ኢትዮጵያ በቅኝ ገዥዎች እና ወራሪዎች ያልተንበረከከች እንዲሁም ያልተደፈረችና ይልቁንም ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ሃያልና ገናና ሃገር ናት። ይህን ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እና ለማስቀጠል የቻለችዉም ዉድ ልጆቻ እና ጀግኖች አርበኞች በከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት ነዉ።
የጣሊያን ጦር በ1888 ዓ/ም በኢትዮጵያዉያን ድል አድራጊነት ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ቢወጣም በጥቁር ህዝቦች መሸነፉ ባሳደረበት ቁጭት ለዳግም ወረራ ከ40 ዓመት የዝግጅት ጊዜ በኋላ የቅኝ ገዥነት ፍላጎቱን ለማርካት በማሰብ በ1928 ዓ/ም ወደ ኢትዮጵያ ለወረራ መጣ።
በዚህ ጦርነት የኢትዮጵያዉያን ጽናት፣አልሸነፍ ባይነት እና አይበገሬነት በተግባር የተገለጠበት ስለነበር ጣሊያን ኢትዮጵያን ማሸነፍ ሳትችል ቀረች።
በአድዋዉ ጦርነት ድል ያልቀናዉ እና እቅዱ የከሸፈበት የጣልያን መንግስትም የደረሰበትን ሽንፈት መቋቋም ባለመቻሉና በአለም ዘንድ በመዋረዱ ምክንያት ለዳግም ወረራ ወደ ኢትዮጵያ ቢመጣም ኢትዮጵያዉያን አርበኞችም ይህን የጣሊያን ወረራና ፍላጎት በመረዳት ሉዓላዊነታቸዉን ላለማስደፈር በሁሉም አቅጣጫ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ሴት ወንድ ሳይሉ በአንድነት እና በጀግንነት በመሰለፍ የሃገራቸዉን አንድነት እና ሉዓላዊነት ለማስከበር አምስት ዓመቱን በሙሉ ዱር ቤቴ በማለት በኋላ ቀር መሳሪያ፣ በግል ስንቅና ትጥቅ በመዝመት የጠላትን ጦር ዳግም በማሸነፍ ሚያዚያ 27/1933 ዓ/ም የነጻነት ሰንደቅ አላማቸዉን ከፍ አድርገዉ በመስቀል ዳግም ነጻነታቸዉን አዉጀዋል።
ቀደምት አርበኞቻችን በየጊዜዉ በሃገራችን ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን በመመከት እና በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ በመዉሰድ አኩሪ ድልን እየተቀናጁ ነጻና ሉዓላዊ ሃገር እንዲሁም የድል አድራጊነት ቅብብሎሽን ለዛሬዉ ትዉልድ ከማስተላለፋቸዉ በተጨማሪ በትዉልዱ ዘንድ ተምሳሌታዊ የድል አድራጊነት መንፈስ እንዲገነባ፣ በማንነቱ እና በሃገሩ እንዲኮራ፣ እንዲከበርና በሔደበት ዓለም አንገቱን ቀናብሎ እንዲሄድ የሚያስችል ጠንካራ መንፈስ አላብሰዉት አልፈዋል ።
ጀግኖች አርበኞቻችን ያበረከቱልንን ነጻነት እና የሉዓላዊነት ቀንን በያመቱ ሚያዚያ 27 ስናከብርም ከዉጭ የተሰነዘረብንን ጥቃት በጋራ ለመመከት የቻልን ህዝብ መሆናችንን አዲሱ ትዉልድም እንዲረዳዉ እና የራሱን አዲስ ታሪክ እንዲፈጠር እንዲሁም የአምስት ዓመቱ ጦርነት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የጀግንነት፣ የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የፍቅር እና የመተሳሰብ ማስመስከሪያ መሆኑን ያሳሰቡት ደግሞ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ናቸዉ።
አርበኞቻችን በአንድነት በመሆን ሃገራቸዉን ከጠላት ወረራ በመከላከል ነጻ ሃገር አስረክበዉናል። የአሁኑ ትዉልድም የአባቶቹን አደራ ለመወጣት ይችል ዘንድ አባቶቻችን የድል አድራጊነት ታሪክ በማስታወስ ዘመኑ በሚጠይቀዉ የትግል አዉድ ላይ በጽናት በመታገል የአባቶቻችንን ጀግንነት ማስቀጠል ይገባናል። የአሁኑ ትዉልድም በአርበኝነት እንዲፈጽማቸዉ የሚጠበቁበት እና ወቅቱ የሚጠይቀዉ በእዉቀት የበለጸገች፣ በኢኮኖሚ የዳበረች ሀገር እንድትሆን ሲሆን። ታላቅ ነበርን ታላቅም እንሆናለን የሚለዉን ሃሳብ እዉን ለማድረግ ከትዉልዱ የሚጠበቅ የአባቶቻችን አደራ ነዉና ይህን ማስቀጠል ወቅቱ የሚጠይቀዉን ጀግንነት በመስራት ለተግባራዊነቱ መትጋት ተገቢ ነዉ።
በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም