አማዞን ውስጥ ምን አለ

0
113

በደቡብ አሜሪካ አህጉር ከፔሩ የአንዲስ ተራሮች ግርጌ ጀምሮ በምሥራቅ አቅጣጫ 3 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ገደማ ድረስ ያለውን ምድር ጥቅጥቅ ያለ ደን ልክ እንደ ብርድ ልብስ ሸፍኖታል። ከላይ ሲታይ አረንጓዴ ባሕር የሚመስለው ይህ ጥቅጥቅ ያለ ደን ሰማያዊ ከሆነው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ጋር ይገናኛል። “የዓለም ሳንባ” ሲሉ ቅጽል ስም አውጥተው ይጠሩታል፤ ይህም ለዓለማችን የአየር ንብረት ሚዛናዊነት ያለውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ ነው፡፡

እንደ ሲ ኤን ኤን እና የተለያዩ ድረ ገጾች መረጃ አማዞን የዓለማችን ትልቁ ደን ሲሆን 40 በመቶ በሚሆኑት ዘጠኝ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ላይ ያረፈ ነው፡፡ ሁለት ሦስተኛው 60 በመቶው የአማዞን ክፍል የሚገኘው በብራዚል ነው፡፡ በፔሩ የሚገኘው የዚህ ጥቅጥቅ ያለ የአማዞን ደን ክፍል ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት ወደ 60 በመቶ የሚያህለውን ይሸፍናል። በዚህ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ከፔሩ አጠቃላይ ሕዝብ አንጻር ሲታይ በጣም ጥቂት ቢሆንም 35 ሜትር ከፍታ ባለው በዚህ ደን ውስጥ በርከት ያሉ እፅዋትና እንስሳት ይኖራሉ። እንዲያውም የአማዞን ደን በምድር ላይ ካሉት የበለጸጉ ሥነ ምህዳሮች መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገራል። ከ3,ሺህ በላይ የሚሆኑት የቢራቢሮ ዓይነቶች በሞቃታማ አየር ውስጥ ከወዲያ ወዲህ ብር ብር ይላሉ። ወደ 4,ሺህ ገደማ የሚሆኑ የኦርኪድ ዓይነቶች የሚያማምሩ አበቦቻቸውን ዘርግተው ይታያሉ። ከ90 በላይ የሚሆኑ የእባብ ዝርያዎች በዛፍ ቅርንጫፎችና በጫካው ውስጥ ይርመሰመሳሉ። እንዲሁም ኢል የተባለውን እባብ መሳይ ዓሣና ፒራንየ የሚባለውን ዓሣ ጨምሮ በግምት ወደ 2, ሺህ 500 የሚደርሱ የዓሣ ዝርያዎች ወንዞችንና ጅረቶችን ተቆጣጥረዋቸዋል።

በዚህ አካባቢ ከሚገኙት የውኃ አካላት መካከል ትልቁ የአማዞን ወንዝ ነው። በአንዳንድ ስፍራዎች በየዓመቱ የሚጥለው ከሁለት ነጥብ አምስት እስከ ሦስት ሜትር የሚደርስ ዝናብ አማዞን  እና 1, ሺህ 100 የሚያህሉ ገባር ወንዞች ከአፍ እስከ ገደፋቸው እንዲሞሉ ስለሚያደርግ ጫካው በጎርፍ ይጥለቀለቃል። ሞቃት የሆነው አየር ከእርጥበት ጋር ተዳምሮ ለተክሎች ተስማሚ የሆነ አየር ይፈጥራል። የሚገርመው ነገር እፅዋቱ በጣም የሚመቻቸው በምድር ላይ ካሉት የአፈር ዓይነቶች ሁሉ ለእርሻ ሥራ ተስማሚ እንዳልሆነ በሚነገርለት የሸክላ አፈር ላይ ነው።

አርኪኦሎጂስቶች፣ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በአማዞን ወንዝ አካባቢ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ያምናሉ። በአሁኑ ጊዜ ከ40 በሚበልጡ ጎሣዎች ውስጥ የታቀፉ በግምት 300,ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በፔሩ የአማዞን ክልል ውስጥ ይኖራሉ። በተጨማሪም ከእነዚህ ጎሣዎች መካከል 14 የሚያህሉት ከቀረው ዓለም ሙሉ በሙሉ ተገልለው ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች “ከሠለጠነ” ኅብረተሰብ ጋር ለአጭር ጊዜ ከኖሩ በኋላ ከዚያ ወዲያ ምንም ዓይነት ግንኙነት ላለማድረግ ሲሉ ከሰው ሸሽተው ወደ ጫካው ዘልቀው ገብተዋል።

