) አሉ:: የእነዚህ ሁሉ ምንጭ ውትድርና ውስጥ ነው ያለው:: ውትድርና የዛሬውን እኔነቴን ቀርጾታል ብየ አስባለሁ::

ወደ እግር ኳስ ስልጠናው እንዴት ገባህ?

በ1985 ለኦሮሚያ ሻምፒዮን ወደ ጂማ ሄድን፤ በዚያም ሳለሁ ሕጻናት ልጆች ኳስ ሲጫወቱ አየሁ:: እነዛ ልጆች የሚገርም ጨዋታ ነበር የሚጫወቱት:: በዚህ መንገድ ተተኪ ልጆችን ማፍራት ይቻላል ብዬ አመንኩ:: ይሄንን ለምን በተወለድኩበት ከተማ አልሞክረውም የሚል ሀሳብም መጣልኝ::

የተወለድኩባት ሜኢሶ ትንሽ ከተማ ናት፤ መሠረተ ልማት እንኳ በቅጡ የላትም፤ ግን እዛ የተወለድን ልጆች ከከተማዋ ስንወጣ በጣም ነው የምንናፍቃት:: እናም እዛች ከተማ ላይ 11 ቡድኖችን በደረጃ፣ በተለያየ የእድሜ ክፍል አዋቀርኩ:: ዋናው ቡድን ለሌሎቹ አርአያ እንዲሆን ነው የሠራነው:: ዋናው ቡድን የአሸናፊነት መንፈስ ኖሮት ለትንንሾቹ እንዲያስተላልፍ ነው የተደረገው:: መሠረቱ በዛ መንፈስ ተጣለ:: በተከታታይ 1985፣ 86፣ 87 ዋንጫ አንስተናል፤ በ1989 ዓ.ም ደግሞ ለኦሮሚያ ክለቦች ሻምፒዮና አልፈን ቦረና ሄደናል::

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ክለቦች ተጫውተሃል፤ አሰልጥነሃል:: ከዚያም ወደ አማራ ክልል መጥተህ በተለይ በአሰልጣኝነት የተሳካ ጊዜ አሳልፈሃል::

እንዴት ወደ አማራ ከልል ልትመጣ ቻልክ?

በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ በመንግሥት ዳግም ወደ ውትድርናው እንድገባ ጥሪ ተደረገልኝ:: በውትድርናው ከፍተኛ ስም እና ማዕረግ ነው የነበረኝ:: ከአለሁበት ቦታ ፈልገው ነው ያገኙኝ:: በውትድርና መምህርነት የራሴን አሻራ አሳርፌያለሁ:: ውጊያው እንዳለቀ ወልድያ ነበር ያረፍኩት:: የእህል ውኃ ጉዳይ ሆነና ከባለቤቴ ከማርታ መኮንን ጋር ተያየን:: ወልድያ ቀረሁ ማለት ነው::

በወቅቱ ጉባ ላፍቶ አርሶ አደር የተሰኘ ክለብ ነበር:: ጉባ ላፍቶ አርሶ አደር የሚለውን ሲሰማ ሰዉ በተሳሳተ መልኩ ሊስለው ይችላል:: ጉባ ላፍቶ አርሶ አደር በጣም የተደራጀ፤ አንድ ዘመናዊ ክለብ ያለው አደረጃጀት እና ስርዓት እንዲሁም ድጋፍ የነበረው ክለብ ነው::

ክለቡን 56 የጉባ ላፍቶ ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት ይረዱታል:: ከእዛ ነው ስሙም የተወሰደው:: ተጫዋቾቹ የወልድያ ልጆች ናቸው:: በመጀመሪያ              ኃይሉ ንጉሤ የሚባል ልጅ ነበር አሰልጣኙ፤ እኔ የእሱ ምክትል ሆኜ ነበር የምሠራው:: በአማራ ክልል የክለቦች ሻምፒዮናን በምክትል አሰልጣኝነት ተሳተፍኩ:: በሚቀጥለው ዓመት ዋና አሰልጣኝ ሆኜ የአማራ ክለቡን የክልል የክለቦች ሻምፒዮና ማድረግ ቻልኩ::

አካባቢው ቅን እና ስፖርት አዋቂ በመሆኑ ችሎታየን በደንብ መረዳት ከሚችሉ ሰዎች ጋር ተገናኝቻለሁ:: በተለያዩ የስልጠና ኃላፊነቶች ላይም ሠርቻለሁ:: በዚህ መሃል ወደ እግር ኳስ ተመልሼ እንድመጣ እና  በእግር ኳሱ ስኬታማ እንድሆን ብዙ ሰዎች ረድተውኛል:: የበጋ፣ ክረምት እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን አሰልጥኛለሁ:: የሴቶች ቡድንንም አሰልጥኛለሁ:: ከእነዚህ መሀል ለኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን መድረስ የቻሉት ሀብታም እሸቱ፣ ገነት ሰጠ እና ሌሎችን አፍርቻለሁ::

በአማራ ከልል እግር ኳስ ስፖርት እድገት ላይ አስተዋጽኦ አለኝ ብለህ ታስባለህ?

እንደ አንድ  ስፖርቱ ውስጥ እንዳለ ግለሰብ  አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ ብየ ላስብ እችላለሁ:: ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማድረግ ችሎታው እና እድሉ ሊኖር ይገባል:: የአንድ ነገር ትልቅነት አንጻራዊ ነው:: ያለህ አስተሳሰብ እና ምዘና ነገሮችን ትልቅም ትንሽም ሊያደርግ ይችላል:: በዋናነት ግን የምፈልገውን ያክል አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ ብየ በድፍረት መናገር አልችልም:: ምክንያቱም የአማራ ክልል ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ያወጣ ክልል ነው:: በእዛ አንጻር ራሴን ለክቼ አላየውም:: ነገር ግን በምችለው ልክ ሰርቻለሁ:: እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ መጫወት የቻሉ ልጆችን አፍርቻለሁ:: በተጫዋቾች ላይም መነሳሳትን ለመፍጠር ሞክሬያለሁ ብዬ አስባለሁ::

ይቀጥላል

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here