አሰልጣኙ ይሳካላቸዉ ይሆን?

0
177

ባለፉት 67 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን 35 ዋና አሰልጣኞች እና ሁለት ጊዜያዊ አሰልጣኞች ማሰልጠናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ::
ከእነዚህ መካከልም አስራ አንዱ በዋና አሰልጣኝነት ተቀጥረው ያገለገሉ የውጪ ዜጋ አሰልጣኞች ናቸው:: የዋልያዎቹ የመጀመሪያው አሰልጣኝ ክሮሺያዊው ስላቫኮ ኮድሪጊጃ መሆኑ በታሪክ ማህደሩ ተቀምጧል::
አሁን ደግሞ አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ አዲሱ የዋሊያዎቹ አለቃ ሆነዋል:: ከ1956 እ.አ.አ እስካሁን ባሉት ጊዜያት ብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማ የሆነባቸው ዓመታት ጥቂት ናቸው::

ኢትዮጵያ በመሰረተችው በግዙፉ የአፍሪካ ዋንጫ መድረክ መሳተፍ እንደ ብርቅ እየታየ መጥቷል:: ሀገራችን በዓለም አቀፍ እና በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ ማጣሪያዎችን ማለፍ ዳገት እየሆነባትም ይገኛል::
አይደለም ከሀገር ውጪ የሚደረጉ መርሀ ብሮችን ማሸነፍ ይቅርና ግብ ማስቆጠር እንደ ትልቅ ውጤት እየታየ ነው::
ከይድነቃቸው ተሰማ እስከ ውበቱ አባተ ያሉት አሰልጣኞች የራሳቸውን አሻራ አሳርፈው አሳልፈዋል::

ሌላኛው ባለ ተረኛ አሰልጣኝ ገ/መድህን ሆነዋል:: አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብሔራዊ ቡድኑን አገልግለዋል:: ውላቸው ሲጠናቀቅም እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ዋና አሰልጣኝ እስኪሾም በኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረ/ማሪያም እየተመራ ቆይቷል:: አሜሪካ ሜክሲኮ እና ካናዳ በጥምረት ለሚያስተናግዱት የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጥቂት ሳምንታት ሲቀሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ አዲሱ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ በመሆን ተቀጥረዋል:: አሰልጣኙ በአንድ ዓመት የውል ስምምነት ነው ኃላፊነቱን የተረከቡት::

አሰልጣኝ ገ/መድን ለብሔራዊ ቡድን ኃላፊነት አዲስ አይደሉም:: ከዚህ በፊት በ2009 ዓ.ም አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከኃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ በጊዜያዊነት ቡድኑን ይዘው ለአምስት ወራት ማገልገላቸው የሚታወስ ነው:: በወቅቱ ሁለት ብቻ መርሀ ግብሮችን ያደረጉ ሲሆን የሌሴቶ እና የሴራሊዮን አቻቸውን አሸንፈው ሥራቸውን ለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አስረክበውታል:: አሰልጣኝ ገ/መድህን አሁን ደግሞ ድጋሚ ሥራውን ተረክበውታል::
አሰልጣኙ ውጤታማ ከሚባሉ አሰልጣኞች መካከል አንዱ ናቸው:: ከዚህ በፊት መቻልን፣ መቕሌ 70 አንደርታን፣ የዋንጫ ባለቤት አድርገዋል::
በ2010 ዓ.ም ደግሞ ጅማ አባ ጅፋር ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ባደገበት ዓመት ዋንጫ እንዲያሳካ በማድረግ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግበዋል:: ጅማ አባ ቡናን እና ሲዳማ ቡናንም ጭምር ያሰለጠኑ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በተመለሰበት ባሳለፍነው ዓመት ድንቅ የውድድር ጊዜን እንዲያሳልፍም አስችለውታል::
በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ መድህን የሠሩት ጠንካራ እና ተፎካካሪ ቡድን በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ዘንድ ቀዳሚ ተመራጭም አድርጓቸዋል::

