አረንጓዴ አሻራ

0
154

ግሎባል ውድስ ዶት ኦርግ እንዳስነበበው ከዓለማችን መሬት ከ33 በመቶ በላይ በደን የተሸፈነ ነው፤ በተመሳሳይ መረጃዎች እንደሚያስረዱት ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ምድራዊ ስፋቷ 60 በመቶ በደን የተሸፈነ ነበር። ይሁን እንጂ በሂደት በብዝኃ ሕይወት መመናመን፣ በሕዝብ ቁጥር መብዛት እና መሰል ምክንያቶች የሀገሪቱ ጥቅል የደን ሽፋን ወደ 3 በመቶ ወርዷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ልዩ ትኩረት በማግኘቱ ሀገራዊ የደን ሽፋናችን እያንሰራራ ነው። በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በመተከላቸውም ሀገራዊዉ የደን ሽፋን ወደ 17 በመቶ ማደጉን ከግብርና ሚኒስቴር የማሕበራዊ ትሥሥር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአየር ንብረት መዛባት ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ መሆኑ ይታወቃል። ለዚህ መሠረታዊው ምክንያት ደግሞ የደን መመናመን መሆኑን ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያብራሩት። በመሆኑም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዋነኛው መውጫ መንገድ ስለመሆኑ ይሁንታ ተችሮታል። ሀገራችንም ታዲያ ትኩረት ከሰጠቻቸው ሀገር አቀፍ ተግባራት መካከል አንዱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት እንደተናገሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሕልውና ጉዳይ ነው። ለአብነትም በ2012ቱ የዓለም አካባቢ ቀን በተከበረበት ዕለት “ብዝኃ ሕይወትን መጠበቅና መንከባከብ ቅንጦት ሳይሆን ህልውና መሆኑን አይተናል” ነበር ያሉት።

ባለፉት ዓመታት የችግኝ ተከላ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሚል ሲካሄድ ቆይቷል። ግብርና ሚኒስቴር  እንዳስታወቀው ለአራት ዓመታት በተካሄደው የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  25 ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል። ከተተከሉት ችግኞች መካከልም 52 በመቶ የጥምር ደን እርሻ፣ የፍራፍሬ እና የእንስሳት መኖ መሆናቸው ተነግሯል። የፅድቀት መጠናቸው ደግሞ ከ80 በመቶ በላይ ነው ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በ2015 ዓ.ምላሽ መጨረሻ አካባቢ መጀመሩ ይታወሳል። በሁለተኛው ምዕራፍ የአራት ዓመታት ጊዜያትም ከ50 ቢሊዮን በላይ ይተከላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። መረጃው እንዳብራራው የችግኝ ጣቢያዎች ብዛት፣ ደረጃ፣ ጥራት እና አቅም አድጓል።

አረንጓዴ የአኗኗር ዘይቤ መፈጠሩ፣ የደን ጭፍጨፋ ምጣኔ በግማሽ እንዲቀንስ ማስቻሉ፣ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ ለብዙዎች የገቢ ምንጭ እና የሥራ ዕድል መፍጠሩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ትሩፋቶች ናቸው ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪም የተራቆቱ አካባቢዎች እና ተፋሰሶች እንዲያገግሙ አስችሏል። በሁለተኛ ምዕራፍም እነዚህን እና መሰል ገጸ በረከቶችን በማጠናከር የሀገራችን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ለማፋጠን በትኩረት ይሠራል ነው የተባለው። ከዚህ ባሻገርም ለጤናማ ሕይወት መሠረት በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠይቋል። ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብም ልዩ ትኩረት የሚሻ ተግባር ነው።

‘ነገን ዛሬ መትከል’ በሚል መሪ ሐሳብ በቀጠለው የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ ነው። የሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአፋር ክልል ተገኝተው ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ለልጆቻችን ዕዳ ሳይሆን ልማትን ማሸጋገር አለብን” ነበር ያሉት። ለዚህ ደግሞ የአሁኑ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል። የጥራት ጉዳይ የቀጣይ አረንጓዴ አሻራ ትኩረት እንደሚሆን በማንሳት በተለይም ለፍራፍሬ እና ለሀገር በቀል ዛፎች ቀዳሚ ትኩረት መሰጠቱን አክለዋል።

እንደ ግሎባል ውድስ ድረ ገጽ መረጃ ሩሲያ፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ አሜሪካ እና ቻይና በቅደም ተከተል የዓለማችንን ከፍተኛውን የደን ሽፋን ይይዛሉ፤ ለአብነትም ሩሲያ ስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር መሬቷበደን የተሸፈነ ሲሆን ይህም የዓለማችንን የደን ሽፋን ከ20 በመቶ በላይ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ አምስት ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት የደን ሽፋን ያላት ብራዚል ይም ከዓማችን የደን ሽፋን 12 ነጥብ ሦስት ያህሉን ይይዛል፡፡ ካናዳ ደግሞ ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት የደን ሽፋንን በመያዝ (ከዓማችን የደን ሽፋን ሰባት ነጥብ ሰባት በመቶ ያህል) በሦስተኛነት ትከተላለች፡፡

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here