“አርበኛው እጁ ተይዞ ይሰጠኝ”

0
193

የኢጣሊያ ዓድዋ ላይ መሸነፍ የሷ ብቻ ሳይሆን የመላው ቅኝ ገዥ ኃይል ሽንፈት ነበርና በቂ ዝግጅት ተደርጎ ሽንፈቱ በድል መለወጥ ነበረበት። ይህ የሀያላኑ ግልፅ መነሻ ነው። አውሮፓውያን በጥቁር ህዝብ ድል ከተደረጉ የሌላውም ሃገር ጥቁር ለነፃነቱ መነሳቱ አይቀሬ ነውና ሽንፈት ብቻ ሳይሆን ስጋትም ጭምር ነበር።

በመሆኑም ዳግም ወረራው እንደማይቀር አሳምረው ያውቁታል፤ ኢጣሊያ ያቦካችውን ራሷ መጋገር እንዳለባትም እንዲሁ። ስለዚህ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን ዳግም ወርሮ ሽንፈቱን በድል እንዲለውጥ ይፈልጋሉና ከፍተኛ ግፊት እንዲሁም ማበረታታት ቢያሳዩ አይደንቅም።

የዳግም ወረራው ጥንስስ ከዓድዋው ድል ማግስት የጀመረ ነው። ጣሊያኖች ከዓድዋው ሽንፈታቸው በኋላ ከአፄ ምኒልክ ጋር ወዲያው ነበር የድንበር ስምምነት ያደረጉት። በዚያው ጊዜም ችኮዲኮላን የተባለው ቆንሲል ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ስለላው መቀጠሉን “ የኢትዮጵያ የአምስት ሺ ዓመት ታሪክ፦ ካልተዘመረለት እያሡ እስከ ተዘመረለት ኢህአዴግ” በተሰኘው ቁጥር ሁለት የታሪክ መፅሐፍ ፍስሃ ያዜ ካሣ ገልጿል።

በጥቅምት ወር 1898 ዓ.ም ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ኢጣሊያ የተፈራረሙት ውልም ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ጋር ብቻ የተያያዘ ይምሰል እንጂ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ለሚኖራት ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ፤ የወደፊት ወረራዋንም የሚያመቻች ነበር።

የኢትዮጵያን እና የኢጣሊያን ፍቅር በደንብ ለማሳየት ደግሞ ሐምሌ 28 ቀን 1920 ዓ.ም ለ20 ዓመት የሚዘልቅ የወዳጅነት እና የሰላም ውል ተፈራረሙ። ከዚሁ ጋርም አሰብን እና ደሴን የሚያገናኝ የመኪና መንገድ ለመሥራት ተስማምተው ነበር። በዚህ ሁኔታ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስታዘናጋና ስታሰልል ከረመች። ጎን ለጎንም ከፍተኛ የጦር ዝግጅት እያደረገች ቆየች።

ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያም ሆነ ሌላ ነገር ገዝታም ሆነ በእርዳታ ለማስገባት ብትፈልግ እንኳ ወደቦቿ ሁሉ በሶስቱ ሃገሮች ቁጥጥር ሥር ነበሩና በተለያዩ ምክንያቶች ሲዘጉባት ለማስመሰል ጥቂት ነገሮችን ሲለቁላት ቆዩ። በመጨረሻ ረዥም ዓመት የወሰደው ዝግጅት ተጠናቆ ውላቸውን በወልወል ጥሰው ጦርነት ጀመሩ።

ወልወል የሚገኘው በምሥራቁ የሃገራችን ክፍል በኦጋዴን አካባቢ ነው። ከጥቂት ምዕተ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ያስቆፈሯቸው በጣም አስፈላጊ እና በርከት ያሉ የውሃ ጉድጓዶች በዚሁ በወልወል ይገኙ ነበር። የፋሽስት ኃይልም ጦርነቱን ለመጀመር ሰበብ ያደረገው ይህንኑ ቦታ በመውረር ነው። ከሶማሊያ ተነስቶ በኢትዮጵያ ድንበር ከሚገኘው ወልወል ላይ በሰፈሩ የኢትዮጵያ ጠረፍ ጠባቂዎች ላይ ሳይታሰብ ተኩስ ከፍቶ ቀላል የማይባል ጉዳት አደረሰ። ይህን የመጀመሪያ ያልታሰበ ጥቃት የኢትዮጵያ  ወታደሮች መከቱና ጠላትን መለሱ። ሸሽቶ የሄደው ጥቂት የጠላት ጦር ህዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም በደንብ ታጥቆ ተሰለፈ።

የወቅቱ የአካባቢው ጠባቂ ጦር አዛዥ የነበሩት የሲዳሞ ተወላጅ ዓሊኑር ከጥቂት ጦራቸው ጋር ሆነው “ይህን ድንበር ለመያዝ የሚነሳ ካለ እኛ የኢትዮጵያ ልጆች አይደለንማ! ያውም ጣሊያን? ያባቶቻችን ተሸናፊ? እኛ የአባቶቻችን፣ አባቶቻችን የኛ ናቸው” በሚል ወኔ ቀስቃሽ ንግግር ወታደሩን አነቃቁት።