ከአሰልጣኙ ምን ይጠበቃል?
አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ምንም እንኳ ለአንድ ዓመት ብቻ ብሔራዊ ቡድኑን እንዲመሩ ኃላፊነት ቢሰጣቸውም ተፎካካሪ፣ጠንካራ እና ጥሩ እግር ኳስ የሚጫወት ቡድን መገንባት ይኖርባቸዋል::

በቀጣይ ባሉት የዓለም፣ የአፍሪካ እና የቻን ዋንጫ ማጣሪያዎች ጥሩ ውጤት የማስመዝገብ ግዴታም ተጥሎባቸዋል::
በጥሩ ሥነ ምግባር፣ በጥብቅ ዲሲፕሊን የታነፀ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን መምረጥም ሌላኛው የተሰጣቸው የቤት ሥራ ነው:: ትልቁን የሥራ ኃላፊነት የተረከቡት አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ከክለቡ ሥራቸው ጎን ለጎን ነው ይህንን የሚሠሩት መባሉ ግን በብዙዎቹ ዘንድ ለምን? የሚል ጥያቄ አስነስቷል::

ብሔራዊ ቡድንን ለማሰልጠን የሚሾም አንድ አሰልጣኝ ትኩርቱ በተሰጠው ኃላፊነት ብቻ እንዲሆን፣ ሌላ ተጨማሪ ክለብ ማሰልጠን እንደማይችል በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ሕግ ተቀምጧል:: የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ያስቀመጠውን ሕግ መሻሩ በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ የፈጠረው ጥያቄ አግባብ ይሆናል::
አሰልጣኙ ግን የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ ተወጥተው ተጨማሪ ዓመታትንም የመቀጠል እቅድ እንዳላቸው በጋዜጣዊ መግለጫቸው ተናግረዋል:: በአንድ ጀንበር ብዙ ነገሮችን ማስተካከል ባይችሉም በሂደት ምርጥ ብሔራዊ ቡድን እንደሚገነቡ ጭምር በመግለጽ::
አሁን ላይ በቡድኑ ውስጥ ተተኪዎች እየታዩ እንዳልሆነ ያረጋገጡት አሰልጣኙ የመተካካት ሥራ እንደሚሠሩም ነው በመግለጫቸው የገለጹት::
ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ለ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አራት ጨዋታዎችን ታከናውናለች:: ከሴራሊዮን፣ ከቡርኪናፋሶ፣ከጊኒቢሳው፣እና ከጅቡቲ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል ዋሊያዎቹ::
ይህ የማጣሪያ መርሀ ግብርም ለአዲሱ የዋሊያዎቹ አለቃ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይሆንም :: ምክንያቱም አሰልጣኙን የሚፈትኑ በርካታ ችግሮች እንደሚኖሩ ከወዲሁ ይገመታል::
በቅርብ ዓመታት ሜዳ ላይ የነበረውን እንቅስቃሴ እንኳ ስንመለከት ኳስ ይዞ የመጫወት እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ የመድረስ ችግር እንደሌለበት በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዘመን ተመልክተናል:: ነገር ግን ብሔራዊ ቡድኑ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ግቦችን የማስቆጠር ችግር እንደነበረበት የምናስታውሰው ነው:: በመጀመሪያው የሜዳ ክፍል ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተከላካዮቹ አለመረጋጋት እና የቆሙ ኳሶችን የመከላከል እና የትኩረት ማጣት ችግር እንደነበረባቸው አይዘነጋም::
የአሸናፊነት ሥነ ልቦናቸውን ከፍ ማድረግም አሰልጣኙ የሚጠብቃቸው ሌላኛው የቤት ሥራ ነው:: ይህ ችግር ብሔራዊ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ብቻ ሳይሆን በሀገራችን በነበሩ አንድ አንድ የማጣሪያ ጨዋታዎችም ዓይተናል::
ታዲያ የተሻለ ቡድን ለመገንባትም ችግሩ እንደ ቀላል መታለፍ እንደ ሌለበት በተደጋጋሚ የሚሰጡ አስተያየቶች ናቸው::
በሀገራችን የፊፋን እና የካፍ መመዘኛን የሚያሟላ አንድም ስቴዲየም ባለመኖሩ ዋሊያዎቹ ስደተኛ ከሆኑ ሰነባብተዋል::
በኢትዮጵያ ማድረግ የነበረባቸውን ጥቂት የማይባሉ የማጣሪያ መርሀ ግብርን ከሀገር ወጥተው ማድረጋቸውም የሚታወቅ ነው:: ይህ ችግር ያለ ደጋፊ መጫወት ከሚያመጣው ተፅእኖ ባለፈ የአየር ፀባዩም ሌላ ጣጣ ይዞ ይመጣል:: ከእግር ኳሱ የምናገኘውን ገቢ ሳንዘነጋ ማለታችን ነው::
በእድሳት ላይ የሚገኝው የድሬደዋ ስቴዲየም ከፊታችን ላሉት ሁለት መርሀ ግብሮች ባይደርስም በቅርቡ ግን ሥራ እንደሚጀምር የድሬድዋ ከተማ ከንቲባ መናገሩ የሚታወስ ነው::
ያም ሆነ ይህ ግን የተጋጣሚን የአየር ፀባይ ቀድሞ መረዳት እና ያንን በሚመጥን መልኩ ዝግጅት ማደርግ የአሰልጣኙ ሥራ መሆኑን የብዙዎቹ ምክረ ሀሳብ ነው::