እነዚህ በጫካ ውስጥ የሚኖሩ ጎሣዎች ወደዚህ አካባቢ የመጡት መቼ ነው? የመጡትስ ከየት ነው? ክርስቶስ ከመወለዱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ሰዎች ከሰሜን አቅጣጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚህ አካባቢ እንደፈለሱ ተመራማሪዎች ይገምታሉ። ሂቫሮዎች (ያረዷቸውን ጠላቶቻቸውን ጭንቅላት በመጨፍለቅ ይታወቃሉ) የመጡት ከካሪቢያን ሲሆን አረዋኮች የመጡት ደግሞ ከቬኔዙዌላ ነበር። ሌሎች ጎሣዎች ከአማዞን በስተ ምሥራቅ ከምትገኘው ከብራዚልና በስተ ደቡብ ከምትገኘው ከፓራጉዋይ እንደመጡ ይታመናል።

አብዛኞቹ ጎሣዎች ተደላድለው መኖር ከጀመሩ በኋላ በተወሰኑ አካባቢዎች ውስጥ ተዘዋውረው እያደኑና እየሰበሰቡ የሚኖሩ ይመስላል። በተጨማሪም አሲድ የበዛበት አፈር የሚስማማቸውን እንደ ካሳቫ፣ ሚጥሚጣ፣ ሙዝና በቆሎ ያሉ ጥቂት ሰብሎችን ያለሙ ነበር። ስፔናውያን ታሪክ ጸሐፊዎች እንደዘገቡት ከሆነ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በሚገባ ተደራጅተው ብሎም ቀለብ የሚያከማቹበትን ዘዴ ፈልስፈው ይኖሩ የነበሩ ከመሆኑም ሌላ የዱር እንስሳትን የሚያረቡበት ዘዴ ነበራቸው።

በዛሬው ጊዜ በርካታ የሀገሬው ተወላጆች በባሕላቸው መሠረት መኖራቸውን ቀጥለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ቤቶቻቸውን የሚሠሩት ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ ዘዴ አማካኝነት ሲሆን ከጫካ ውስጥ አጣናዎችን ቆርጠው ግድግዳውን እና ጣሪያውን ካዋቀሩ በኋላ ጣሪያውን በዘንባባ ቅጠሎች ወይም በሌሎች የሣር ዓይነቶች ይከድኑታል። እነዚህ ቤቶች ከመሬት ከፍ ብሎ በተሠራ ርብራብ ላይ ስለሚቆሙ በየዓመቱ በሚከሰተው ጎርፍ የማይጥለቀለቁ ከመሆናቸውም በላይ ብዙውን ጊዜ አደገኛ እንስሳት አይገቡባቸውም።

የተለያዩ ጎሣዎች የተለያየ ዓይነት አለባበስና አጋጌጥ አላቸው። እልም ባለ ጫካ ውስጥ የሚኖሩ ወንዶችና ሴቶች የሚለብሱት የሚገለደሙ ልብሶችን ወይም አጫጭር ጉርድ ቀሚሶችን ሲሆን ልጆቻቸው ግን ምንም ልብስ አይለብሱም። ከውጪው ዓለም ጋር ይበልጥ ግንኙነት ያላቸው ጎሣዎች ደግሞ የምዕራባውያንን አለባበስ ይከተላሉ። አንዳንዶቹ የሀገሬው ተወላጆች አፍንጫቸውን ወይም ጆሮዎቻቸውን ተበስተው ቀለበት እንዲሁም የእንጨት፣ የአጥንት ወይም የላባ ጌጦችን ያደርጋሉ። እንደ ማዮሩና ያሉት ሌሎች ጎሣዎች ደግሞ ጉንጫቸውን ይበሳሉ። አንዳንድ የቱኩና እና የሂቫሮ ተወላጆች ጥርሳቸውን ያስሞርዳሉ። በተለያዩ ጎሣዎች ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች የሰውነታቸውን ፀጉር ተላጭተው ቆዳቸውን ይነቀሱታል።

የአማዞን ሰዎች በሺህ የሚቆጠሩ የእፅዋት ዓይነቶችን ስለሚያውቁ ጫካውን እንደ መድኃኒት መደብር አድርገው ይጠቀሙበታል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል በእባብ ለተነደፈ፣ ለተቅማጥ እና ለተለያዩ የቆዳ በሽታዎች ከእፅዋት መድኃኒት ያዘጋጃሉ። ምዕራባውያን ጎማ ከመፈልሰፋቸው ከረጅም ጊዜ በፊት የአማዞን ሰዎች የጎማ ዛፎችን በስተው ወተቱን በማጠራቀም ለሥራ የሚጠቀሙባቸውን ቅርጫቶች ለመለቅለቅ እና የመጫወቻ ኳስ ለመሥራት ይጠቀሙበት ነበር። በተጨማሪም ነዋሪዎቹ ከጫካው ውስጥ ሩቅ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች መልእክት ለማስተላለፍ የሚረዱና ለመጓጓዣነት የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን ለመሥራት የሚያስችሉ ጥሬ ዕቃዎችን ያገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ወንዶች ዛፍ ቆርጠው በወንዝ ላይ ለመጓጓዝ የሚያገለግሉ ታንኳዎችን ይሠራሉ። እንዲሁም ትላልቅ ግንዶችን በመቦርቦር ሩቅ ቦታ ላይ ለሚገኙ ሰዎች መልእክት ለማስተላለፍ የሚያስችሏቸውን ከበሮዎች ይሠራሉ።