በዚህ እለት ረቡዕ ህዳር 26/1927 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ድረስ ያለ እረፍት ተዋጉ። ከኢትዮጵያ 94 ሰው ሞቶ 45 ሲቆስል፤ ከኢጣሊያ 77 ወታደሮች መገደላቸውን ጳውሎስ ኞኞ “የኢጣሊያ እና የኢትዮጵያ ጦርነት” በሚለው መፅሐፉ አካቶታል። በዚህም የኢጣሊያ ጦር አፈገፈገ። እነዚህ ውጊያዎች ኃይል መፈተሻ አይነት ነበሩ። ኢትዮጵያ የወልወሉን ግጭት እንዳየች ፊቷን ወደ ዲፕሎማሲው ብታዞርም ሰሚ አልተገኘም። የመንግሥታቱ ማኀበር አባል ሃገር መሆኗን እያስታወሰች ብትከራከር ኢትዮጵያ እና ኢጣሊያ በ1920 ዓ.ም የተስማሙበትን የድንበር ውል ኢጣሊያ መጣሷን እያነሳች አቤቱታዋን ብታቀርብ ከማንኛውም ወገን አዎንታዊ ምላሽ አጣች። ራሷን የምትከላከልበት መሳሪያ በእርዳታም ሆነ በግዥ እንዳታገኝ አደረጉ።

ወራሪው ሃይል ደግሞ ወረራው ወረራ እንዳይመስል የተለያዩ ዘዴዎችን ለመጠቀም ሞከረ። ከነዚህም ውስጥ በወልወሉ ትንኮሳው የተገደሉበትን ወታደሮች በመጥቀስ “ቀድመው ትንኮሳውን የፈጠሩት የኢትዮጵያ ድንበር ጠባቂዎች ናቸው” በማለት የካሳ ጥያቄ አቀረበ። “የተገደሉብኝ ዜጎች ደም አለ፤ ለዚህ ካሳ 200 ሺ ብር ይሰጠኝ፤ በኢጣሊያ ወታደሮች ላይ ከባድ ጥፋት ያደረሰው አርበኛ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር እጁ ተይዞ  ይሰጠኝ…” ቢልም የኢትዮጵያ መንግሥት አልተቀበለውም። የወልወል ግጭት የኢጣሊያ የወረራ ጅምር እንጂ ይፋ የሆነና በዓለም ህዝብ ዘንድ በውል የታወቀ አልነበረም፤ ተራ ግጭት ተደርጎ ተወስዶ ነበር።

ኢትዮጵያዊያኑ ከ1927 እስከ 1928 ፊት ለፊት በመጋፈጥ፤ ከ1928-1933 ዓ.ም ደግሞ በአርበኝነት ጣሊያኖችን በጠንካራ ክንዳቸው ሲከላከሉ እና ሲያጠቁ ነበር። በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ዘመን ተዘርዝረው የማያልቁ ውድ የኢትዮጵያ ጀግኖች በየግዛቱ መሽገው ሃገራቸውን ከወራሪው ፋሽስት ለመታደግ በቁርጠኝነት ተፋልመዋል። በዚያን ጊዜ ሴት ወንድ፣ ሽማግሌ አሮጊት፣ ህፃናት ሳይቀሩ በየዘርፉ ለአርበኞች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር።

መረጃ በማቀበል፣ ስንቅ በመቋጠር፣ ዶሮ እና እንቁላል ለኢጣሊያ ወታደሮች እየሸጡ በሚያገኙት ገንዘብ መልሰው ከራሳቸው ጥይት ገዝተው ለወገኖቻቸው በመላክ፤ በራሱ ጥይት ጠላት እንዲሞት አድርገዋል።

በባንዳነት ለኢጣሊያ ወግነው ወገናቸውን የወጉ የመኖራቸውን ያህልም ባንዳ መስለው ለሃገራቸው ነፃነት የታገሉ የውስጥ አርበኞች የተጫወቱት ሚናም ቀላል አልነበረም። አምስት ጥይት የተኮሰ ባንዳ “25 ተኮስኩ” ብሎ ተናግሮ ሃያውን ለወገኖቹ ይልክላቸዋል። እንዲህና እንዲያ እያደረጉ ድፍን አምስት ዓመቱን እረፍት ነስተዋቸዋል።

የኢጣሊያ ጀነራሎች የኢትዮጵያውያኑን ጀግንነት መቋቋም ሲሳናቸው፤ የትግል ስልታቸውን በመለወጥ እርስ በርስ ለማፋጀት በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት ህዝቡን ከፋፍለው ኦሮሞውን “የአማራ ተገዥነት ይብቃህ… ነፃ ልናወጣህ ነው የመጣነው…” እያሉ ለሌላው ብሔርም ተመሳሳይ መልዕክታቸውን እያሰራጩ የሃገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ ለማሳጨድ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ሆኖም እምብዛም ሰሚ አላገኙም ሲል የታሪክ ጸሐፊው ፍስሃ ያዜ ያስረዳል።

በወልወሉ ጦርነት ወራሪው ኢጣሊያ በደረሰበት ኪሳራ ተነሳስቶ፤ ከፍተኛ ጥረት አድርጎ መግደልም ሆነ መማረክ ስላቃተው የኢትዮጵያ መንግሥት እጁን ይዞ ሊሰጠኝ ይገባል ያላቸው ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ማን ናቸው? የቀጣዩ ሳምንት እትማችን የሚመልሰው ይሆናል።

የሳምንት ሰው ይበለን!

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here