በእርግጥ በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚገኝበት ምድብ የተደለደሉት ሴራሊዮን፣ ጊኒ ቢሳው እና ቡርኪናፋሶ በሀገራቸው ካፍ የሚጠይቀውን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጭ የሚያደርጉ ይሆናል:: ይህንን ተከትሎም ሦስቱም ሀገራት በተመሳሳይ ሞሮኮ ላይ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቻቸውን ለማድረግ ከውሳኔ ላይ ደርሰዋል:: በዚህ መሰረት ኢትዮጵያን ጨምሮ አራቱ የምድቡ ተሳታፊዎች በሞሮኮ ጨዋታዎቻቸው ያከናውናሉ::
ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው እስከ ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ በተከታታይ የተሳተፈችባቸው ጊዜያት ናቸው:: በ1962 እ.አ.አ ደግሞ ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫም ማሳካቷ የሚታወስ ነው::

Bekur /በኲር, [11/13/2023 9:20 AM]
ዋሊያዎቹ በወቅቱ አሰልጣኝ ይድነቃቸው ተሰማ እየተመሩ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ:: ኢትዮጵያ በ1982 እ.አ.አ በመንግስቱ ወርቁ እየተመራች ሊቢያ ላይ በተዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈች ሲሆን ከዛ ጊዜ በኋላ ግን በአፍሪካ መድረክ ለመታየት 31 ዓመታትን መታገስ ነበረባት:: ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በ2013 እ.አ.አ እንድትሳተፍ በማድረግ የዚህ ታሪክ ባለቤት ናቸው:: አልፎ አልፎ ብቅ እያሉ በአፍሪካ መድረክ መሳተፍ ደግሞ የዋሊያዎቹ መገለጫ ሆኗል::

በ2021ንዱ የካሜሮን የአፍሪካ ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኑ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ ከስምንት ዓመታት በኋላ በመድረኩ ሀገራችን መሳተፏም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው::
በሴካፋ ውድድርም ቢሆን ስኬታማ የነበሩት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው፣ አስራት ኃይሌ እና ጀርመናዊ አሰልጣኝ ጁዋን ፊጊ ናቸው::
ዲያጎ ጋርዚያቶ፣ ኤፊ ኦኑራ፣ቶም ሴንትፊንት፣ማሪያኖ ባሬቶ ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ ዋሊያዎቹን ያሰለጠኑ የውጪ ሀገር ዜጎች ናቸው:: ነገር ግን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ሳይችሉ ቀርተው ከሥራቸው ተሰነብተዋል::

አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ በመቻል፣ በመቕሌ 70 አንድርታ እና በጅማ አባ ጅፋር የፈፀሟቸውን ገድሎች በብሔራዊ ቡድኑም ይደግሙት ይሆን ? በጊዜ ሂደት የመሚለስ ጥያቄ ነው::

(ስለሽ ተሾመ)
በኲር ኅዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here