የአማዞን ነዋሪዎች ጫካው በሌሊት በሚንከራተቱ ነፍሶች፣ ሕመም በሚያስከትሉ መንፈሶችና ወንዝ ላይ አድብተው ሰለባዎቻቸውን በሚለክፉ አማልክት የተሞላ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለአብነት ያህል በፔሩ ከሚገኙት ትላልቅ ጎሣዎች መካከል አንዱ የሆነውን አግዋሩናን እንመልከት። አግዋሩናዎች “አባት ተዋጊ፣” “አባት ውኃ፣” “እናት ምድር፣” “አባት ፀሐይ” እና “ቃልቻ አባት” የሚባሉ አምስት አማልክት አሏቸው። ሰዎች ከሞቱ በኋላ ወደ እፅዋትነትና እንስሳትነት ይቀየራሉ ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። የሀገሬው ሰዎች መንፈሳዊ ፍጡራንን ላለማስቆጣት ሲሉ አንዳንድ እንስሳትን ከመግደል የሚቆጠቡ ከመሆኑም በላይ ሌሎች እንስሳትን የሚያድኑት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ነው።

ከጥንት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣውን ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ሕይወት የሚመሩት አዋቂዎች እንደሆኑ ተደርገው የሚታመኑት ቃልቻዎች ናቸው። እነዚህ ቃልቻዎች ለመመርቀን ሲሉ የሚያቃዡ እፅዋትን ይጠቀማሉ። አንዳንድ የመንደሮቹ ነዋሪዎች ከሕመማቸው ለመፈወስ፣ የአደንና የእርሻ ሥራቸው ምን ውጤት እንደሚኖረው ለመረዳት እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ወደ ቃልቻዎች ይሄዳሉ።

የአማዞን ሕዝቦች የሚኖሩበት ጫካ በፍጥነት እየተመናመነ ነው። ጫካውን አቋርጠው የሚያልፉ አዳዲስ መንገዶች ተሠርተዋል። በእርሻና በኮካ ልማት መስፋፋት ምክንያት ደኑ ከጊዜ ወደጊዜ እየተመናመነ ነው። በሕገ ወጥ የደን ምንጠራ ሳቢያ በየቀኑ 1 ሺህ 200 የእግር ኳስ ሜዳዎች የሚያህል ስፋት ያለው ደን እየወደመ ነው! ማዕድን በሚያወጡ ሕጋዊ ተቋማትና ሕገ ወጥ በሆኑ የኮኬይን ምርቶች ምክንያት ወደ አማዞን ወንዝ የሚገቡ ገባር ወንዞች እየተበከሉ በመሆኑ የውኃ አካላት አደጋ ተደቅኖባቸዋል።

በፔሩ የማኑ ብሔራዊ ፓርክ የጎብኝዎች መዳረሻ ነው፤ ይህ ፓርክ ከማንኛውም አጥፊ የሰው ልጅ ጉዳት ተርፏል – አንድም መንገድ አያልፍም። በሀገሬው ተወላጆች ብቻ ነው የሚተዳደረው፤ በውጤቱም ይህ 17, ሺህ 162 ኪሎ ሜትር ስኩዬር ተጠብቋል፡፡ አንድ ሺህ የተለያዩ የአጥቢ እንስሳት እና የአእዋፍ ዝርያዎች ከመጥፋት ተጠብቀዋል፡፡

ሌላው ወደ ጥልቁ ደን የእግር ጉብኝት ነው፡፡ በዚህ የአማዞን የደን ጉብኝት ውስጥ ወደ ጫካው የርቀት እምብርት ገብተው የተለያዩ አካባቢዎችን ይጎበኛሉ፡፡ ከ450 እስከ 5 ሺህ ዶላር ሊያወጡ ይችላሉ፡፡

ብራዚል አማዞን ወንዝ የመዝናኛ መርከብ ሽርሽር ሌላው የጎብኝዎች ቀልብ የሚስብ ነው፤ የቱካኖ ሞተር ጀልባ ብዙም ያልታወቁ የአማዞን ወንዝ ገባር ወንዞችን ለማሰስ ጥሩ መንገድ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሎጆች፣ ቅንጡ ሆቴሎች እና ሌሎች አዝናኝ ክስተቶች በአማዞን ጫካ እና ወንዝ ይካሄዳሉ፡፡

ምንጭ፡ ጂ ደብልዩ ዶት ኦርግ፣ አማዞን ቱርስ፣ ሳውዝ አሜሪካ ትራቭል፡፡

(ቢኒያም መስፍን)

  በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here